ከስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በየመንና ሶሪያ የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽተው እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ የሁለቱ አገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ 1 ሺ 900 የየመን እንዲሁም 98 የሶሪያ በድምሩ 1 ሺ 998 የሁለቱ አገራት ስደተኞች ይገኛሉ፡፡
በየመንና ሶሪያ ለዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ስደተኞች ኑሯቸውን በተለያየ መልክ እየገፉ መሆኑ የአደባባይ እውነታ ነው፡፡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአዲስ አበባ የተወሰኑ ስፍራዎች ተዘዋውሮ እንደታዘበው ከሁለቱ አገራት የመጡ ስደተኞች ከከተማው ነዋሪ ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን፤ በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ ስደተኞችም ይገኛሉ፡፡
ከየመን መዲና ሰንዓ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ የሚናገሩት ሳላህ አህመድ ያገኘናቸው ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ በማር መሸጫ ሱቅ ውስጥ ከሌሎች ከአገራቸው ከመጡ ወዳጆቻቸው ጋር ነበር፡፡ በአገራቸው በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የቅርብ ቤተሰብ በመበታተኑና የነበራቸውን ንብረት በመውደሙ ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከገቡበት ቀን ጀምሮ የሰው ሀገር ውስጥ ያሉ እንደማይመስላቸው የሚናገሩት ሳላህ ኢትዮጵያዊያንም እንደ ውጭ ዜጋ እንደማያዩዋቸው ነው የገለጹት፡፡ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቻቸው እኩል የሚንከባከቡ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን በመግለጽ የተለያዩ ገቢ ማግኛ ሥራዎችን እንዲሠሩ በጊዜያዊነት ማረፊያ ቤት የሚሰጡም መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡
አቶ ሳላህ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የሚገኘው የየመን ኤምባሲና የኢትዮጵያ መንግሥት ያመቻቹላቸውን እድል ተጠቅመው አንዳንድ ገቢ ማግኛ ሥራዎችን እየሠሩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀዱ ኑሯቸውን ቀላል አድርጎላቸዋል፡፡
ከሶሪያ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱት ወይዘሮ ፋጡማ ጃእፋር በበኩላቸው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተመጸወቱ ህይወታቸውን ለማኖር እየተጣጣሩ መሆናቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከሳምንት በፊት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ከገቡበት እለት ጀምሮ ሰላምና ፍጹም እረፍት እንደሚሰማቸው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያዊያን እጅግ ገር እና ሰው ለመርዳት ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸውንም ተናግረው ነበር፡፡
የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ጁነዲን ረሺድ፤ ከየመን እና ሶሪያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች የሀገሪቱ የጸጥታ ስጋት እንዳይሆኑ ወደ ሀገር ሲገቡ ተገቢው የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት ያለውን ጦርነት ሸሽተው ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ፤ በምን መልኩ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ተገቢው ማጣራት ከተደረገ በኋላ ነው የስደተኝነት እውቅና የሚሰጠው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚገኙ የሁለቱ ሀገራት ስደተኞች የከተማ ስደተኝነት እውቅና ከመሰጠቱ በፊት የስደተኞቹ የኋላ ታሪክ፤ ከየት እንደመጡና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮችን ቃለመጠይቅ ከተደረገ በኋላ የስደተኝነት እውቅና የተሰጣቸው መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ጁነዲን፤ ለእነዚህ እውቅና ለተሰጣቸው ስደተኞች አስፈላጊ ነገሮችም እንዲሟሉላቸው እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና ከሌሎች ሰብዓዊ እና ማህበራዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ተገቢውን ሰብዓዊ እና ማህበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ጁነዲን ማብራሪያ፤ በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድንጋጌዎች መሰረት በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የሚመደብ ዓመታዊ በጀት አለ፡፡ ኢትዮጵያም ድንጋጌዎቹን ተቀብለው ካጸደቁት ሀገራት አንዷ እንደ መሆኗ ስደተኞቹን ተቀብላ በተመደበው በጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታ አለባት፡፡
አቶ ጁነዲን እንደሚያብራሩት፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ መልካም ስም ያላት በመሆኗ የየመንና ሶሪያ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መሰደድን እየመረጡ ነው፡፡ ስደተኞቹን በተመለከተ መፍትሄ ተብሎ ከሚታሰቡ አማራጮች አንዱ እነርሱን የመቀበል ፍላጎት እና አቅም ወዳላቸው ሀገራት ማስተላለፍ ነው፡፡ ካደጉት ሀገራት ጋር በሚደረጉ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሚገኙ የየመንና የሶሪያ ስደተኞችን የመቀበል ፍላጎት ወዳላቸው የማስተላለፍ ሥራም እየተከናወነ ነው፡፡
የኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ የኮሙዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ የማነ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ ወደ ኢትዮጵያ በተለያየ አይነት ቪዛ የሚገቡ የውጭ ሀገራት ዜጎች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ መምሪያው በህግ ከተሰጠው ስልጣን አንዱ የውጭ ሀገራትን ዜጎች መመዝገብና መቆጣጠር እንደሚገኝበት በመጥቀስ፤ በተለይ በቱሪስት ቪዛ የሚገቡ የት ሆቴል እንደሚያርፉ አሳውቀው መቆየት እንዳለባቸው ነው የሚያነሱት፡፡ እነዚህ ጉብኝታቸውን ከማካሄድ ባለፈ በተለያየ የሥራ መስክ እንዲሰማሩ እንደማይፈቀድላቸው ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ የማነ ማብራሪያ፤ የውጭ አገራት ዜጎችን በተመለከተ በህግ የተቀመጠ ነገር ቢኖርም የተለያዩ አገራት ዜጎች በቱሪስት ቪዛ መጥተው በተለያየ የሥራ መስክ የሚሰማሩ ከመኖራቸውም በላይ፤ ቪዛቸውም ሳይታደስ በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱም አሉ፡፡ የተለያየ ሥራም የሚሠሩ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ የውጭ አገር ዜጎች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የሥራ መስኮች መሰማራት ባይችሉም፤ በተለያዩ አካባቢዎች ይህን ጥሰው ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ላይ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን፤ ወደ ፊትም እየተጣራ ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 4 /2011
መላኩ ኤሮሴ