አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ዩኒቨርሲቲውን ላለፉት በርካታ ዓመታት ያውቁታል። ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመሩት እንዴት አገኙት?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ዩኒቨርሲቲውን በደንብ አውቀዋለሁ፤ ለ19 ዓመትም ከመምህርነት ጀምሮ በተለያዩ የስራ ዘርፎች አገልግያለሁ፤ ዩኒቨርሲቲው ያሉበትን ችግሮችና የደረሰበትን ጥሩ ነገርም አውቃለሁ። ዩኒቨርሲቲው ከቀድሞው ጋር ስናወዳድረው በብዙ ነገሮች ተለውጧል፤ እኔም ፕሬዚዳንት ስሆን ጥሩ ነገሮችን ለማስቀጠል ችግሮቹን በመፍታት ደግሞ ዩኒቨርሲቲውን ወደ ፊት አራምዳለሁ ብዬ ነው የተነሳሁት።
አዲስ ዘመን፡- ጥሩ ጎኖችን ማስቀጠል መልካም ነው ግን እርሶ መጥፎ ሆኖ ያገኙት ነገር ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ወደ ፕሬዚዳንትነት በምመጣበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ለበርካታ ዓመታት ሂሳቡ ሳይዘጋ የኦዲት ግኝት ያለበትና በርካታ ገንዘብም እንዴት እንደወጣ የማይታወቅበት ሁኔታ ነበር፤ በዚህ ዙሪያ ላይ በደንብ ተሰርቶና ወጪ ገቢው ታውቆ ስራዎች መቀጠል እንዳለባቸው ይታወቃል።
አዲስ ዘመን፡- ከዩኒቨርሲቲው 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ተበልቷል ይባላል?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ይህ ሀሰት ነው፤ እነዚህ ገንዘቦች በሚወጡበት ጊዜ የአሰራር ጉድለት ነበረባቸው እንጂ ገንዘቡ ተበልቷል ማለት አይደለም። አንዳንዱም በጣም የቆየ ስለሆነ ሂሳቦቹን አስተካክሎና አጥርቶ ማግኘት ባለመቻሉ የተባለ ነው። ይህም ቢሆን ግን በመንግስት አሰራር ያልሄደ ገንዘብ ሁሉ መስተካከል አለበት።
ዩኒቨርሲቲው 50 ሺ ተማሪ አለው። ከዚህ ውስጥ 23ሺ ማደሪያ ተሰጥቶት ከግቢው ቁርስ፣ ምሳና እራት የሚቀርብለት ነው። ይህንን ለማሟላት ደግሞ ጨረታዎች ይወጣሉ፣ አቅራቢዎችም ይመጣሉ ግን አንድ አቅራቢ ዛሬ ላይ አልተሳካልኝም ማቅረብ አልችልም ሊል ይችላል። በዚህ ጊዜ ተማሪ ጾሙን ማደር ስለሌለበት ከህግ ውጭ ግዢዎች ይፈጸማሉ። እናም ከላይ የተነሳው ያልተወራረደ ሂሳብም በዚህ መንገድ የመጣ ነው።
ያለው የግዢ ህግ ምቹ አይደለም እያልን እየተናገርን ነው። መንግስትም ይህንን መስማት መቻል አለበት፤ ለዩኒቨርሲቲዎች የሚፈቀደው የግዢ ስርዓት ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባና ከሌላው የተለየ መሆን አለበት። በመሆኑም ነጻነት በመስጠት በውጤታቸው መገምገም ነው የሚያስፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- የማስተካከያ እርምጃዎቹስ ምን ይመስላሉ?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ባሻገር አንዱ የሚታወቅበት ነገር ምርምሮችን ማድረግ ነው፤ ለዚህ ስራ ደግሞ ምቹ የሆነ አሰራር አልነበረውም። ዩኒቨርሲቲው በጀት ቢመድብም የፋይናንስ አሰራሩ በጣም የተንዛዛና ለሙስና በር የከፈተ በመሆኑ እሱን ማስተካከል ቀዳሚ ስራ ነበር።
ሌላው የሰው ኃይል ቅጥር፣ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ እንዲሁም በግዢ ላይ ከፍተኛ ችግር ነበር ይህንንም ለማስተካከል መስራት ያስፈልግ ነበር።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኦዲት ዙሪያ እስከ አሁን ሲሰራ የቆየው የመንግስትን ህግ ጥሶ ነው፤ይህ እንዲስተካከልም አማካሪዎችን በመቅጠርና ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ያልተዘጉ ሂሳቦችን ያልተሰበሰቡ ገንዘቦችን እንዲሁም ያልተወራረዱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ገንዘቦችን ማስተካከል ያስፈልግ ስለነበር በዩኒቨርሲቲው 13ቱም ኮሌጆች የሂሳብ መዝገቦችን በመሰብሰብና በመፈተሽ ስርዓት ለማስያዝ ተሞክሯል። በዚህም ያለፉት ዓመታት የሂሳብ ሪፖርት ከመሰራቱም በላይ አሁን ላይ የዩኒቨርሲቲው ሂሳብ ምን ይመስላል? ያለተወራረዱ ሂሳቦች የት ናቸው? ማነው ሊጠየቅ የሚገባው? የሚለውን በመለየት ለአንድ ዓመት ስራዎች ተከናውነው የማጣራት ስራው በማጠናቀቅ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ስራ ውስጥ ለሂሳብ ጉድለቶቹ ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎችን አላገኛችሁምን?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- በዚህ ስራ ላይ ያሳለፍነው ጊዜ በጣም ፈታኝ ነበር። መዝገቦች ይጠፋሉ። አንዳንድ የሂሳብ ባለሙያዎችም መዝገቦችን ለመስጠት ፍቃደኛ አይደሉም። ምክንያቱ ደግሞ ፋይሎች በሚወጡበት ጊዜ ብዙ ነገሮች ይጋለጡ ስለነበር ብቻ በጠቅላላው ከእኛ ሰራተኞች ጋርም እየታገልን ነው እዚህ የደረስነው። ይህ ጅማሬው ነው። የዚህን ውጤት ይዘን ወደፊት ደግሞ
የተሻለ ስራ እንሰራለን ብለን እናስባለን።
ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የሚያወጣቸው ጨረታዎችም ከፍተኛ የሆነ ክፍተት የነበረባቸው መስመራቸውን የሳቱ ሙስና የሚታይባቸው ነበሩ። በተሰራው ስራም በሙስና ከዩኒቨርሲቲው ካዝና ወጥቶ ግለሰቦች ዘንድ ገብቶ የነበረን እስከ ሰባት መቶ ሺ ብር የሚገመት ገንዘብ ያስመለስንበት ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ያለው።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው የሚያከና ውናቸው ግንባታዎች መካከል በኮሜርስ ግቢ ውስጥ የተገነባው ህንጻ ደረጃውን ያልጠበቀ ዘመኑ የሚጠይቀውን የኢንተርኔት መሰረተ ልማት ያላሟላ ነው፤ አሁን ላይ ደግሞ ህንጻው አገልግሎቱን በአግባቡ ሳይሰጥ እየተበላሸ ነው፤ በዚህ ላይ ያልዎት ሀሳብ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ዩኒቨርሲቲው በህንጻ ግንባታ በኩል በጣም ኋላ የቀረ ነው። መንግስት ትኩረቱን ያደረገውም አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በመሆኑ ነው። አሁን የዩኒቨርሲቲው መምህራን ቢሮ ቢታይ አንዳንዱ በጣም ያሳዝናል፤ ከዚህ አንጻር ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ዩኒቨርሲቲው የአዳዲስ ህንጻ ግንባታዎች ያስፈልጉታል ተብሎ ነው ወደ ስራ የተገባው።
ግንባታ ሲሰራ በጣም ክትትል ያስፈልገዋል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም ብዙ ገንዘብ ስለሚወጣ ለሙስና የተጋለጠ ነው። ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻም ነው። እኛ ዘንድ ሁለት ህንጻዎች እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ተስተውሎባቸዋል።
ኮሜርስ ብቻ አይደለም የህንጻ ግንባታ ችግር ያለበት ሰፈረሰላም ላይም ያለው የጤና ሳይንስ ኮሌጅም እንደዚያው ችግር ያለበት ነው። በተለይ የኮሜርሱ በጠባብ ቦታ ላይ ጥሩ ህንጻ የተሰራ ቢሆንም በህንጻው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስመር ላይ ስህተት ተፈጥሯል። ስራዎች አንድ ላይ ለኮንትራክተሩ አልተሰጡም። ህንጻው ተሰራ እንጂ ፈርኒቸር የለውም። የኢንተርኔት አገልግሎትም የለውም፤ ለኮንትራክተሩም አብሮ አልተሰጠም። እንደገና ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ቢሆንም የግድ መስተካከል ስላለበት እንደገና እየተሰራ ይገኛል።
ኮሜርስ ህንጻው በውጭ ያምራል ውስጥ ሲገባ ግን በጣም የሚያሳዝን ነው። ቢሮዎቹ የከብት ማደሪያ ነው የሚመስሉት። መስኮት የላቸውም፤ በእኔ አተያይ ግን ከዲዛይኑ ጀምሮ ችግር ያለበት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአንጋፋነቱ አንጻር በተለይም በምህንድስናው ዘርፍ ምን ያህል አበርክቶ አለው?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ዩኒቨርሲቲው በምህንድ ስናውም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ የአገርን ችግር በመለየት ለመንግስት የሚያቀርብ ነው፤ የበርካታ ፖሊሲዎችና የመንግስት መስሪያ ቤት የችግር ጥናቶች የሚካሄዱትም እዚሁ በእኛ ነው። በምህንድስናው ዘርፍም ሁለት ካምፓሶች አሉት። በእነሱ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችም ናቸው የአገሪቱን ግንባታ በተቆጣጣሪነትና በአማካሪነት የሚመሩት።
በሌላ በኩል ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት በተወሰነው መሰረት የምህንድስና ዘርፉን በተመለከተ የአምስት ኪሎ ፕሮፌሰር ናቸው የሚመሩት። ይህ በመሆኑ ደግሞ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በአገር ደረጃ የሚሰሩ የግንባታ ስራዎች እንዴት ይመሩ ? ዲዛይናቸው ምን መሆን አለበት? የኮንትራት አስተዳደሩ ምን መምሰል አለበት? የሚለውን እያማከረ ይገኛል። በተለይ በዩኒቨርሲቲው ለሚካሄዱ ግንባታዎች ከፍተኛ እገዛን እያደረገ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው የአንጋፋ ነቱን ያህል ለትምህርት ጥራት መጠበቅ አርአያ መሆን አልቻለም ይባላልና እዚህስ ላይ ያለዎች ሀሳብ ምን ይመስላል?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ተማሪዎቻችን ከተመረቁ በኋላ ቀጣሪዎቻቸው የሚፈልጉትን እውቀት የያዙ እንዲሆኑ ለማድረግ ወደ 7 ነጥቦች ያሉት ስትራቴጂ ነድፈን ነው የተነሳነው። ይህም ሲባል ተማሪዎች የጽንሰ ሀሳቡንና የተግባር ክህሎቱን ለማወቅ እንዲችሉ መምህራን የትምህርት ሰዓታቸውን ሳያጓድሉ ወደክፍል በመግባት ማስተማር ያለባቸው ከመሆኑም በላይ ተማሪዎቻቸውን ተከታታይ የሆነ ግምገማ በማድረግ የሚሰሩበትን አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ነው።
ሌላው ደግሞ አስተማሪዎች በተማሪዎቻቸውና በጓደኞቻቸው እየተመዘኑ ያሉበት ደረጃ እንዲታወቅ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ሌላው ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እጥረት ያለባቸውን ተማሪዎች እየለየ የክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና ሊሰጥ የሚችል የእንግሊዝኛ ማዳበሪያ ማዕከል በማቋቋም ተማሪዎች ወደእዛ እየሄዱ እንዲማሩ ማድረግ ተችሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ለተጨማሪ እውቀት የሚያዘጋጃቸው እንዲሆን ለማድረግ በተለያዩ ክለቦች እንዲደራጁ የማድረግና እንዴት ከሰው ጋር መግባባት ይችላሉ? ስራ መፈለግ የሚቻለው እንዴት ነው? ችግሮች ሲገጥሟቸው እንዴት መውጣት ይቻላቸዋል? የሚለውን እንዲያውቁ “ኬርየር ዲቨሎፕመንት ሴንተር” በማቋቋምና በየኮሌጁም ተወካዮችን በማስቀመጥ ተማሪዎች ምን ዓይነት ችግሮች አሉባቸው የሚለውን በመለየት በዛ ላይ ተጨማሪ ስልጠናዎችን የመስጠትና ታዋቂ አንደበተ ርዕቱና ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች አነሳሽ ንግግሮች እንዲያደርጉ በማድረግ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨር ሲቲዎች ላይ እየታዩ ያሉ ግጭቶች አሉ። ሆኖም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላይ ይህ ዓይነቱ ችግር እስከ አሁን ላለመታየቱ ሚስጥሩ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- አዎ! ከዚህ ቀደም እንደዛ ሊሆን ይችላል፤ አሁን ግን ይህ ሁኔታ በእጅጉ ተቀይሯል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተከፈተው የኬሪየር ዲቨሎፕመንት ክፍል የስራ ውጤት ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና የምርምር ማዕከል እንጂ የጸብ አውድማ እንዳይሆን ስራዎች ተሰርተዋል። ይህ ሲባል ተማሪዎች ሀሳባቸውን አይገልጹም ማለት አይደለም። ሀሳባቸውን እንዲገልጹ መድረኮች ይመቻቹላቸዋል። አክቲቪስቶቸም ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ሰዎች ወደግቢው በመምጣት ወርክሾፕ እንዲያካሂዱ እንፈቅዳለን። እዚህ ላይ ግን የግቢው ተማሪዎችና ሰራተኞች የፖለቲካ ወገንተኝነትን ይዘው ምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም። ሆኖም እንደ ተመራማሪ እንደ ሀሳብ ሰጪ ግን ውይይት ያካሂዳሉ።
ለግቢው ሰላም መሆን ሌላው አስተዋጽኦ ያበረከተው የተማሪዎች ህብረት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመረጥ ማድረግ መቻሉ እንዲሁም ተማሪዎች ሰላማቸውን በራሳቸው እንዲጠብቁ የተማሪ ስካውቶችን ወደ ስራ ማስገባታችን ትልቅ ለውጥ አሳይቶናል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ማለት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የገዢውም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ ዎች አባላት የሉም፣ እንቅስቃሴም አይካሄ ድም ማለት ነው?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- የፓርቲዎች አባላት የሆኑ ተማሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ። አብዛኛው የፓርቲ መሪዎችም እኮ ያሉት እዚሁ ግቢ ነው። ግን አንዱም ቢሆን የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ በግቢው ውስጥ እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድም። በመጀመሪያ እንደመጣሁ ያደረኩትም ዩኒቨርሲቲው ገለልተኛና እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የፖለቲካ ሀሳቦች ላይ መመራመርና ሀሳብ ማንሸራሸር እንጂ ወገንተኛ መሆን አይቻልም የሚል ነው። አሁን ላይ በግቢው ውስጥ የኢህአዴግም ሆነ የሌሎች ፓርቲዎች ቢሮ የለም። ለዚህም ነው ግቢው ሰላም የሆነው፤ የፖለቲካ ተሳትፎን አደርጋለሁ የሚል ካለ ከግቢው ውጪ ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የግጭት መነሻ እየሆኑ ነውና እርስዎ ከራስዎት ግቢ ተሞክሮ አንጻር ለሌሎች ምን ይመክራሉ?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ዩኒቨርሲቲው በዚህ ረገድ ያለው ተሞክሮ ከፍተኛ ነው፤ ከዚህ በፊትም ይህንን ተሞክሮ ለማስፋት ትልልቅ የሰላም ኮንፈረንስ አካሂዷል፤ የተማሪዎች ህብረትንም በገንዘብ በመደገፍ የሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ህብረት በመጋበዝ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ተሞክሯል። በጠቅላላው ግን ከዩኒቨርሲቲው ትምህርት መወሰድ ያለበት የትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማርና ከምርምር ስራ ውጪ ከፖለቲካ ግርግር ነጻ መሆን እንዳለባቸው ነው።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የገዢውም ፓርቲ ይሁን የማንም የፖለቲካ መንቀሳቀሻ አይደለም። መንግስትንም እጁንና እግሩን እንዲሰበስብ ወደ ዩኒቨርሲቲው መግባት እንደማይችል አቋም ይዘናል። መንግስትም ሰምቶናል። እኛ ዘንድ ያሉት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ቢሆኑ ተነጋግረን ከአንዳንዶቹ ጋር መግባባት ላይ ደርሰናል። ሌላውም ዩኒቨርሲቲ ማድረግ ያለበት መጀመሪያ ግቢውንና አመራሩን ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ነጻ ማውጣት ነው፤
አዲስ ዘመን፡- የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪው ትስስር በጣም ደካማ ነው ይባላል፤ በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚታየው ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ ባሻገር ለተግባር ልምምዳቸው ትኩረት አይሰጥም ይህ እውነት ነው?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እያሉ ከኢንዱስትሪው ጋር መገናኘት አለባቸው፤ ይህ ሲሆን ኢንዱስትሪው ምን ይፈልጋል የሚለውን በቀላሉ ለማወቅ ይችላሉ። በመሆኑም ተማሪዎች ወደ ኢንዱስትሪ ሄደው ስራው ምን እንደሚመስል እንዲያዩ ለማድረግ እየተሰራ ከመሆኑም በላይ የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ተቋቁሟል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ግን የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ትስስር እንደ ኢንጂነሪንግ ያሉ የትምህርት ዘርፎች ላይ ብቻ ያጠነጠነ ነው፤ ሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ክፍሎችስ ይህ አይነቱ ትስስር ስለማያስፈልጋቸው ነው ያልተሰራበት?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- ኢንጂነሪንግ ብቻ የነበረው ድሮ ነው። አሁን በማንኛውም መስክ የሚሰለጥን ሁሉም ተማሪ ይህንን ፕሮግራም የሚሳተፍበትና ክረምቱን ከትምህርት ዓይነታቸው ጋር ተዛማጅ ስራ ወደሚሰሩ ተቋማት ይላካሉ። በእርግጥ ስራው ባለፈው ዓመት የተጀመረ ነው። መንግስት ወደፊት በትምህርት ካሪኩለሙ ውስጥ ይህንን አሰራር አስገዳጅ አድርጎ እስከሚያቀርበው ድረስ እኛ ቀደም ብለን ጀምረነዋል። ይህም በጣም ጠቃሚ ሆኖ አግኝተነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲው ቀደም ባለው ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እንደነበር ይታወሳል፤ አሁን ላይ ግን ይህ ቀዳሚነቱ እንደወረደ ይነገራል፤ በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር ጣሰው፤ አገሪቱ ላይ የመጀመሪያው እንደመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃም ያለው ተቀባይነት ቢሆን ጥሩ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜም እያሻሻልን ነው፤ በቀደመው ጊዜ ከዓለም 1ሺ300ተኛ ነበርን፤ አሁን 890 እስከ 900ኛ ደርሰናል፤ በአፍሪካ ወደ 16 ደረጃ ላይ ነን። ይህንን ወደ 10ኛ ደረጃ ለማምጣት እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- ባለኝ መረጃ ዩኒቨርሲቲውን ግንባር ቀደም ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል በተለይም ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ስራዎችን በመስራት በተጽዕኖ ፈጣሪ መጽሄቶች ላይ ማሳተም ነውና ከዚህ አንጻር ደግሞ ደካማ ነው ይባላል። እርስዎ በዚህ ይስማማሉ? ከሆነስ ምክንያቱ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- የዛሬ ስድስት ዓመት ከተራ ሪፖርቶች ውጪ በደንብ የተለፋባቸውና ተጽዕኖ የመፍጠር ኃይል ያላቸውን ህትመቶች በዓመት 200 ወረቀት ብቻ ነበሩ ይቀርቡ የነበረው፤ እያደገ እያደገ መጥቶ ባለፈው ዓመት 1000 ደርሷል። ዘንድሮ ደግሞ 2000 ደርሷል። ይህም ቢሆን ግን ዩኒቨርሲቲው 3000 የሚደርሱ ሰራተኞች አሉት፤ ከዚህ ቁጥር አንጻር በጣም አነስተኛ ነው። ቢያንስ በዓመት አሁን ካለው በላይ መሆን አለበት ብለን እናስባለን። እንጠብቃለንም።
አዲስ ዘመን፡- የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ሰራተኞች በምርምር ስራዎች መሳተፍና ጽሁፎቻቸውንም ማሳተም እንዳለባቸው ይታ ወቃል። በተለይም ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ የሚማሩ ተማሪዎችስ በዚህ ስራ ላይ ተሳትፎ ማድረግ የለባቸውም? ካለባቸውስ እየተደረገ ነው? ካልተደረገስ ለምን ማድረግ አልተቻለም?
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- በዓመት ከ1000ሺ በላይ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች እንዲሁም 300 የሚሆኑ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ይመረቃሉ፤ እነዚህ ተማሪዎች ጽሁፋቸውን ያሳትሙ አያሳትሙ ማንም የሚከታተላቸው የለም። ከዚህ በኋላ ግን አንድ የሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪ ከመመረቁ በፊት ሁለት ወረቀቶችን እንዲያሳትም ግዴታ ተቀምጧል። የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂውም እንደዚያው የመመረቂያ ጽሁፉን ከሰራ በኋላ ቢያንስ አንድ ሊታተም የሚችል ወረቀት ሊጽፍ ይገባል። ይህን ህግ ከአንድ ዓመት በኋላ ተግባራዊ እናደርገዋለን።
አዲስ ዘመን፡- አመሰግናለሁ
ፕሮፌሰር ጣሰው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 3/2011
እፀገነት አክሊሉ