የ12ኛ ክፍል ውጤት ማሽቆልቆል ሥነልቦናዊ ጫናውና መፍትሔው?

ዜና ትንታኔ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ውጤት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያሽቆለቆለ ይገኛል። በዚህ ምክንያትም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በዘንድሮው ዓመት ከአንድ ሺ በላይ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አላሳለፉም፡፡ ይህ ሁኔታ በሌሎች ተማሪዎች ላይ የሚኖረው ሥነልቦናዊ ጫና ምን ይሆን?

በአማኑኤል ሆስፒታል የተመላላሽ ሕክምና ክፍል ኃላፊ እና የሥነ አዕምሮ ሕክምና ፕሮፌሽናል ስፔሻሊስት አቶ ሳሙኤል ቶሎሳ እንደሚናገሩት፤ የ12ኛ ክፍል ውጤት ማጣት በተለይ በሥነ አዕምሮ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፤ ይህ ሲባል ውጤት በሚጠብቁት ተፈታኝ ተማሪዎች እና እነሱን አርዓያ አድርገው በሚከተሉት የታችኛው ክፍል ተማሪዎች ላይ ተመሳሳይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡

አብዛኛው ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ ሕልም ይኖረዋል፤ ያንን ለማሳካት ደግሞ ዋነኛ መንገዱ ትምህርት መሆኑን በመረዳት ይጥራል፤ ጎበዝ የሚባሉት ተማሪዎች አርዓያ በማድረግ እነሱን ይከተላሉ፡፡ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የ12ኛ ክፍል ውጤት እያሽቆለቆለ በመሆኑ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የሥነ አዕምሮ ጫና እያመጣ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡

በተለይ በውጤቱ ላይ ተማምነው ይህንን አሳካለሁ እንዲህ እሆናለሁ በማለት ሕልም የነበራቸው ተማሪዎች ውጤቱ በሚፈልጉት ደረጃ ሳይሳካ ሲቀር ኅዘን፣ ብስጭት እና መከፋት ውስጥ ስለሚገቡ የተስፋ መቁረጥ ሥነልቦናዊ ጫና እንደሚከሰትባቸው ያስረዳሉ፡፡

ይህ ደግሞ ምክንያታዊ ስለሆነ ከጊዜ ብዛት ማኅበረሰቡ በሚሰጠው ምክር እየቀነሰና በራሱ ጊዜ ጫናው እየቀለለ የሚሄድ ቢሆንም፤ አንዳንዶቹ ላይ ግን ከፍተኛ የሥነ አዕምሮ ጫና በመፍጠር ራስን እስከ መጉዳት እንደሚደርስ ይጠቅሳሉ፡፡

በተከታታይ ዓመታት የተከሰተው የውጤት ማሽቆልቆል የ12ኛ ክፍል ተማሪ ተፈታኞች ‹‹እኔም እወድቃለሁ›› በሚል ከፍተኛ ፍርሃት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እየከተታቸው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ ምንም ውጤት ባላስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በጣም የመጨነቅ እና የመፍራት ስሜት ሊኖራቸው እንደሚችልና ውጤት አናመጣም የሚል ድምዳሜ ውስጥ እንደሚገቡ ያብራራሉ፡፡

እንደ አቶ ሳሙኤል አባባል፤ በተመሳሳይ ብዙ ጊዜ ወላጆች ከራሳቸው በላይ የልጆቻቸው ቀጣይ ሕይወት ያስጨንቃቸዋል፤ በመሆኑም ልጆቻቸው ተጎድተው ሲያዩ መላው ቤተሰብ ይረበሻል ቤት ውስጥ ደስታ ይጠፋል፤ በተለይ ልጁ/ልጅቷ ውጤት ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ከሆነ የልጃቸው ጤንነትም ጭምር ያስጨንቃቸዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት በተከታታይ ማሽቆልቆል በትምህርት ለውጥ አይመጣም የሚል የተሳሳተ እና አደገኛ አመለካከት ያስከትላል፤ ሀገር የምትለወጠው እና የምትገነባው በትምህርት እና በተማረ የሰው ኃይል መሆኑን እንዲዘነጋ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋታቸውን ያስረዳሉ፡፡

ይህ ከባድ ጉዳይ መፍትሔ ያስፈልገዋል በተለይ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ላይ ሌሎች ብዙ አማራጮች እንዳሉ ማስረዳት እንደሚስፈልግ በመጥቀስ፤ ወጣቶች ያሉበት ዕድሜ ከፍተኛ ጉጉት ያለበት ጊዜ በመሆኑ ጥቂቶቹ ካሉበት ሲወርዱ ከፍተኛ የመጎዳት ስሜት እንደሚኖራቸው ይገልፃሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሱስ ውስጥ መግባት፣ ራስን ማግለል፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ መነጫነጭ፣ ለረጅም ሰዓት ቤት ውስጥ መቀመጥ፣ በተደጋጋሚ ማልቀስ እና ለረጅም ሰዓት መተኛት ምልክቶች ወደ ሥነ ልቦና ሐኪም መውሰድ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ፡፡

የማኅበረሰብ አንቂዎች እና ሶሻል ሚዲያ በስፋት የሚታወቁ ሰዎች በውጤቱ እና በትምህርት ዙሪያ ከመቀለድ እና ከመሳለቅ ይልቅ በምን መልኩ አማራጮችን መጠቀም እንደሚቻል፣ በኢኮኖሚ የሚያሳድጉ የሥራ ዘርፎች መኖራቸውን እንዲሁም በኑሮ ራሳቸውን የተቀየሩ ኢንተርፕርነር ግለሰቦች አርዓያ በማድረግ በተከታታይ ማሳየት ላይ ትኩረት ቢያደርጉ መልካም ነገር እንደሚፈጠር ያብራራሉ፡፡

በአማኑኤል ሆስፒታል የክሊኒካል ሳይኮሎጂ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሥዩም ዘውዴ በበኩላቸው፤ ትምህርት ሰዎች ግባቸውን ለማሳካት የሚሄዱበት አንደኛው መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ ተፈለገው ሽግግር ለመድረስ ደግሞ ፈተና አንዱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ የተነሳ የፈተና መውደቅ በተፈታኞች እና በዙሪያቸው ላሉት ተከታይ ተማሪዎች እንዲሁም ለቤተሰብም ጭምር አሉታዊ ጫና እንደሚያሳድር ይገልፃሉ፡፡

እንደ አቶ ሥዩም ገለፃ፤ የውጤት ማሽቆልቆል ተከታይ ተፈታኞች ላይ ፍርሃት እና ተስፋ መቁረጥ ያስከትላል። በመሆኑም አምና እና ዘንድሮ ፈተናው ከበፊቱ የተለየ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስለነበረ ይህ በራሱ አዲስ ፈተና በመሆኑ በቀጣይ የተማሪዎች የኮምፒተር ዕውቀት ለማሻሻል እና ከውድቀት እንዲማሩ በተለያየ መንገድ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ፡፡

አሁን ላይ የሚራገቡት አሉታዊ ጎኖች ብቻ ናቸው፤ ይህ ደግሞ መፍትሔ ሊሆን አይችልም የሚሉት አቶ ሥዩም፤ በመገናኛ ብዙኃን እና በማኅበራዊ ገፆች ላይ በአወንታዊ መንገድ አማራጮችን በማሳየት መረጋጋትን መፍጠር ቢቻል የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም በተለይ ተማሪዎች ላይ ሥራዎች እንዲሠሩ እና የወደቁት ተማሪዎችም ከገቡበት የሥነ ልቦና ውድቀት አገግመው ሌላ አማራጭ መኖሩን ተረድተው እንዲሠማሩ መደረግ አለበት፡፡ ሁሉም በዘርፉ ለትምህርት ትኩረት ቢሰጥ መሻሻሎች ማምጣት እንደሚቻል ያመለክታሉ፡፡

ትምህርት ቤቶች፣ መምህራንና ባለድርሻ አካላት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ረገድ የበኩላቸው ድርሻ እንዲያበረክቱ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ምሑራኑ ይገልጻሉ፡፡ በሁሉም ደረጃ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ሲቻልም ሁሉም ተማሪ በሥራውና በድካሙ ልክ ውጤት በማምጣት የውጤት ማሽቆልቆሉ ችግር እየተፈታ እንደሚሄድ ምክረ ሀሳባቸው ሰጥተዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You