ቅድመ ጥንቃቄን የሚሻው የመሬት መንቀጥቀጥ

ከትናንት በስቲያ ምሽት 2 ሰዓት ገደማ በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ የተከሰተውና በሬክተር ስኬል 4 ነጥብ ዘጠኝ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ መዲናችን አዲስ አበባ ድረስ የተሰማ ነበር። የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰተበት አካባቢ የተወሰኑ ቤቶች መፍረሳቸውንና የመሬት መሰንጠቅ እንዳጋጠመም የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ማስታወቁ ይታወሳል። ንዝረቱ በተሰማበት በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ያሉ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤ መፍጠሩም ተስተውሏል።

ለመሆኑ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ወይም ርዕደ መሬት መነሻው ምንድነው? የመሬት መንቀጥቀጥ መቼና በምን ያህል መጠን ሊከሰት ይችላል የሚለውን መተንበይ ይቻላል ወይ? በሀገራችን ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ የሆኑ ከተሞች የትኞቹ ናቸው? ክስተቱ የከፋ አደጋ እንዳያደርስ ለመከላከል ምን አይነት የቤት ሥራ ይጠብቀናል? በሚሉት ላይ ያነጋገርናቸው የዘርፉ ምሁራን የሚከተለውን መረጃና አስተያየት ሰጥተውናል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የጂኦ ፊዚክስ፣ ስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ኤልያስ ሌዊ ከሰሞኑ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከአዲስ አበባ በ125 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ ከበሰቃ ሀይቅ በስተሰሜን በኩል ያለ ቦታ ላይ የተከሰተ መሆኑን አንስተው፤ የመሬት መንቀጥቀጡ በመሬት ውስጥ ተጉዞ ሞገዱ አዲስ አበባ ከተማ ድረስ መሰማቱን አስታውሰዋል።

እስካሁን ድረስ በዘርፉ በተደረጉ ጥናቶች የመሬት መንቀጥቀጥ በዚህ ጊዜ ሊከሰት ይችላል ተብሎ መተንበይ እንዳልተቻለ የሚናገሩት ዶ/ር ኤልያስ፤ ነገር ግን በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያሉ አካባቢዎች ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን ማወቅ መቻሉን ይገልጻሉ።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል የጂኦ ፊዚክስ መምህር የሆኑት አቶ ገነነ ካዊሶም ልክ እንደ ዶ/ር ኤልያስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ መቼ ይከሰታል የሚለው ላይ ሳይንስ እንዳልደረሰበት ይናገራሉ። ከተጋላጭነት አኳያ ግን ከዚህ ቀደም አንድ የነበሩና የተከፈሉ ቦታዎች ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸው የሚታወቅ መሆኑን ያብራራሉ።

እርሳቸው እንዳሉት፣ ለክስተቱ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል ታላቁ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ተብሎ በሚጠራውና ከቀይ ባህር ጀምሮ አፋር፣ አዳማ፣ ሀዋሳና ዲላን ይዞ ኢትዮጵያን እየከፈለ የሚሄደውና የቱርካና ሐይቅን እየቆረጠ ሄዶ እስከ ሞዛንቢክ ድረስ የሚዘልቀው አካባቢ ለመሬት መንቀጥቀጥ አልፎም ለእሳተ ገሞራና መሰል የመሬት እንቅስቃሴዎች ተጋላጭ ነው።

ሐዋሳ ከተማ ላይ ባለፈው ዓመት ብቻ ሦስት ጊዜ እምብዛም ያልተስተዋሉ የመሬት መንቀጥቀጦች መከሰታቸውን ማስተዋላቸውንም ተናግረዋል። አዳማ እና ዲላ ከተሞችም ለዚህ ተጋላጭ መሆናቸውንም አያይዘው አንስተዋል።

ዶ/ር ኤልያስ ደግሞ በስምጥ ሸለቆ አቅራቢያ ያሉ አካባቢዎችን ጨምሮ መዲናችን አዲስ አበባም ለመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የተጋለጠች መሆኗን ያነሳሉ። ክስተቱ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ መጠነ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚያሻም አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።

በርካታ ባለድርሻ አካላት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን ለመከላከል ብዙ ሥራዎች እየሠሩ እንዳሉ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ይህ ግን በቂ እንዳልሆነና ሰፊ እና ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚያሻ ይገልጻሉ። ለምርምሩ መስክ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በምርምር የሚወጡ ውጤቶችን ግብዓት አድርጎ ከመጠቀም አንጻር እንደ አደጋ ዝግጁነት፣ የመከላከያ ሠራዊት የከተማ ልማትና መሠል ተቋማት በትብብርና በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

አዲስ አበባን ጨምሮ ለአደጋው ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚሠሩ ሕንፃዎችን የሚገነቡ ኮንትራክተሮች፣ ግንበኞችና ሌሎችም ሲሚንቶን ከጭቃ ጋር እያቦኩ መለሰን ሳይሆን ደረጃውን የጠበቀ ሕንፃ መገንባት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢመጣ “እኔ፣ ልጆቼ፣ ቤተሰቤ የሚቀበሩበት የመቃብር ስፍራ ሳይሆን የመኖሪያ ቦታ ነው የምሠራው” ብሎ በጥንቃቄ መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ ይመክራሉ።

እንደ ከተማ ልማትም ሕንፃዎችን ጨምሮ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች የአደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገነቡ ሕንፃዎች ምን መሆን አለባቸው አርክቴክቶቻችንም ምን አይነት ሕንፃ ቢገነባ የመሬት መንቀጥቀጥ ጉዳትን ሊቀነስ ይችላል ብለው ማሰብ አለባቸው ይላሉ።

ከግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች እያደረግን ድንገት የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለብን? የሚለውን በየትምህርት ቤቶች ውስጥ ማስተማር እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ዶ/ር ኤልያስ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያጠቃቸው ሀገራት ዜጎች ምን አይነት ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚባ በትምህርት ሥርዓታቸው ውስጥ አካተው እንደሚያስተምሩም ለአብነት አንስተዋል።

የመሬት መንቀጥቀጥ በሚከሰትበት ጊዜ ምንም እንኳ ክስተቱ ፋታ የሚሰጥ አይነት ባይሆንም መረጋጋትና አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ የአደጋ ተጋላጭነትን እንደሚቀንስ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የመሬት መንቀጥቀጡ በሚከሰትበት ጊዜ ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች ጠረጴዛ ስር በመግባት፣ ጭንቅላታቸውን በእጃቸው ሸፍኖ መቀመጥ፣ የሚነድ ነገር ካለ ተቀጣጥሎ አደጋ እንዳያስከትል ቶሎ ማጥፋት የተሻለ እንደሚሆን ይመክራሉ።

በዚህ ጊዜ ሊፍት ወይም አሳንሰር መጠቀም ትልቅ ስህተት ነው ያሉት ዶክተሩ፤ ውጪ ያሉ ሰዎች ደግሞ ራሳቸውን የኤሌክትሪክ ፖል ካለበት አካባቢ ማራቅ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።

አቶ ገነነ በበኩላቸው፣ ጂኦሎጂስቶች “የመሬት መንቀጥቀጥ ሰው አይገልም ነገር ግን ሕንፃ ነው” የሚል ብሒል እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ክስተቱ በሚፈጠርበት ጊዜ መደናገጥ ሳይሆን በተቻለ ፍጥነት ከሕንፃ መውጣት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። ከዚህ ቀደም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት ተማሪዎች ከሕንፃ ዘለው ለመውጣት የመፈጥፈጥ አደጋ እንደገጠማቸው አስታውሰው፤ ከሕንፃ መውጣት ከሕንፃ

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም

Recommended For You