
አዲስ አበባ፡- በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰላም የሰፈነበት የመማር ማስተማር ሂደት እንዲፈጠር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላፊዎችና የቦርድ አመራሮች ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው ተገለፀ፡፡
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ በተመለከተ በተጠናቀረው የመስክ ሪፖርት ዙሪያ ትናንት በኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል ውይይት ሲደረግ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉት፤ በአሁን ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የብጥብጥና የሁከት መነሻ ሆነዋል፡፡ ችግሮቹ ውጫዊም ሆኑ ውስጣዊ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቦርድ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በመወጣት ረገድ ችግሮች ታይቶባቸዋል፡፡
በተወሰኑ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የተቋማቱና የቦርድ አመራሮቹ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ችግሮች የሚፈቱበት አሰራር መዘርጋታቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሌሎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ የአካባቢው ማህበረሰብ ተቋማቱ ውስጥ በመግባት ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቦርድ አመራሮች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
በየአካባቢዎቹ ያለው አለመረጋጋት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዳይስፋፋና ተቋማቱን የብዝሀነት መግለጫ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉትን የግብዓትና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ለመፍታት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ባገናዘበ መልኩ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡
የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚነሱ ሁከቶችና ብጥብጦች እየተባባሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሮቹን በማስቆም ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቦርድ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣታ ቸውን በተደረገው የመስክ ግምገማ መረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዶክተር ሂሩት ገለፃ፤ የተያዘው የትምህርት ዘመን አጀማመሩ ጥሩ የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በቡድን በመሆን በተደረጉ ግጭቶች እስካሁን አምስት ተማሪዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ የግጭቶቹ ምክንያት ደግሞ በፖለቲካ አመለካከት የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ናቸው፡፡
ችግሩን ለመፍታት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አዳዲስ የቦርድ ሰብሳቢ የመመደብ ሥራ መከናወኑን በመጥቀስ፤ በምክትል ሰብሳቢነት ደግሞ የከተማ ከንቲባዎችና የዞን አስተዳዳሪዎች መካተታቸውን አመልክተዋል፡፡ በአዲስ መልክ የተደራጀው የቦርድ ሰብሳቢ ብቃታቸውና ለውጭ አምጭነታቸው ታይቶ የተመደቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተደረገውን የመስክ እንቅስቃሴ ሪፖርት ያቀረቡት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉት፤ በአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የቦርድ አመራር መጓደል፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳን ቶች ጋር ተናቦ አለመሥራት፣ አብዛኛው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምክትል ፕሬዚዳንትና በተወካይ መመራታቸው እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች በተማሪዎቹ ተቀባይነት ማጣታቸው በክፍተትነት ተገምግሟል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 4 /2011
መርድ ክፍሉ