አዲስ አበባ፡ – የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎትን የተመለከቱ ሁለት ደንቦችን አጸደቀ። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትናትናው ዕለት ባካሄደው 39ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ39ኛ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔዎች ከሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ደንብ እና የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሠራተኞች ደንብ ተጠቃሽ ናቸው።
ደንቡ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ሃላፊነት ለመወጣት፤ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለደንበኞች ለመስጠት እንዲሁም ከፓስፖርት የቆይታ ጊዜ ጋር በተያያዘ ያሉ ጥቄዎችን መፍታት እንዲችል የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
እንዲሁም መሥሪያ ቤቱ የጀመረውን ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግና በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር ለማስቻል የአገልግሎቱን ልዩ ባህሪይ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሠራተኞች መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን ፤ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ተወያይቶ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረጉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ ብሔራዊ የመካከለኛ ዘመን 2017-2020 የገቢ ስትራቴጂ ላይ የተወያየ ሲሆን ስትራቴጂው የታክስ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ለግል ኢንቨስትመንቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የታለመ መሆኑም ተነስቷል።
ይህም የታክስ ፖሊሲዎችን እና አስተዳደራዊ ሪፎርሞችን እንዲሁም ማሻሻያዎችን ለመተግበር የሚያስችል እና ከ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ተደርጎ የቀረበ ነው። ምክር ቤቱም በስትራቴጂው ላይ በዝርዝር በመወያየት አጽድቆታል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ከማልታ ሪፐብሊክ መንግሥት እና ከቻድ ሪፐብሊክ መንግሥት ጋር የተፈራረማቸውን የአየር አገልግሎት ስምምነቶችን ለማጽደቅ የቀረቡ ሁለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቷል።
ስምምነቶቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ማንኛውም የማልታ ከተማ እና ወደ ኢንጃሚና ከተማ በ3ኛና 4ኛ ትራፊክ መብት የመንገደኛ እና የጭነት የበረራ ምልልስ ለማድረግ፣ ተወካይ አየር መንገዶችን በሽርክና ለማሠራት፣ በ5ኛ ትራፊክ መብት ወደ ተመረጡ መዳረሻዎች በረራ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተነስቷል።
ረቂቅ አዋጆቹ ሀገሪቱ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት፣ ለወጪ ንግድ፣ ለቱሪዝም፣ ለሥራ እድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ስምምነቶች በመሆናቸው ምክር ቤቱ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ውሳኔ ሰጥቷል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የዓለም አቀፍ ምልክቶችን ከሚመለከተው የማድሪድ ስምምነት ጋር የተዛመደውን ፕሮቶኮል ለማጽደቅ በወጣ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።
በውይይቱም ፕሮቶኮሉ የንግድ እና የአገልግሎት ምልክቶች በሀገር ውስጥ ሕግ ከሚደረግላቸው ጥበቃ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥበቃ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑም በተጨማሪ ምርቶች እና አገልግሎቶች ያላግባብ ለሌሎች ጥቅም እንዳይውሉ በቂ ጥበቃ የሚደረግበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
እንዲሁም ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችና አገልግሎቶች እንዲኖሩና የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ምክር ቤቱ በፕሮቶኮሉ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የፓሪስ ኢንዱስትሪያዊ ንብረት ኮንቬንሽንን ለማጽደቅ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።
በውይይቱም በአባል ሀገራት መካከል ሕብረት በመፍጠር የኢንዱስትሪ ንብረትን ለመጠበቅ፣ የፈጠራ ባለቤትነት፣ የኢንዱስትሪ ንድፎች፣ የንግድና የአገልግሎት ምልክቶች፣ የንግድ ስሞች፣ የምርቶች ምንጭ አመልካች ምልክቶች ለመጠበቅ የሚያችል መሆኑ ተነስቷል።
በመሆኑም የኮንቬንሽኑ መጽደቅ ሀገሪቱ ለምታደርገው የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ድጋፍ የሚሆን ሲሆን ከአባል ሀገራቱ ለሚነሱ የኢንዱስትሪያዊ ንብረት ጥበቃን ለሚመለከቱ ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።
በዚህም ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 22 ቀን 2017 ዓ.ም