“የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተከፈለ ዕዳ አለበት” – አቶ ሽፈራው ተሊላ ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ የመሠረተ ልማት በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በመኖሪያ እና በንግድ ቤታችን ውስጥ ለተለያዩ ተግባራት ጥቅም ላይ ይውላል። የኃይል ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ ባለበት በዚህ ጊዜም፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አገልግሎቱን አስተማማኝ እና ዘላቂ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት የኤሌክትሪክ ኃይልን የማመንጨት፣ የማስተላለፊያ እና የማሰራጨት ኃላፊነት አለባቸው፣ ይህም ተቋማቱን በሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የተቆራኙ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስፈላጊ ኃይልን ከመስጠት በተጨማሪ ዘላቂነት እና ፈጠራ ላይ ያተኩራሉ። እንደ ፀሐይ እና ንፋስ ያሉ የታዳሽ ኃይል ምንጮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በማዘመን የአካባቢን ተፅእኖ የሚቀንሱ ንፁህ ቴክኖሎጂዎችን ለማካተት ስልቶችን ይቀይሳሉ። የዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴያቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን፤ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የሥራ እድል በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገትን ይደግፉበታል።

በዚህ ተለዋዋጭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት የቁጥጥር ሥርዓት ለውጦች በማድረግ እና መሠረተ ልማት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ከቻሉ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተመጣጣኝ እና ዘላቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ይችላሉ። እኛም ይህንኑ ሃሳብ ይዘን ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመሄድ ስለ ተቋሙ የአስተዳደር ሥርዓቶች፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት፤ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች እና የኦዲት ሪፖርቶች የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ለተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ተሊላ አቅርበን፤ ባለፈው ሳምንት የክፍል አንድ ዝግጅታችንን ለንባብ ማብቃታችን የሚታወስ ነው። ዛሬ ደግሞ የመጨረሻውን ክፍል (ክፍል ሁለት) እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ!

አዲስ ዘመን፡- “ስማርት” ቆጣሪዎችን ከማሰራጨት አንጻር እንዴት እየተሰራ ነው?

አቶ ሽፈራው፡- የደንበኞችን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን ተቋማችን በስፋት እየሰራባቸው ከሚገኙት ጉዳዮች መካከል በቴክኖሎጂ የበለጸጉ “ስማርት” ቆጣሪዎችን ለማኅበረሰቡ ማሰራጨት አንደኛው ነው። ቴክኖሎጂው የደንበኛውንም ሆነ የተቋሙንም ስራ የሚያቃልል ሲሆን፤ ደንበኛውና ተቋሙ አስተማማኝ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያግዛል። ቀደም ብሎ የነበሩት ቆጣሪዎች የተቋማችን ሰራተኞች ሄደው ካነበቧቸው በኋላ ነው ወደ ሲስተም የሚገቡት።

በንባብ ላይ ደግሞ ስህተት ሊከሰት ይችላል። ይህም ያልተገባ ዋጋ ሊፈጠር ስለሚችል በደንበኛውና በተቋሙ ግኝኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። ይህን ለማስተካከል ነበር ቆጣሪዎቻችንን ወደ ስማርት ቆጣሪዎች ለመቀየር የሰራነው። አሁን ላይ ስማርት ቆጣሪዎችን የሚፈልጉ በርካታ ደንበኞች ስላሉ የበፊቶችን ቆጣሪዎች በአንድ ጊዜ መቀየር አይቻልም። ነገር ግን ሂደት የሚተገበር ይሆናል። ምክንያቱም ትልቅ ኢንቨስመንት የሚጠይቅ በመሆኑ።

ስማርት ቆጣሪዎችን ከመተካት አንጻር በመጀመሪያ ላይ ቁልፍ ደንበኞች ለሚባሉት እና ለሀገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ በሚያበረክቱ ደንበኞችን ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው። ወደ 40 ሺህ ለሚጠጉ የኢንዱስትሪ ደንበኞች እና ትልልቅ ተቋማት በስማርት ቆጣሪ እየተቀየርን ነው።

የኢንዱስትሪ ደንበኞች በቁጥር ትንሽ ቢሆኑም የፍጆታ መጠናቸው ግን ከፍተኛ ነው። ቀጥሎም ሶስተኛ ደረጃ (three phase) ደንበኞች የሚባሉ አሉ። የንግድ ተቋማትን ወደዚህ ይቀየራሉ። በ2017 ወደ 125 ሺህ ደንበኞች የስማርት ቆጣሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል። የቆጣሪዎች ግዥ ተከናውኖ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ነው፤ ገብቶ እንዳለቀ ስማርት ቆጣሪውን የመትከል ስራ ይከናወናል። በቀጣይም በሂደት ትንንሽ ደበንበኞችን የመቀየር ስራ እንሰራለን።

ስማርት ቆጣሪዎች በርካታ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፤ ከእነዚህ ጥቆሞች መካከልም በሁለቱ ወገኖች (በአገልግሎት ሰጭው እና በደንበኛው) መካከል የሚኖረውን ግኙነት ያሳልጣል። ይህ ማለት የደንበኛው ቆጣሪ ካለበት ስፍራ ወደ ማዕከል (አገልግሎት ሰጭው) ግንኙነት ማድረግ ያስችለዋል። በተመሳሳይ ከማዕከል ወደ ቆጣሪው መልዕክት መላክ የሚችልበት ሁኔታ አለ። ይህም በደንበኛው እና በአገልግሎት ሰጨው መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረክታል።

ሌላው ይህ ቆጣሪ የኃይል መቋረጥ ሲኖር መረጃ ይሰጣል። በኃይል ላይ ያለ የጥራት ችግር ካለ ያሳያል። በመተግበሪያው ምን ያህል ኃይል እየተጠቀመ እንደሆነ መከታተል ይቻላል። ፍጆታው እንዴት ነው የሚለውን ጉዳይ ማየት ይችላል። ወደ ፍጆታ ሂሳቡ ስንመጣም ለደንበኛው የሚሆን የሞባይል መተግበሪያ እያበለጸግን ነው። ይህም የደንበኞችንና የተቋሙን አሰራርና ተጠቃሚነት የሚያሳልጥ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ በሚሰሩ ለመተካት እየተሰራ ነው። ከዚህ አንጻር አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ፍጆታ መሸከም የሚያስችል የመሰረተ ልማት አለ ብለው ያምናሉ?

አቶ ሽፈራው፡- አሁን ላይ በሀገራችን አዳዲስ እና ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች፣ የንግድ ተቋማት እና ሕንጻዎች እየተገነቡ በመሆናቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እያደገ ነው። ለምሳሌ፣ ትናት በከተማችን ይታዩ የነበሩ ሕንጻዎች ትንሽ ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ነበሩ። አሁን ላይ በሜጋ ዋት የሚጠቀሙ ሆነዋል። በተጨማሪም በከተማችን በፊት የነበሩ ትንንሽ ቤቶች የነበሩበት ቦታ ላይ ትልቅ ሕጻንዎች እየተገነቡ ነው። እነኝህ ሕንጻዎች በውስጣቸው በርካታ ተቋማትን ይይዛሉ፤ ከፍተኛ የሆነ የኃይል አቅርቦትም ይፈልጋሉ።

የእነዚህን ሕንጻዎች የኃይል ፍላጎት ለማርካት እንደተቋም ብዙ ገንዘብ ኢንቨስት ማድረግን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት ዋና ፈተና ነው። ሆኖም መንግስት የመሰረተ ልማት አቅም ለማሳደግ በርካታ ቢሊዮን ብሮችን በመመደብ ከፍተኛ ስራዎችን እያከናወነ ነው።

ለእነዚህ ግዙፍ ተቋማት አገልግሎት ለመስጠት እንደ ሀገር በኃይል ማመንጨት በኩል በርካታ ስራዎችን እያከናወን ነው። በዚህ ዓመት የሕዳሴ ኃይል ወደ መስመር እየገባ ነው። በቀጣይም ሌሎች የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች (የእንፋሎት እና የነፋስ ) ማመንጫዎች ኃይል እየተገኘ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ የኃይል ፍላጎት ከ10፤ ከ20 ዓመት በኋላ የት ይደርሳል? ከዕድገቱ ጋር ተያይዞ ማስተናገድ የሚችል የመሰረተ ልማት አቅም ምን መሆን አለበት? የሚለውን ከግምት ውስጥ ያስገቡ እቅዶች እየተተገበሩ ነው ።

አዲስ ዘመን፡- በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ እየተገለጸ ነው። የተደረገው የዋጋ ጭማሪ እንዴት የሚገለጽ ነው?

አቶ ሽፈራው፡- ለምሳሌ፣ 27 ሳንቲም ሲከፍሉ የነበሩ ደንበኞች ከአራት ዓመት በኋላ አንድ ነጥብ አምስት ስድስት ሳንቲም ተጨማሪ የሚከፍሉ ይሆናል። አራት እጥፍ የሚባለው መነሻ ታሪፉ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ደንበኞቻችን ስለተደረገው ጭማሪ ፍትሃዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ሚዲያዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሊዘግቡ ይገባል።

እንደሚታወቀው የኃይል ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ ቁልፍ መሳሪያ ነው። ለኢንዱስሪ፣ ለከተሞች፣ ለተለያዩ ልማታዊ ስራዎች አስፈላጊ ነው። ለኤሌክትሪክ ኃይል ማምረቻ የሚሆነው የመሰረተ ልማቱ ግንባታ እንደማንኛውም “ኮሜዲቲ” ይመረታል፤ ከፍተኛ ገንዘብም ይወጣበታል። ለምሳሌ፣ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ለመስራት በመቶ ቢሊዮኖች ብር ወጭ ተደርጎበታል።

ይህ ኃይል ኢንዱስትሪዎች ጋር ሲደርስ ኢንዱስተሪዎች ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ ያደርጋል። ከቤታችን ሲገባ ሕይወትን ቀላል እንዲሆን ያስችላል። ነገር ግን ግድቦችን ለመስራት እና ኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት፣ ከፍተኛ ወጪ ይወጣል። ከግድቦች ጋር ተያይዘው ያሉት የኃይል ማመንጫ ጀኔሬተሮችና ተያያዥ ስራዎች፣ ኤሌክትሪክ ኃይል ከተመረተበት ደንበኛው ወዳለበት ትራንስፖርት ለማድረስ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል።

እነዚህን ስራዎች ለመስራት እንደማኛውም ኢንቨስትመንት ብሮችን ተበድረን ነው ያለማነው ። ምክንያቱም ከሀገራችን ኦኮኖሚ አንጻር በአንድ ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ማምጣት አይቻልም። በመሆኑም ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ከውስጥም ከውጭም የሚወሰዱ ብድሮች አሉ። እነዚህ ብድሮች ደግሞ መመለስ አለባቸው። ብድሩ የሚመለሰው ደግሞ የተመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል በአግባቡ እና በትክክለኛ ዋጋ ሲሸጥ ነው። ይህም ማለት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ዋጋ ተብሎ የሚጠራው ነው።

አሁን የተሰራው የኤሌከትሪክ ታሪፍ የዋጋ ማመላከቻ ታሪፍ (coast reflective tariff) ነው። ይህም ማለት ያወጣውን ወጪ የሚተካ ወይም የሚመልስ ማለት ነው። ከወጣው ወጪ ተቋማችን ላይ ተጨማሪ ትርፍ የለውም ማለት ነው። መንግስት ትርፍ አልፈልግም ብሎ ለኢኮኖሚው መስዋት አድርጓል።

አዲስ ዘመን፡- የታሪፍ ማሻሻያው ለመሰረተ ልማቶች የወጣውን ብር ሙሉ በሙሉ መመለስ ያስችላል?

አቶ ሽፈራው፡- አይችልም። አሁን ለጊዜው እኛ ታሪፉን ሰርተናል፤ በየጊዜው ለውጦች ይኖራሉ። የዛሬ ስድስት ዓመት ማለትም በ2010 ዓ.ም የኢነርጂ ታሪፍ ለማስተካከያ ተፈቅዶ ነበር። ማስተካከያ የተፈቀደው 1998 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓም ድረስ ምንም አይነት ማስተካከያ ባለመደረጉ ነው። በእነዚህ ዓመታት ተቋሙ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ተደራሽ ለማድረግ ለመሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ገንዘብ ኢንቨስት ሲያደርግ ነበር። መሰረተ ልማቶች ደግሞ ሲሰሩ የነበረው በብድር ነው።

ነገር ግን ምንም አይት የዋጋ ማስተካከያ ባለመደረጉ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወጭ የተደረገው ብድር ለረጅም ጊዜ ተጠራቅሟል። እንደመስሪያ ቤት ዋናው ፈተናው የተጠራቀመው ብድር ነው ። በተለይ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተከፈለ ዕዳ አለበት። በ2010 ዓ.ም በተደረገው ማስተካካያ ብቻ ከቀጠልን ያወጣነው ወጪ መመለስ አንችልም። ይህ ደግሞ ነገ ሌላ ኃይል ማመንጫ መገንባት እንዳንችል ያደርጋል፤ ነገ ሌላ የማሰራጫ መስመር አይኖረንም፤ ምንም አይነት ስራ ሊከፈት የሚችልበት እድል አይኖርም። ስለዚህ እንዲህ አይነት ኢኮኖሚያዊ ችግር እንይዳከሰት መንግስት የወሰነው የዋጋ ማመላከቻ ታሪፍ ትክክለኛ እና ወቅቱን ያገናዘበ ነው።

በነገራችን ላይ የእኛን ታሪፍ ከሌሎች ሀገራት ጋር ስናወዳድር በጣም ዝቅተኛ ነው። ጎረቤታችን ኬንያ በአንድ ኪሎ ዋት 17 ብር ታስከፍላለች። እኛ ግን የዋጋ ማመላከቻ ብለን ያወጣነው ስድስት ብር ነው። ይህ በጣም ዝቅተኛ ነው። ሌሎች ከእኛ ሀገር ሶስት ዕጥፍ ይበልጣሉ።

 

ይህም ምን ያህል ዜጎች እንዳይጎዱ፤ ነገር ግን ተቋማቱ ደግሞ እንዳይሞቱ እና ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የሚያመላከት ነው ።

አዲስ ዘመን፡- አሁን የተጨመረው የዋጋ ማመላከቻ ታሪፍ የኑሮ ውድነትን ያባብሳል የሚል ስጋት አለ፤ ከዚህ አንጻር ምን ታስቧል?

አቶ ሽፈራው፡- አሁን የተደረገው የዋጋ ማስተካከያ በኑሮ ውድነት ላይ ያለው ተፅዕኖ ምንድን ነው የሚለውን ነገር ከፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመሆን አይተናል። ያን ያህል የጎላ ተጽዕኖ የለውም። የኃይል ታሪፍ መጨመሩ በሌሎች እቃዎች ላይ የሚያመጣው የዋጋ ጭማሪ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የሚያመጣው ጫና ሁለት በመቶ ገደማ ነው። ይህም ከአራት ዓመት በኋላ ነው።

ይህ ታሪፍ በአንድ ጊዜ ሳይሆን ቀስ በቀስ የሚጨመር ነው። ለምሳሌ 27 ሳንቲም ሲከፍሉ የነበሩ ደንበኞች መስከረም ላይ 35 ሳንቲም እንዲከፍሉ ነው የሚደረገው። ስለዚህ ከአራት ዓመት በኋላ ሰዎች የመክፈል አቅማቸው እያደገ ይመጣል። የዋጋ ማመላከቻ ዋጋው ስድስት ብር ቢሆንም ከታችኛው የኢኮኖሚ እርከን ላይ ያሉ ዜጎች የሚከፍሉት ግን ከዚያ ያነሰ ነው። ለምሳሌ፣ እስከ 50 ኪሎ ዋት ፓወር የሚጠቀሙት የሚከፍሉት ስድስት ብር ቢሆንም ከአራት ዓመት በኋላ የሚኖረው ጭማሪ አንድ ነጥብ ስድስት ብር ነው።

እስከ 70 ኪሎ ዋት 75 በመቶ ድጎማ አላቸው። እስከ 100 ኪሎዋት ያሉት 40 በመቶ እስከ 200 መቶ ኪሎ ዋት ተጠቃሚዎችም እንዲሁ ድጎማ አላቸው። ከዚያ በላይ ግን ተጠቃሚነቱ ሲጨምር የመክፈል አቅም አለው ማለት ነው። ጭማሪው ቀስ በቀስ እንዲሆን የተደረገው በአንድ ጊዜ በኅብረተሰቡ ሕይወት የሚያመጣውን ጫና ለመቀነስ ታስቦ ነው። ስለዚህ አሁን የተደረገው ጭማሪ ተጨመረ ተብሎ ሕብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የሚከት አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- ሕዳሴ ግድብ ኃይል አመንጭቶ ወደ ስራ በሚገባበት ወቅት ይህን ያህል ጭማሪ ማድረግ ተገቢነት የለውም የሚሉ የሕብረተሰብ ክፍች አሉ። በዚህ ላይ የእርሶ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ሽፈራው፡- ጭማሪው ያን ያል ሕብረተሰቡን በሚጎዳ መንገድ የተደረገ ነገር እንዳልሆነ ገልጫለሁ። ወደ ሕዳሴ ስንመጣ ግድቡን ለመገንባት የወጣ ገንዘብ አለ። ከ180 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጥቶበታል። ስለዚህ ይህን የወጣው ገንዘብ ካልተካነው ለሕዳሴ ግድብ የተበደርነው ብር ካልተከፈለ ተቋሙ እንዴት መቆም ይችላል? የተገነባው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጭ ተደርጎበት ነው። ዜጎች ተሳትፈውበታል፤ በነጻ ገንዘባቸውን ለግሰዋል።

ይሁን እጂ አብዛኛው ገንዘብ ከሀገር ውስጥ ባንኮች በብድር የመጣ ነው። ለምሳሌ፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ አባላት ተባብረው አንድ ኩንታል ጤፍ ገዙ እንበልና እስከሚቀጥለው ወር መብላት ይችላሉ። ከሚቀጥለው ወር በኋላ ቤተሰቡ ሌላ ኩንታል ጤፍ መግዛት ካልቻለ መኖር አይችልም ማለት ነው። ስለዚህ ጤፉን ለመግዛት ሁሉም ጊዜውንና ጉልበቱን ሽጦ ብር ማምጣት መቻል አለባቸው። ይህም ልክ እንደዚህ ነው።

ዛሬ ሕዳሴን ገንብተናል፤ ነገ ደግሞ ሌላ መገንባት ካልቻልን ችግር ሊገጥመን ይችላል። ዋናው ተጠቃሚነቱ ላይ ነው። ሕዳሴን በዝቅተኛ ዋጋ ነው ተጠቃሚ እየሆን ያለው። ከኬንያ ብናመጣው ኖሮ ከኬንያ ለራሷ ዜጎች 17 ብር ከሸጠች ለእኛ በ17 አትሸጥም፤ ምንአልባትም 25 ብር ልትሸጥልን ትችል ነበር ። ሕዳሴ ነገም ጥገና ይፈልጋል፤ ለዚህ ደግሞ ገንዘብ መያዝ አስፈላጊ ነው። ሕዳሴ ባይመጣ ኖሮ በዚህ ዋጋ ኃይል ማግኘት አንችልም ነበር።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የሰራው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት እንዳመላከተው በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ ከስትራቴጂክ እቅድ አንጻር 39 በመቶ ነበር። ከዚህ አንጻር የቀጣይ እቅዱ ምን ደረጃ ለማድረስ ነው?

አቶ ሽፈራው፡- እቅዶች በምናቅድበት ጊዜ ታሳቢ ተደርጎ ሚታቀዱ ነገሮች ይኖራሉ። በእቅድ ታሳቢ የሚደረጉ ነገሮች ትክክል እና ተአማኒነት ባለው መንገድ ካላስቀመጥን እቅዱ ወረቀት ላይ ብቻ ይቀራል፤ ወይም ከአፈጻጸማችን በታች ይሆናል።

እንደ ተቋም አብዛኛው በተደራሽነት ላይ ያለው ፈተና የገንዘብ ውስንነት ነው። የውጭ ምንዛሬ እና የሀገር ውስጥ ገንዘብ በበቂ ሁኔታ ያለመኖር እቅዶቹ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው። አሁን ላይ በምናገኘው ገንዘብ ልክ እያቀድን ነው። ድሮ ግን አንድ ሺህ እና ሁለት ሺህ ከተሞችን እናገናኛለን በሚል ያለንን ያላማከለ እቅድ ይወጣ ነበር።

እንደ ሀገር ከተሞችን ተደራሽ ለማድረግ በፕሮግራም የተጀመረው 1998 ዓ.ም ነው። በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ኤሌክትሪክ የነበራቸው 690 ከተሞች ብቻ ነበሩ። በዚህ ፕሮግራም አዳዲስ ከተሞች እና መንደሮች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። አሁን ላይ 8 ሺህ 200 ከተሞች እና መንደሮች ኤሌክትሪክ እያገኙ ነው።

በ50 ዓመታት ውስጥ ተቋሙ ያልሰራውን ሁለት አስርት ዓመታት ባላሞላ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት አንዳንድ ጊዜ የበጀት እና መሰል የአቅም ውስንነቶች ፈተና ናቸው ። ይህንና አሁን ላይ ከማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርሙ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በዙ የተሻሻሉ ነገሮች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- በዋና ኦዲተር ባለስልጣን እንደተረጋገገጠው ተቋሙ የዓመቱ የፊዚካል የስራ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሆኖ ሳለ የሚጠየቀው በጀት ግን ከተቀመጠው በላይ ነው። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

አቶ ሽፈራው፡- አዎ! አንዳንድ ጊዜ ቀጣይነት ያላቸው ፕሮጀክቶች ይኖራሉ። በዚህ ወቅት ፊዚካል እቅድ እና ፋይናንሻል እቅድ በትክክል ላይመጣጠኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ሰኔ እና ግንቦት ላይ ስናከናውናቸው የነበሩት የፕሮጀክት ክፍያዎች በዚህ በጀት ዓመት ላይጠናቀቁ ይችላሉ። አጋጣሚ ሆኖ ኦዲተሮች ደግሞ በዚህ በጀት ዓመት ኦዲት ሊያርጉ ይችላሉ። በዚህ ወቅት የፊዚካል የስራ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሆኖ የተጠቀምነው በጀት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የተዛባ ግንዛቤ (misperceive) እንዳይደረግ እና ገንዘብ እያባከኑ ነው ወደ ሚለው ትርጓሜ እንዳይመጣ ፕሮጀክቶች ሁል ጊዜ በገንዘብ የተወሰኑ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። የፊዚካል አጠቃላይ ስራቸው በዚህን ያህል በጀት ነው የሚጠናቀቁት ከተባለ ያ አይቀየርም። ምን አልባት የዋጋ ማስተካከያ ከሌለ በስተቀር አይቀየርም፤ የሚባክን ገንዘብም አይኖርም። ስለዚህ የተለየ ነገር ካልሆነ በስተቀር ኮንትራክተሩ በያዘው ዕቅድ ስለሚሄድ ብዙ ችግሮች አይኖሩም።

አዲስ ዘመን፡- ከፍተኛ ወጭ የወጣባቸው ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተሰርተው እያለ ተቋሟችሁ መስራት ያለበትን ባለመስራቱ የገጠር አካባቢዎች መብራት እያገኙ አይደለም። ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ሽፈራው፡- ይህ የሆነበት ምክንያት የማስተላለፊያ መስመሮች እና የማሰራጫ ጣቢያ ሁለት ፕሮጀክቶች የሚሰሩት በተለያዩ ኮንትራክተሮች በመሆኑ ነው። ማስተላለፊያዎችን እና ማሰራጫዎችን የሚሰራው ኮንትራክተር አንድ ካልሆነ እና ሁለቱ ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ ካላለቁ/ካልተጠናቀቁ ወይንም አንደኛው ፕሮጀክት የሚዘገይ ከሆነ የጠቀሳችሁትን አይነት ችግር ሊከሰት ይችላል። ስለሆነም እስከሚጠናቀቅ ሊጠብቁ ይችላሉ ማለት ነው። ይህም ማቀናጀትን ይጠይቃል። ለማቀናጀት የሚከብደው ደግሞ አንዱ ጥሩ ሲሰራ ሌላኛው ኮንትራክተር ላይሰራ ይችላል።

አዲስ ዘመን ፡- በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስራ ላይ የሚገኙ የተቋማችሁ ሰራተኞች ምን አይነት የደህንነት ዋስትና ጥበቃ ታዳርጋላችሁ? አደጋ በደረሰ ጊዜ የሕይወት ኢንሹራንስ አላችሁ?

አቶ ሽፈራው ፡- እንግዲህ ሁሉም ሰው ወደስራ ሲወጣ የሚተማመነው የሀገሪቷን ፀጥታ ኃይል ነው። እኛም አሁን ከቤታችን ወጥተን ቢሮ ስንመጣ ሀገሪቷ ያለው የፀጥታ አካል ይጠብቀናል በሚል እሳቤ ነው። ነገር ግን እዚህ አዲስ አበባ ራሱ አንዳንድ ጊዜ ከዛ ውጪ የሆኑ ገጠመኞች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። በተመሳሳይ በተቋማችን ሰራተኞች ላይ እንደዚህ አይነት ነገሮች ያጋጥማሉ።

ግን በጣም ውስን ችግር ነው። ችግሮች ሲያጋጥሙ ተቋሙ ለሰራተኞቹ ኢንሹራሽ አለው። ከተጎዱ የሚያሳክምበትም አሰራር አለው። በአካል ጉዳት ከደረሰም ለዚያ ኢንሹራንስ የሚከፈልበት አሰራር አለ። በሕይወትም ደግሞ የሚከሰት አደጋ ካለ በተመሳሳይ ኢንሹራንስ አለው።

በጸጥታ ችግር የመሰረተ ልማቶች ጉዳት ከደረሰባቸው ኃይል የተቋረጡባቸውን አካባቢዎች ለመጠገን የሰራተኞች ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያስችል የጸጥታ መዋቅር በቦታው ሲኖር ጥገናው ይከናወናል። ለምሳሌ መከላከያ አከባቢዎችን ከተቆጣጠረ እና ለስራው የጸጥታ ሁኔታውን ዝግጁ ካደረገ በኋላ ከስር ከስር ተከታትለን ገብተን እንጠግናለን።

አዲስ ዘመን ፡- የደንበኞችን ወረፋ ለማስቀረት በካርድ የሚሰሩ ማሽኖችን ከመጠቀም አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው ?

አቶ ሽፈራው፡- አሁን ላይ ለደንበኞች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረግን ነው። አገልግሎት ፈልገው ወረፋ የሚጠብቁ ደንበኞችን ችግር ለመፍታት ‹‹ቤንዲንግ›› ማሽን አዘጋጅተናል፤ ፖስ ማሽንም አምጥተናል። በዚህም አገልግሎት እያገኙ ነው። ከዚህ ባሻገር አገልግሎት የምንሰጥበትንም ጊዜ ጨምረናል።

አዲስ ዘመን ፡- በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የፈጠረውን ጫና እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ሽፈራው፡- መሰረት ልማት ላይ ከባድ ጫና ይፈጥራል። የሰላም መደፍረሱ በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ በተመሳሳይ በእኛም ላይ ተጽዕኖ ያመጣል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊት ብዙዎችን አካባቢዎች አረጋግቷል። በምዕራብ ኢትዮጵያ አገልግሎት ተቋርጦባቸው የነበሩ አካባቢዎች አሁን ላይ ወደ አገልግሎት እየተመለሱ ነው። ወደ 360 የሚሆኑ መንደሮች ኤሌክትሪክ ተቋርጦባቸው ነበር።

መከላከያና ሕብረተሰቡ እየረዳን እኛም ሰራተኞችን ልከን ዜጎች ወደ ነበሩበት ሰላማዊ የኑሮ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያደረግን ነው። በዚህም ከ300 በላይ ለሚሆኑት አገልግሎቱን መልሰናል። የተወሰኑ ይቀሩናል፤ በሚቀጥለው ወር እንጨርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

አዲስ ዘመን ፡- ስርቆትን ለመከላከል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ ከመስራት አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው?

አቶ ሽፈራው፡- ስርቆትን ለመከላከል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ እየሰራን ነው። የእኛ መሰረተ ልማት ያለው በየሰው ደጅ ነው። ስለሆነም ዋናውና ትልቁ ኃላፊነት የሕብረተሰቡ ነው። ሀብቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አይደለም፤ የመንግስትም አይደለም! የሕዝብ ነው። ይህን ሀብት ሕብረተሰቡ ሀብቴ ነው ብሎ መጠበቅ አለበት። ስለዚህ ሕብረተሰቡ እና በየአካባቢው የሚገኙ አስተዳደር አካላት ይሄንን መሰረተ ልማት እንዲጠብቁ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሕብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት በመጠበቅ ሌቦችን እጅ ከፍንጅ ይዞ ለጸታ ኃይል አስረክቧል። በጥቆማ ተይዞ በፍትህ አካላት እርምጃ የተወሰደባቸው አሉ። ይህንን ማድረግ የሁላችንም ነው። የሚዲያው ድርሻም ግንዛቤ ከመፍጠር አንፃር ስራዎችን መስራት አለበት።

እዚህ ሰፈር ያለው ሕዝብ ኤሌክትሪክ ባያገኝም እንኳን የኤሌክትሪክ መስመሩ በሰፈሩ ካለፈ ነገ ተጠቃሚ እንደሚሆን ሊገነዘብ ይገባል። ለዚህ ያን መሰረተ ልማት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት። ነገር ግን መሰረተ ልማቱ ከፈረሰና ከተሰረቀ አገልግሎት የማግኘት እድሉ እየራቀ ይሄዳል፤ እያገኙ ያሉትም ይቋረጥባቸዋል። ስለዚህ ይህ እንዳይሆን የጋራ ንብረታችንን በጋራ መጠበቅ አለብን።

አዲስ ዘመን፡- ለሀገር ውስጥ ተቋራጮች የሚሰጠው ውል አቅማቸውን ያላገናዘበ እና የሚደረገው ቁጥጥርም ልል መሆኑ በዋና ኦዲተር ከቀረበው ሪፖርት ማየት ተችሏልና በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

አቶ ሽፈራው፡- ልክ ነው፤ የአቅም ውስንነት ሊኖር ይችላል። እኛ በኢትዮጵያ ውስጥ እየሰራን ያለነው አንዱ ስራ ሕብረተሰቡ ቀጥታ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ነው። ሌላው ደግሞ ዜጎች በዚህ ዙሪያ ላይ የስራ እድል እንዲያገኙ ነው። ቀደም ሲል በውጭ ኮንትራክተሮች ሲሰሩ የነበሩት ስራዎች ቀስ በቀስ በሀገር ውስጥ እንዲሰሩ እየተደረገ ነው። ያንንም ስልጠና በመስጠት ጭምር፤ አቅም እንዲፈጥሩ በማገዝ የተሰራ ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ ግን መውደቅ እና መነሳት ሊኖር ስለሚችል እየተከታተሉ እያረሙ መስመር ውስጥ እያስገቡ መሄድ ተገቢ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምትፈልገው ደረጃ የማያድጉ እና የማይለወጡ አሉ። እነሱን ደግሞ በማስተካከል አቅም መፍጠር እንዲችል ማገዝ፤ በሚገባቸው ጊዜ አቅም መፍጠር ካልቻለ ደግሞ ማስወጣት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በዋናነት ለፕሮጀክቶቻችሁ የጨረታ መስፈርታችሁ ምንድን ነው?

አቶ ሽራው፡- የጨረታ መስፈርታችን ጥራት ነው። እንደ ውጭ ኮንትራክተሮች በጣም የተጋነነ አይነት የጥራት መስፈርት ብናወጣ አያሟሉም። የስራ ጥራትንም ጉዳይ ደግሞ አገልግሎቱ ላይ ተፅዕኖ ስለሚያመጣ በመሆኑ የምንታገሰው አይደለም። ይህን ከግምት በማስገባት ተጫራቾች በትንሹ ሊኖራቸው የሚችለው የቴክኒካል እና የፋይናንስ አቅም ምንድን ነው? የሚለው አስቀምጠን በዚያ እንገመግማለን ።

ከዚህ አንጻር አንዳንዶች ከመስፈርቱ ጋር አቻ በሆነ መልኩ ሚጣጣም አቅማቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ገንዘብ ይገኝበታል በሚል በግርግር ወደ ጨረታ የሚመጡ አሉ። እነሱ በሂደት ከውስጡ እየጠሩ ይሄዳሉ።

አዲስ ዘመን፡- ዋና ኦዲተር ካስቀመጠው የአይቲ እና የፋይናንሻል ኦዲት በመነሳት ስትራቴጅክ እቅዶችን ከመተግበር አኳያ ምን እያደረጋችሁ ነው? አሰራራችሁን ለማዘመን እንዲረዳ የአይሲቲ ኦዲት አሰርታችሁ ታውቃላችሁ?

አቶ ሽፈራው፡- እንደተቋም የአይሲቲ ኦዲት እናደርጋለን። እንደማንኛም ‹‹ፐርፎርማንስ›› ኦዲት የአይሲቲ ኦዲት እናደርጋለን። ራሳችንም እንዴት ነው አይሲቲን እየተጠቀምን ያለነው? የሚለውን በባለሙያዎች የዳሰሳ ጥናት እያየን ነው። በዚያ ላይ ተመስርተን ተጨማሪ ማሟላት እና ማጠናከር ያለብን አካባቢዎችን በመለየት በእሱ ላይ እንሰራለን። የአይሲቲ አጠቃቀማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው። በ2012 ዓ.ም የገቢያችን አሰራር ወደ አይሲቲ ለውጠናል። አቅሙ ቀስ በቀስ እያደገ ነው።

ነገር ግን አሁንም በተፈለገበት ደረጃ ላይ አይደለም። የውስጥ አቅምን እንዴት እናሳድጋለን የሚለውን ከሚያለሙ አካላት ጋር እየተነጋርን ነው። እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ተቋማትን ተሞክሮ አይተናል። በቀጣይም ከተሞክሮዎች በመነሳት ማስተካከያዎችን ተግባራዊ እናደርጋለን።

አዲስ ዘመን፡- የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ሊጠናቀቅ ነው፤ ይሄም የሀገሪቱን ሕዝቦች የኃይል ፍላጎት ለማዳረስ የሚያስችል ይሆናል፤ ታዲያ የመሰረተ ልማቱ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ሽፈራው፡- መሰረተ ልማት ለኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው። ስለሆነም ሕዳሴ ላይ ያለውን ኃይል ማጓጓዝ ከዚያ ደግሞ ደንበኛውና ኢኮኖሚው ጋር በማድረስ መስራት ያለባቸው ስራዎች ናቸው። ይህም በቀጣይት የኢኮኖሚ እድገቱን ተከትሎ የሚሰራ ነው። ለዚያም የሚያስፈልጉ ኢንቨስትመንት ስራዎችን ማከናወን ይጠይቃል። ለዚህ መሰረተ ልማት ግባታም 545 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከዓለም ባንክ የተገኘ ብድር አለ።

አሁን ያለውን የኃይል ፍላጎት የሚያሟላ መሰረተ ልማት እየተገነባ ነው። ነገር ግን ፍላጎት የሚቆም ሳይሆን የሚቀጥል በመሆኑ የማስፋፋት ስራዎችን እንቀጥላለን። ስለዚህ ሕዳሴም አሁን ሲገነባ እንጠቀምበታለን ተብሎ የሚሰራ ነው። ስለዚህ በማክሮ ኢኮኖሚ የሚፈቱ ብዙ ማነቆዎች አሉ። የውጭ ምንዛሬ ላይ ያለው እጥረት ይህ እቅድ ይፈታዋል።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

አቶ ሽፈራው ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን ረቡዕ መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You