ለስድስት ሺህ ጥንዶች የመካንነት ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ማዕከሉ አስታወቀ

አዲስ አበባ፡- ባለፉት አምስት ዓመታት ስድስት ሺህ ለሚሆኑ ጥንዶች ከበድ ያለ የመካንነት ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የመካንነትና ሥነ ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል አስታወቀ፡፡

የማዕከሉ ኃላፊ ዶክተር መሠረት አንሳ ለኢፕድ እንደገለፁት፤ የሕክምና አገልግሎቱ መሰጠት ከጀመረ አምስት ዓመት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታትም ስድስት ሺህ ያህል ጥንዶች በቴክኖሎጂ የታገዘ ከፍተኛ ደረጃ የመካንነት ሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡

በዓመት 16 ሺህ ያህል ጥንዶች የመካንነት ምርመራ ለማድረግ ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ ከእነዚህ ውስጥ ከ700 እስከ አንድ ሺህ የሚሆኑት ቀላል የመካንነት ሕክምና እንዲሁም ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ 500 የሚሆኑት ከበድ ያለ የመካንነት ሕክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡ በድምሩ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ጥንዶች ቀላልና የላቀ የመካንነት ሕክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቅሰዋል፡፡

በማዕከሉ ከምርመራ ጀምሮ በካሜራ የታገዙ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች እንደሚሰጡም ኃላፊዋ ተናግረው፤ የወንድና የሴት እንዲሁም የሁለቱም ፆታ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት በግልና በመንግሥት እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡ ሕክምናው እንደችግሩ ሁኔታ እንደሚወሰንም ነው ኃላፊዋ የጠቆሙት፡፡

የመካንነት ሕክምና በባሕሪው ውድና ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ በርካታ ታካሚዎች ፍላጎቱ ቢኖራቸውም በአቅም ማነስ ምክንያት ተመርምረው ወደ ሕክምናው እንደማይገቡ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ በየዓመቱ ወደ ማዕከሉ ከሚመጡና ምርመራ ከሚያደርጉ 16 ሺ ጥንዶች ውስጥ ቢበዛ አንድ ሺህ 700 ያህል ጥንዶች ብቻ ወደ ሕክምና እንደሚገቡም ጠቁመዋል፡፡

የመድኃኒት ውድነት፣ የዘር ፍሬ ላለቀባቸው ጥንዶች ከሌሎች ልገሳ አለማግኘት፣ የላቁ የዘረ መል ምርመራዎችን ለማድረግ የሚያስችሉ መሣሪያዎች አለመኖር ብሎም የሕክምናው ተደራሽነት ውስን መሆን የመካንነት ሕክምና ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

አሁንም ድረስ የመካንነት ሕክምና ስለመኖሩ ያላወቀ ማኅበረሰብ እንዳለ የተናገሩት ዶክተር መሠረት፤ እንዲያም ሆኖ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገልግሎቱ ፈላጊ በመኖሩ ሕክምናውን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የሕክምናውን ተደራሽነት ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋት ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ወደ ማዕከሉ መጥተው የሚሠለጥኑበት የሕክምና ባለሙያዎች መኖራቸውንም ዶክተር መሠረት ጠቁመው፤ ነገር ግን ሕክምናውን ለማስጀመር የሚያስችል በቂ ሀብት ባለመኖሩ አስካሁን ድረስ ከአንድ በስተቀር ከአዲስ አበባ ውጪ የተከፈተ የመካንነት ሕክምና ማዕከል አለመኖሩን አመልክተዋል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የመካንነትና ሥነ ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል 7 ሰብ እስፔሻሊስትና 5 ሠልጣኝ ሐኪሞችን በመያዝ ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ከኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሌና ሶማሌ ላንድ ለሚመጡ ጥንዶችም አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You