ዜና ሀተታ
አያልነሽ አሰፋ ትባላለች። የምትኖረው በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ሲሆን የሶስት ልጆች እናት ናት። በልጅነቷ ወድቃ በእግሮቿ ላይ ጉዳት በመድረሱ እንደልቧ መንቀሳቀስ የማትችል ስትሆን፤ በዚህም ልጆቿን ለማሳደግ እጅ እንዳጠራት ትገልጻለች። ወረዳው አካል ጉዳተኛ ዜጎች እገዛ እንዲያገኙ ለማድረግ ሰዎችን ሲመዘግብ በዚያ ምክንያት መመዝገቧን ገልጻለች።
በአጋጣሚ አካል ጉዳተኛ ወገኖችን የሚደግፍ ካይማ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ከአውስትራሊያ ኤምባሲ የሚደገፍ የዳፕ ፕሮጀክት እንዳለ እንደተነገራት አውግታናለች።
በዚህም ፋውንዴሽኑ ከአምስት ወር በፊት ዘመናዊ የዶሮ መኖርያ ቤት፣ 25 ዶሮዎችና ለ2 ወር የሚቆይ የዶሮ መኖ እንደተሰጣት ትናገራለች። በተደረገላት ድጋፍ ዶሮዎችን በማሳደግ ገቢ እያገኘች ነው። አሁን ላይ ችግሮቿ በከፊል እንደተቀረፈላት ጠቁማለች።
ለአካል ጉዳተኛ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ ከተቻለ መሥራትና እራሳቸውን መቀየር ይችላሉ የምትለው ወይዘሮ አያልነሽ፤ ለአካል ጉዳተኞች የሚደረጉ መሰል ድጋፎች ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ሊቀጥል ይገባል ብላለች። በዚህም ደስተኛ መሆኗን ገልጻ፤ ለተደረገላት ድጋፍም አመስግናለች።
ሌላኛው የድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ቸርነት ደምሴ ይባላሉ። የሚኖሩት በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በሚገኘው የጦር ጉዳተኞች ካምፕ ሲሆን በካምፑ ለበርካታ ዓመታት እንደቆዩ ይናገራሉ። በጦርነት ምክንያት እጃቸው ላይ ጉዳት በመድረሱ እንደፈለጉት መሥራት እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ካይማ ፋውዴሽን አካል ጉዳተኛ የሆኑ በዶሮ እርባታ መሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን እንደሚደግፍ ሲነገር ሰምተው በወረዳው አማካኝነት በካምፑ የሚኖሩ 10 ግለሰቦች በማህበር ተደራጅተው ሥራውን መጀመራቸውን ያስረዳሉ። በማህበሩ ውስጥ ያሉት የተለያየ የአካል ጉዳት ተጠቂዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ፋውንዴሽኑ 100 ዶሮዎችን፣ የዶሮ መኖ እንዲሁም የዶሮ እርባታ ሥልጠና ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልጸው፤ በዚህም የሥራ ተነሳሽነት እንዲጨምርና ከመቀመጥ በተገኘው እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ህብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኞች ያለው የአመለካከት ሁኔታ እንዲቀየር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
የካይማ ፋውዴሽን ካንትሪ ዳይሪክተር ታዲዮስ ሀብቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ካይማ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ኤምባሲ ስር ከሚገኝ የዳፕ ፕሮጀክት ጋር በትብብር እንደሚሠራ ገልጸው፤ በአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ኑሮ እንዲሻሻል የቤተሰብ የዶሮ እርባታ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል። የፕሮጀክቱ ዓላማ ለችግር ተጋላጭ ማህበረሰብ አባላትን የኑሮ እና የአመጋገብ ፍላጎት ለማሻሻል መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ያስጀመረውን የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ የዶሮ እርባታ ቴክኖሎጂ ፓኬጆችን በመጠቀም የንግድ የዶሮ ዝርያዎችን፣ ምግብን እና የጤና አስተዳደርን ማሳደግን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በፕሮጀክቱ ለ17 አባወራዎችና 10 ግለሰቦች በስሩ ላቀፈ አንድ ማህበር 90 ቀናት የሆናቸው 25 ዶሮዎች፣ ዘመናዊ የዶሮ ቤት እና ከ60 ቀናት የሚሆን መኖ እገዛ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ከወረዳው የተመረጡ በርካታ ሰዎች በማህበረሰብ የዶሮ እርባታ ክትባት ሠልጥነው ከካይማ ፋውንዴሽን የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። በተጨማሪም ፋውንዴሽኑ የሠለጠነ የማህበረሰብ አቀፍ ክትባቶች በልደታ ከተማ ለሚገኙ ከ700 በላይ ዶሮዎችን ክትባት መሰጠቱን አመላክተዋል።
እንደ ዶክተር ታዲዮስ ገለጻ፤ ድጋፍ የተደረጉት ዶሮዎች በሁሉም ቤተሰብ ውስጥ እንቁላል መጣል የጀመሩ ሲሆን የተሻለ ለውጥ አሳይቷል።
በቀጣይ ፕሮግራሙን አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት መታቀዱን ገልጸው ሥራውን በሚፈለገው መጠን ለማስኬድ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም