ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ከያዙት ሀገሮች አንዷ ብትሆንም፣ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም በተለይ ወደ ውጪ በመላክ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ከእቅዷም ሆነ ካላት አቅም ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው።
የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድ፣እንስሳቱ ወደ ውጪ ከመላካቸው በፊት የህክምናና የመሳሳሉት ክትትል የሚደረግባቸው ኳርቲኖች አለመኖር እና የመሳሰሉት ለአፈጻጸሙ እና ገቢው ዝቅተኛነት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ከፍተኛ መጠን ያለው የቁም ከብት ተልኮ እየተገኘ ያለው አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢም ሌላው ተግዳሮት ተደርጎ ይወሰዳል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤በ2011 በጀት ዓመት ባለፉት አስር ወራት የቁም እንስሳት፣ ሥጋ እና የሥጋ ተረፈ ምርት ወደ ውጪ በመላክ ከ113 ነጥብ 8ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የቁም እንስሳት፣ ሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርት ወደ ውጪ በመላክ ከተገኘው 113ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 36ነጥብ89 ሚሊዮን ዶላር የተገኘው 404ሺ788 የቁም ከብቶች ወደ ውጪ በመላክ ነው። ወደ ውጪ ከተላከ 14 ነጥብ 61 ሚሊዮን ቶን ሥጋ 74ነጥብ 34 ሚሊዮን ዶላር ፣ከ1 ነጥብ 44 ሚሊዮን ቶን ሥጋ ተረፈ ምርቶች ደግሞ 2ሚሊዮን 613ሺ150 ዶላር ተገኝቷል።
ወደ ውጪ የተላከው የቁም ከብት ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አስር ወራት ጋር ሲነፃፀር በ28ነጥብ71 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ ወደ ውጪ የተላከ ሥጋም በገቢ 6ነጥብ 27 በመቶ እና በእቅድ ከተያዘው አንጻር ደግሞ በ35ነጥብ67 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
በቁም ከብት ብቻ የተገኘው ገቢ 36ነጥብ 89ሚሊዮን ዶላር መሆኑንና ይህም የገቢ ዕቅዱን 30 ነጥብ47 ከመቶ ነው። አፈጻጸሙም ከ2010 ተመሳሳይ አስር ወራት ጋር ሲነፃፀር በተላከ መጠን 35 ነጥብ 67 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣በገቢ ግን 28ነጥብ 71 በመቶ ቅናሽ የታየበት ሆኗል።
በውጪ ንግዱ ላይ ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ እንዲሁም የቁም እንስሳትን ግብይት ለማሳለጥ የወጡ መመሪያዎችን እና ደንቦችን በትክክል አለመተገበር በግብይት ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን አቶ ወንድሙ ጠቅሰው፣ ወደ ውጪ የሚላኩ የቁም እንስሳት የሚቆዩበት ዘመናዊ መጠለያ በየአካባቢው አለመኖርም ሌላው የዘርፉ ተግዳሮት መሆኑን አስረድተዋል ።
ላኪዎች የቁም እንስሳት ሽያጭ ገቢን ከመሸጫ ዋጋ በታች እያስመዘገቡ ያለበት ሁኔታም ሌላው ለገቢው ማነስ ምክንያት መሆኑን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በቁም እንስሳት ትራንስፖርት እና በጅቡቲ ወደብ አገልግሎት ላይ ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉም ነው መረጃው የጠቆመው።
ሀገሪቱ የቀንድ ከብቶች እንዲሁም በግና ፍየል ወደ ውጪ ስትልክ መቆየቷ ይታወቃል።አሁን እየላከች ያለችው የቀንድ ከብት ብቻ ሲሆን፣ፍየልና በግ መላክ ግን ካቆመች ስድስት ወራት መቆጠራቸውን ከኢትዮጵያ ስጋ እና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ትላልቅ ቄራዎች ማምረት መጀመራቸው ለበግ እና ፍየል ወደ ውጪ አለመላክ አንዱ ምክንያት መሆኑን የኢንስቲትዩቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስጋ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ቄራዎች መስፋፋት ለበግና ፍየል በአገር ውስጥ በቂ ገበያ በመደበኛነት እንዲኖር እያስቻለ መሆኑን አመልክቷል።
ሀገሪቱ በበግና ፍየል ምትክ አሁን ስጋ ለውጭ ገበያ በስፋት እያቀረበች ስትሆን፣ የሚላከው ስጋ መጠን በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ተጠቁሟል። የሚለከው መጠን ቢጨምርም ገቢው ግን እየቀነሰ መሆኑም ተጠቁሟል። ለእዚህ ምክንያቱ ገቢው ከመሸጫ ዋጋ በታች እየተደረገ መመዝገቡ /አንደር ኢንቮይስ/ ላይ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ህዝብ ግንኙነት አቶ ደበሌ ለማ ይገልጻሉ። ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም ምክንያት እንደሌለም ይጠቁማሉ።
ቄራዎቹ ሲቸገሩ የቆዩት በፍየልና በግ አንዳንዴም በሬ እጥረት እንደነበር አቶ ደበሌ አስታውሰው፣ የቁም እንስሳት በተለይም የበግና የፍየል የውጪ ንግድ መከልከሉ ለቄራዎች የሚቀርበው የቁም እንስሳት ብዛት እንደጨምርና በዚህም የቄራዎቹ የግብአት ችግር እንደፈታ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይናገራሉ።‹‹በቁም እንስሳት እጥረት የማምረት ስራው የማይስተጓጎል ቄራ የትኛውንም ትዕዛዝ እንደሚቀበልም ይገልጻሉ።ይህ ማለት የኤክስፖርት መጠኑ በብዛትም በገቢም ይጨምራል፤ የስጋ የወጪ ንግድ አደገ ማለትም ነው ይላሉ።ይህም ለቄራውም፣ ለሀገሪቷም እንዲሁም ለአርሶ አደሩም አስተዋጽኦ እንዳለው ያብራራሉ ።
አቶ ደበሌ የቁም በግና የፍየል ኤክስፖርት ተከልክሎ የበግና የፍየል ስጋ ኤክስፖርት ቢፈቀድም ከስጋ እና ስጋ ተረፈ ምርት የወጪ ንግድ እየተገኘ ያለው ገቢ አሁንም ሰፊ ልዩነት እንዳላመጣም ይጠቁማሉ ።
በሀገሪቱ የታየው የፀጥታ ችግር በስጋ የወጪ ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን ይጠቅሳሉ።በተለይ ፍየሎች ብዛት ከቆላማው የኦሮሚያ እና ከሶማሌ ክልሎች እንደሚገኙ ተናግረው፣ ቄራዎች የደጋ ፍየሎች ስጋ ወደ ውጪ መላክ እንደማይፈልጉም ተናግረው፣ ስጋው ጥቁር የሚሆንበት ሁኔታ እንዳለ ይጠቅሳሉ።
ገበያችን ዱባይና ሳዑዲ ስለሆነ የስጋው ቀለም ትንሽ ከተቀየረ አይፈለግም፤ያጣጥሉታል የሚሉት አቶ ደበሌ፣በአብዛኛው ስጋ የሚላከው ከባሌ፣ቦረ፣ ጉጂ ሐረርና ሶማሌ ክልል አካባቢ የሚመጡ ፍየሎችን ለቄራዎች በማቅረብ መሆኑን ያብራራሉ ።
ከተጠቀሱት አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ በቂ የፍየል አቅርቦት እንዳልነበር ተናግረው፣ በዚህ የተነሳም ነጋዴዎቹም ባለቄራዎቹም መቸገራቸውን ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ደበሌ ገለጻ፤በጸጥታ ችግር ሳቢያ አርሶ አደሩም እንስሳቱን ወደ ገበያ ለማውጣት ይቸገራል። ይህ ችግር ሙሉ ለሙሉ ከተቀረፈ የወጪ ንግዱ በእጥፍ ሊጨምር ይችላል።
በግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የገበያ ጥናት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ጌትነት በላይ እንደሚሉት፤የቁም እንስሳት ወደ ውጪ የሚላክበት ሁኔታ እየቀነሰ የሚመጣ ሲሆን በተለይ በግና ፍየል በቁም ከመላክ ስጋ ወደ መላክ ተገብቷል።
የቁም እንስሳት የወጪ ንግዱ ትልቁ ችግር ያለው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በጥራት፣ በመጠን፣ በጊዜ ተቀናጅቶ የማልማቱ ሥራ ውስንነት እንዳለበት ይናገራሉ።
‹‹ሁለተኛው በቁም እንስሳት ብዛት እንደ ሀገር ቀዳሚነቱ ቢኖረንም፣ ግብይቱን ሕግን ተከትሎ ከመፈፀም አኳያ ውሱንነቶች አሉ።››ሲሉም ይገልጻሉ። ሕጋዊ በሆነ መልኩ ግብይቶችን ከማድረግ ይልቅ ሕገወጥ ግብይት የሚፈጸምባቸው ገበያዎች እየተስፋፉ እንደሚገኙም ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ጌትነት ገለጻ፤ በተለይ የሀገሪቱ መግቢያ መውጫ በር በሚባሉት እንድ ቶጎ ጫሌ፣ መተማ፣ ሁመራ በመሳሰሉት ሕገወጥ ግብይት እየተፈጸመ ይፈጸማል።ይህን ችግር ለመፍታት ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ አካላት ኃላፊነት ወስደው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ችግሩን አጉልቶ ከመናገር የበለጠ መፍትሔ ለመስጠት አልተንቀሳቀሱም፡፤
የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ባለስልጣን በሕገወጥ እንዲወጡ የሚደረጉ የቁም እንስሳትን የሚይዙ ቢሆንም፣ለተያዙት የቁም እንስሳት ማቆያ፣ ውሃ፣ ምግብ በማዘጋጀት በኩል ችግር ይስተዋላል። እንስሳቱን ለማቆየት ተዘጋጅተዋል የሚባሉ ቦታዎች የሉም፤እነዚህ ችግሮች የቁም እንስሳት የወጪ ንግዱ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ።
አቶ ጌትነት በግና ፍየልን በቁም ከመላክ በስጋ እርድ መላክ እንደሚያዋጣ ጠቅሰው፣እንስሳቱን በቁም ከመላክ ይልቅ በስጋ መልኩ ሲላኩ የበለጠ ዋጋ እንደሚያወጡ ይጠቁማሉ። አምራቾቹ የላኪዎቹን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ ሁኔታ በስጋ መልኩ ቢልኩ የተሻለ ገበያ እንደሚያገኙም ይገልጻሉ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሩ አቶ ወንድሙ ሕገወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለወጪ ንግድ መቀዛቀዝ እና ለውጪ ምንዛሪ ግኝት መቀነስ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፣ችግሩ ይህ ብቻ እንዳልሆነም ነው የሚጠቆሙት። ችግሩ ለሀገራዊ የገቢ አሰባሰብ ጭምር እንቅፋት እንደሆነም አመልክተው፣ ሕገወጥ ንግድንና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ተቀናጅቶ መግታት በሚቻልበት አግባብ ላይ የንቅናቄ ሰነድ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ምክክር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 2/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ