በመዲናዋ ሸማቹ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችሉ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል። በተለይም በከተማዋ የሚታየውን የዋጋ ንረት በእጅጉ ለመቀነስ እንደሚያስችልም ይገለጻል።
ለመሆኑ እነዚህ የገበያ ማዕከላት በአሁኑ ወቅት እየሰጡ ያለው አገልግሎት ምን ይመስላል፤ ገበያን ከማረጋጋት አንጻርስ ምን እየሠሩ ነው? ከማዕከላቱ መካከል አንዱ የሆነውን የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከል እንቅስቃሴ ቃኝተናል።
የለሚ ኩራ የግብርና ምርት የገበያ ማዕከል በርካታ ቁጥር ያላቸው አምራቾች፣ ነጋዴዎችና አቅራቢዎች በተዘጋጁላቸው መሸጫ ቦታዎች ላይ የሽንኩርት፣ ቲማንቲም፣ ጤፍ፣ ዱቄትና የመሳሰሉት ምርቶች እያቀረቡ እንደሚገኝ ተዘዋውረን ተመልክተናል።
ታዲያ የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከሉ አሁን ምን እየሠሩ ነው፤ ስንል አቅራቢዎችና ሸማቾችን አነጋግረናል። የቶኩማ አትክልትና ፍራፍሬ አቅራቢው አቶ ዋቅቶላ ሴንጦ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ በለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች ገበያ ማዕከል ላይ ከውጪ ገበያ 15 በመቶ ቅናሽ በማድረግ እያቀረቡ እንደሚገኝ ይናገራል።
በመቂ የእርሻ ማሳ የቲማንቲም፣ ፓፓያ፣ ሽንኩርት፣ ፎሶሊያና ቃሪያን በማምረት ወደ ገበያ እንደሚያቀርቡ የገለጸው አቶ ዋቅቶላ፣ በገበያ ማዕከሉ ከሚመጡት ሸማቾች በተጨማሪ በሱቅ ለሚሸጡ ነጋዴዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርቡ ይገልጻል።
በለሚ ኩራ የግብርና ምርት መሸጫ ገበያ ማዕከል የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ከውጪ ገበያው 15 በመቶ ቅናሽ በማድረግ እያቀረቡ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ድንች በኪሎ 25 ብር፣ ቲማንቲም 40 ብር፣ ሽንኩርት 95 ብር፣ አቡካዶ 25 ብር ድንች ስኳር 25 ብር ጥቅል ጎመን 20 ብር ፣ብርቱካን 100 ብር፣ አናናስ 40 ብር እያቀረቡ እንደሚገኝ ያስረዳል።
በገበያ ማዕከሉ ይስተዋሉ የነበሩ የመብራት፣ የውሃና የግብርዓት ችግሮች እየተቀረፉ እንደሚገኝም ይገልጻል።
በገበያ ማዕከሉ እየቀረቡ ያሉ ምርቶች በዋጋ ተመጣጣኝ በመሆናቸው ተጠቃሚ ሆነናል የሚሉት ደግሞ ከአያት አካባቢ የቤት አስቤዛ ለመሸመት የመጡት ወይዘሮ ሰብለ ተስፋዬ ናቸው። በተለይም ፍራፍሬዎች ፍሬሽና ጥራታቸው የጠበቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለጤናም ተስማሚ መሆናቸውን አንስተዋል።
የገበያው ማዕከሉ በአቅራቢያቸው መገንባቱና ምርት ማቅረቡ ጊዜያቸውንና ወጪያቸውን እንደቆጠበላቸው በመግለጽ፣ ጥራት ያለው ሽንኩርት በኪሎ 100 ብር፣ ድንች 25 ብር፣ ቲማንቲም 50 ብር መግዛታቸውን ይገልጻሉ።
የግብርና ውጤት እህል ምርቶችን ለሚያቀርበው አቶ ማረኝ ጀማነህ እንደሚናገረው፣ በገበያ ማዕከሉ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በቆሎ፣ ነጭ፣ ቀይና ሰርገኛ ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን እያቀረቡ እንደሚገኝ ይናገራል።
ነጭ ጤፍ በኩንታል 13 ሺህ 500 ብር፣ ቀይ ጤፍ 11 ሺህ 400 ብር፣ በቆሎ 3 ሺህ 600 ብር እያቀረቡ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ የገበያ ማዕከሉ የደላሎችን ሚና ያስቀረ በመሆኑ ውጪ ላይ ለገበያ ከሚቀርበው ዋጋ 15 በመቶ ቅናሽ በማድረግ እየሸጡ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።
የአካባቢው ህብረተሰብ በተለይም በበዓላት ወቅት በብዛት ምርቶችን እየሸመተ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ከአዲስ ዓመት በዓል በኋላ ግን መቀዛቀዝ ማሳየቱን ይገልጻል።
ለሸማቹ ምስር፣ ማካሮኒ፣ የሀገር ውስጥ ሩዝ፣ ዱቄት፣ የተለያዩ የጥራጥሬ ምርቶችን እያቀረቡ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ አተር ክክ በኪሎ 130 ብር ፣ሩዝ 115 ብር፣ የሽሮ እህል 115 ብር፣ ድፍን ምስር 158 ብር ማካሮኒ 110 ብር እያቀረቡ መሆናቸውን ያስረዳል።
በማዕከሉ የመብራት እየቀረበላቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ነገር ግን የውሃ ችግር አሁንም እንዳለባቸውም ይገልጻል። በገበያ ማዕከሉ ሽንኩርት፣ ቲማንቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ አቦካዶና የግብርና ምርቶችን እያቀረቡ እንደሚገኙ አቶ ኤርሚያስ አማረ ይገልጻል።
ከውጪው ገበያ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ምርቶችን ለገበያ ማቅረባቸውን በመግለጽ፣ ሽንኩርት 100 ብር፣ ጥቅል ጎመን 20 ብር እየሸጡ እንደሚገኝና የገበያው ሁኔታ የአካባቢው ሸማቾች እየለመዱ በመሆኑ መነቃቃት እንዳለው ያስረዳል።
በገበያ ማዕከሉ የውሃ ችግር በተወሰነ መልኩ እንዳለና መብራት አቅርቦት ግን መጀመሩን የገለጸው አቶ ኤርሚያስ፣የገበያው ሁኔታ ከዘመን መለወጫ በዓል በኋላ መቀዛቀዙንና ለመስቀል በዓል ግን ጥሩ ሁኔታዎች መኖራቸውን ይናገራል።
የገበያ ማዕከሉ መከፈት ያመረትነውን ምርት በቀጥታ ለገበያ እንድናቀርብ እንደረዳቸው ጠቅሰው፣ በርካታ ምርቶችን ወደ ገበያው ብናቀርብም ሸማቾች እየተጠቀሙበት አይደለምና ሸማቾች ወደ ገበያ ማዕከሉ በመምጣት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይገባል ሲል ይገልጻል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍስሃ ጥበቡ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ በገበያ ማዕከላቱ የሚስተዋሉ የመሠረተ ልማትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በገበያ ማዕከላቱ የሚስተዋለውን የመሠረተ ልማትና የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሠራሩ ሂደት በአንዳንድ የገበያ ማዕከላት የሚስተዋሉትን የመሠረተ ልማትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 ዓ.ም