የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘመናዊ የመሠረተ ልማት በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በመኖሪያ እና በንግድ ቤታችን ውስጥ ለተለያዩ ተግባራት ጥቅም ላይ ይውላል። የኃይል ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ ባለበት በዚህ ዘመን የኤሌክትሪክ አቅርቦት አገልግሎቱን አስተማማኝ እና ዘላቂ ማድረግ አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት የኤሌክትሪክ ኃይልን የማመንጨት፣ የማስተላለፊያ እና የማሰራጨት ኃላፊነት አለባቸው፣ ይህም ተቋማቱን በሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ የተቆራኙ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስፈላጊ ኃይልን ከመስጠት በተጨማሪ ዘላቂነት እና ፈጠራ ላይ ያተኩራሉ። እንደ ፀሐይ እና ንፋስ ያሉ የታዳሽ ኃይል ምንጮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በማዘመን የአካባቢን ተፅእኖ የሚቀንሱ ንፁህ ቴክኖሎጂዎችን ለማካተት ስልቶችን ይቀይሳሉ። የዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴያቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የሥራ እድል በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገትን ይደግፉበታል።
በዚህ ተለዋዋጭ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት የቁጥጥር ሥርዓት ለውጦች በማድረግ እና መሠረተ ልማት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን መቅረፍ ከቻሉ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ተመጣጣኝ እና ዘላቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ይችላሉ።
እኛም ይህንኑ ሃሳብ ይዘን ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመሄድ ስለ ተቋሙ የአስተዳደር ሥርዓቶች፤ የአገልግሎት አሰጣጣጥ ሂደት፤ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች እና የኦዲት ሪፖርቶች የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ለተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ተሊላ አቅርበንላቸዋል። የሰጡንንም ምላሽ በሁለት ክፍል ይዘንላችሁ የምንቀርብ ይሆናል። የመጀመሪያውን ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፤ መልካም ቆይታ
አዲስ ዘመን፡- በ2016 በጀት ዓመት ምን ያህል ዜጎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል? አጠቃላይ የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ምን ያህልስ ደርሷል?
አቶ ሽፈራው፡– የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ እየሰራ ነው። ከአምስት ዓመቱ በመነሳት ደግሞ የሶስት ዓመት የስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቷል። 2016 በጀት ዓመት የሁለተኛውን ዓመት የስትራቴጂክ እቅድ ሲያከናውን ነበር። በዚህ ስትራቴጂክ እቅድ መሠረት አራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን እንገኛለን። የመጀመሪያው ከኃይል መቆራረጥ ጋር የተገናኙ ችግሮችን በመቅረፍ የደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስተማማኝ ለማድረግ መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት እና የማዘመን ሥራ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ደንበኛ ተኮር አገልግሎት መስጠት ነው። ሌላው እና ሶስተኛው ተቋሙ ጤናማ እና አስተማማኝ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖረው ማስቻል ሲሆን፤ አራተኛው ደግሞ ተቋማዊ አቅም (institutional capacity building) እና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ መፍጠር ነው።
አሁን ላይ እንደ ተቋም እነዚህን አራት የትኩረት መስኮችን በመያዝ እቅዶችን እያከናወንን እንገኛለን። ከደንበኛ ተኮር አገልግሎት አንጻር ብዙ ሥራዎችን እየሰራን ነው። አንደኛ የደንበኞችን ተጠቃሚነት ማብዛት ነው። በ2016 በጀት ዓመት 600 ሺ አዲስ ደንበኞችን ለማግኘት እቅድ ነበር። ነገር ግን ማግኘት የተቻለው 427ሺ ደንበኞችን ነው። ይህም የእቅዳችንን 71 በመቶ ነው። ይህ አፈጻጸም 71 በመቶ የሆነው እቅድ ስናቅድ እቅዱ በጣም የተለጠጠ (ambitious) ስለነበር ነው። እቅዱን መለጠጥ ያስፈለገበትም ዋና ምክንያትም የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ዝቅተኛ ስለሆነ ይሄንን በማሳደግ በርካታ ደንበኞችን የማግኘት እና እርካታን የመፍጠር ሥራዎችን ለመሥራት በማሰብ ነው። ከዚህ አንጻር በበጀት ዓመቱ በርካታ ሥራዎችን አከናውነናል።
ከተደራሽነት አንጻር እንደ ሀገር ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 54 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ይህ ቁጥር እንደ ሴክተር ያለ ቁጥር ነው። በዚህ ውስጥ ብዙ ባለድርሻ አካላት አሉ። የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተለይም ዋናውን የኤሌክትሪክ መረብ ወደ ደንበኞች ተደራሽ እንዲሆን የማስፋፋት ሥራ በዋናነት የሚሰሩ ቢሆንም ከዚያ በመለስ ሌሎች የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮች አሉ። ከግሪድ፣ ከሶላር ሚኒ ግሪድ ወጣ ያሉ እና ኃይል የማያገኙ የጤና እና የትምህርት ተቋማት ከሶስት እስከ አስር ኪሎዋት ድረስ ማመንጨት የሚችል የሶላር ኃይል ማመንጫ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው። በዚህም ጤና ተቋማት ላብራቶሪያቸውን የትምህርት ተቋማት ደግሞ ከድጋፍ ሰጪዎች በአግባቡ የሚሰራ ኃይል ማግኘት የሚችሉበት እድል የተመቻቸላቸው ነው።
የነፍስ ወከፍ አገልግሎትን በሚመለከት በጣም ተራርቀው የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከግሪድም ከሶላር ሚኒ ግሪድም ኃይል መስጠት አዋጭ ስለማይሆን ለእያንዳንዱ አባወራ የሚጠቀምበትን ‹‹የሶላር ሆም ሲስተም›› አሰራሮችን ዘርግተናል። በዚህም ተራራቀው የሚኖረውን የገጠሩ ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይህን ጨምሮ ያለው አጠቃላይ የኃይል አቅርቦት ድምር ውጤት ወደ 54በመቶ ማድረስ ተችሏል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2016 ዓ.ም አንድ መቶ ከተሞችን ኤሌክትሪክ ተደራሽ ለማድረግ አቅዶ 116 ከተሞችን ማዳረስ ችሏል። በጀት ወስኖን እንጂ ሕዝቡ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያቀርበው ጥያቄ እና ፍላጎት አሁንም በጣም ሰፊ ነው። አሁን ባለን አቅም ለሁሉም ሰው በአንድ ጊዜ በጀት መድቦ ማዳረስ አይቻልም። የመሠረተ ልማቱን ማስፋፋት ሥራ ረጅም ጊዜ እና ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ነው። ይሁንና ይህንን ሥራ በ2016 በጀት ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ስናከናውን ቆይተናል።
አዲስ ዘመን፡- የህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በ2017 በጀት ዓመት ምን ታስቧል?
አቶ ሽፈራው፡- 2017 ዓ.ም ሶስተኛው የስትራቴጂክ እቅድ ዓመት ነው። የትኩረት መስኮቹም ቀደም ብለን ከላይ የጠቀስናቸው ናቸው። ከዚህ በመነሳት በበጀት ዓመቱ የደንበኞችን ተጠቃሚነትን እና ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን አቅደናል። 600ሺ አዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ እና ተደራሽ ለማድረግ ከወዲሁ ሰፊ ዝግጅት አድርገን እየሰራን ነው። ከዋናው ‹‹ግሪድ›› እና ‹‹ከሶላር ሚኒ ግሪድ›› መረብ ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ አዳዲስ ከተሞች፣ መንደሮችን እና አካባቢዎችን እናገናኛለን ብለን አቅደናል። በተጨማሪም ከግሪድ እና ከሶላር ኤሌክትሪክ አቅርቦት ወደ 1400 የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ይህን ለመሥራት የሚያስችለውን ጥናት አጠናቀን ወደ ጨረታ ሂደት ውስጥ ገብተናል። 2017 በጀት ዓመት ላይ አንዱ የሚከናወነው ይሄ ነው። ሥራው በዓመቱ ሙሉ በሙሉ ላያልቅ ይችላል ግን ሰፊውን ሥራ እንሰራለን።
ጤና ጣቢያዎች እና ትምህርት ቤቶች ላይ የሚሰራው ሥራ ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር በተለይ ወጣቶች ትምህርት ቤት የተሟላ ትምህርት እንዲያገኙ፤ በጤና ጣቢያዎች ደግሞ እናቶች የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ቴክኖሎጂው በጣም ወሳኝነት አለው።
ሌላው በበጀት ዓመቱ ለመሥራት የታቀደው ደግሞ ከኃይል አስተማማኝነት እና አገልግሎቱን ለማሳደግ የሚረዱ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን አቅም ማሳደግ እና ማሻሻል ሥራዎች ይገኙበታል። ከዚህ አንጻር አሁን ላይ ስድስት ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አሉ። ይህንንም ሥራ እስከ 2017 በጀት ዓመት አጋማሽ ድረስ እናጠናቅቃለን።
ሌሎች የዞን 10 ከተሞችን እና ትልልቅ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸውን አካባቢዎችን መሠረተ ልማት እንደገና አቅም የማሳደግ ሥራ ይሰራል። ምክንያቱም ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሆነ እነዚህን አካባቢዎች የኢኮኖሚ እድገቱ የሚፈለገውን ፍላጎት ተመጣጣኝ የሆነ መሠረተ ልማት መገንባት ስላለብን እሱን እየሰራን ነው።
በመልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ (ሪሃቢቴሽን) አንጻር በ2017 በጀት ዓመት በ72 ከተሞች ላይ ጥናት በማድረግ የጨረታ ሰነድ ዝግጅት እና የኮንትራክተር መረጣ ሥራዎችን እንጀምራለን። ይህም በአጠቃላይ እንደ ሀገር ያለውን ኤሌክትሪክ አስተማማኝነት ችግርን የሚቀንስ ይሆናል።
በአዲስ አበባ ላይ ‹‹የስካዳር ሲስተም›› ተግባራዊ እናደርጋለን። እስካዳር ማለት ኦፕሬሽኑ ቀደም ሲል በማኑዋል የምንሰራውን ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከአንድ ማዕከል የምንቆጣጠርበትን ኦፕሬሽን የሚደግፍ ሥርዓት ነው። ይህን እናጠናክራለን የምናስቀጥለው ነው። በ2017 በጀት ዓመት አንዱ የትኩረት አቅጣጫችን ነው።
ሌላው ከደንበኛ አገልግሎት ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አንዱ ቁልፍ ችግራችን ብለን የለየነው ከደንበኞች አገልግሎት ጋር በተያያዘ የደንበኞች ቅሬታ መኖሩን ነው። ከዚህ አንጻር ባለፈው ዓመት የደንበኞችን የአገልግሎት እርካታ ለማወቅ በገለልተኛ አካል ጥናት አስጠንተን ነበር። በጥናቱ መሠረትም የደንበኞች እርካታ 62 በመቶ መሆኑን አረጋግጠናል። በተያዘው በጀት ዓመት ይሄንን ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ እንሰራለን። ለደንበኞች እርካታ ማነስ ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች በጥናት በመለየታችን በበጀት ዓመቱ ለማሳካት ያሰብነውን 80 መቶ የደንበኞች እርካታ ለማሳካት ሥራችንን አንድ እርምጃ ቀላል ያደርገዋል። የደንበኞችን እርካታ ከሚቀንሱ ምክንያች አንዱ ከአዲስ ኃይል ጋር የተገናኘ ነው።
ከዚህ አንጻር አዲስ ደንበኞች የኃይል አገልግሎት በጠየቁ ጊዜ የጠየቁት ጥያቄ በወቅቱ እና በአፋጣኝ ምላሽ እንደማያገኙ ይናገራሉ። በርግጥ ከዚህ ጋር ተያይዞ 2016 በጀት ላይ መሻሻሎች ነበሩ። በዚህም ወደ 50 በመቶ የሚሆኑ ደንበኞች በእስታንዳርዱ መሠረት አገልግሎት አግኝተዋል። ሌሎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ያላገኙ አሉ። ነገር ግን እኛ እንደ ተቋም አገልግሎት ደንበኞች ያላገኘባቸውን ምክንያት አሳማኝነት እንለካለን። አንድ ደንበኛ በ11 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የጠየቃቸውን አገልግሎቶች ማግኘት አለበት ብለን ያስቀመጥነው ስታንዳርድ አለ። ከዚህ አንጻር ቅሬታ ያነሱ ደንበኞች በስንት ቀን አገልግሎት አግኝተዋል? የሚለውን በየጊዜው እንገመግማለን። በአስቀመጥነው ስታንዳርድ መሠረት አገልግሎት ያገኙት ደንበኞች ከ54 በመቶ በላይ ይሆናሉ።
ይህ ማለት አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ የሚያሳይ ነው። ከግብአት፤ ከሠራተኞችም ጋር በተወሰነ ደረጃ የተገናኙ ውስንነቶች አሉ። እነዚህን ውስንነቶች ዘመናዊ አሰራርን በመፍጠር እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም በ2017 በጀት ዓመት እናሻሽለዋለን ብለን ከአሰብናቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።
ሁለተኛው ከደንበኞች አገልግሎት ጋር እንደ ችግር የተመለከትነው ከጥገና አገልግሎት ጋር በተገናኘ ነው። እሱንም በተመሳሳይ ሁኔታ ‹‹ኦቶሜት›› በማድረግ የክትትል ሥርዓቱን ጠንካራ በማድረግ ለደንበኞች በሞባይል መተግበሪያ አማካኝነት ጥያቄ እንዲያቀርቡና አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎችን አሰራሮችን በመፍጠር ለደንበኞቻችን አገልግሎት በመስጠት የእርካታ ደረጃቸውን እናሻሽላለን።
አዲስ ዘመን፡- አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችሉ እቃዎች በምን አግባብ ነው የምትገዙት? ከጥራት ቁጥጥር አንጻርስ በምን ያህል ደረጃ ተአማኒ የሆነ ፍተሻ አድርጋችሁ ነው ግዥ የምትፈጽሙት?
አቶ ሽፈራው፡– እንደ ተቋም የግብአት አቅርቦትን በተመለከተ ስታንዳርዳይዝድ የሆነ ስፔስፊኬሽን አለን። በዚያ ስፔስፊኬሽን መሠረት የሀገር ውስጥ ተጫራቾች ቅድሚያ እንሰጣለን። በሀገራችን ትራንስፎርመር እና ኮምፓክት የሚመርቱ ተጫራቾች አሉ። ለእነሱ ቅድሚያ ይሰጣል። ለሀገር ውስጥ ተጫራቾች እንዲሁ ለጨረታ ቅድሚያ አይሰጣቸውም።
መጀመሪያ የማምረት ብቃታቸውን በማረጋገጥ የተሟላ ዝግጅት አላቸው ወይስ የላቸውም የሚለውን አስቀድመን እናያለን። በዚያ መሠረት ብቁ ከሆኑ እንዲያመርቱ እድል እንሰጣቸዋለን። ካመረቱም በኋላም ደግሞ ፋብሪካቸው ውስጥ ወይም በሌላ አካልም የፍተሻ ሥራዎችን እናደርጋለን። ይሄ በእኛ ኢንጂነሮች የሚደረግ ነው።
በእኛ የኢንጂነሪንግ ክፍል ስር የጥራት ክፍል አለ። ከጥራት ጋር ተያይዞ ይህ ክፍል ቁጥጥር እና ክትትል ያደርጋል። በዚህም ምክንያት የጥራት ደረጃ ሳያሟሉ ወደ እቃ ግምጃ ቤትም ገቢ እና ርክክብም የሚደረግ እቃ አይኖርም። በሀገር ውስጥ ተጫራቾች የማይሟላውን ደግሞ በተለይ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱም ውስን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያለንን ሪሶርስ ተጠቅመን ከውጭ እናስገባለን።
ከውጭ በምስናስገባቸው እቃዎች ላይ የሚደረገው ቁጥርም ከሀገር ውስጥ ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ ማለት ለተጫራቾች ዲዛይን ስፔስፊኬሽን ይሰጣቸዋል። ዲዛይን አፕሩቫል እናደርጋለን። ቀጥሎም ምርቱ ከተመረተ በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ ከመጓጓዙ በፊት በኛም አንድ ሰው የጥራት ፍተሻ ያደረጋል። ግዢ የፈጸመበት እቃ የተቀመጠውን መስፈርት ካሟላ ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ ይመጣል። ወደ ሀገር ውስጥ ከመጣ በኋላም የተለያዩ የጥራት ማረጋገጫ ሥራዎችን እንሰራለን። በሰራነው የጥራት ማረጋገጫ መሠረት እቃው ብቁ ከሆነ ወደ እቃ ግምጃ ቤት ይገባል፤ ለተጠቃሚዎችም ይከፋፈላል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ የግዢ ሥርዓት ምን ያህል አስተማማኝ ነው ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ሽፈራው፡- ውስንነቶች ሊኖሩበት ይችላሉ። የውስንነት ምክንያት አንደኛው የጥራት ፍተሻ የምናካሂድባቸው ማዕከላቶች ዓለም አቀፍ አክሪዲቴሽን የሆነ አይደለም። በሀገር ውስጥ ያሉት፤ ከውጪ በሚቀርቡት ላይ ምንድነው የምናደርገው ‹‹ኢንዲፔንደንት ቴስት ሰርተፊኬት›› ሪፖርት እንዲያቀርቡ እናደርጋለን። እኛ ‹‹ኢንዲፔንደንት ቴስት ሰርተፊኬት›› ሪፖርቱን ከተመለከትን በኋላ ለግዢ የቀረቡትን እቃዎች ያላቸውን ብቃት እንፈትሻለን።
ቀጥሎም በገለልተኛ አካል ‹‹ቴስት›› እንዲደረጉ እናደርጋለን። እንደዚህም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ ችግሮች ይከሰታሉ። ችግር ባጋጠመን ጊዜ ሀገር ውስጥ ባሉት የጥራት ተቆጣጣሪዎች ፍተሻ የምናደርግ ይሆናል። ይህንን ችግር በዘለቄታው ለመፍታት ግን የተስማሚነት ፍተሻ አቅም እንጠቀማለን። ነገር ግን ከዚህ ውጭ የሆኑ እና በዚህ ደረጃ የማይሰሩ በከፍተኛ ቮለቴጅ ቴስት የሚፈልጉ ሥራዎች ይኖራሉ። እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ በራሳችን ኤክሰለንስ ሴንተር (የልህቀት ማዕከል) አዲስ አበባ ሳሊተ ምህረት አካባቢ እየገነባን ነው። እሱ ሲጠናቀቅ ተቋሙን ያሳድጋል ብለን እናምናለን። ከጥራት ጋር የሚኖሩ ፍተሻዎችን በጣም ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ያደረጋል። ግንባታው ሲጠናቀቅ ግብዓቶች በሙሉ በዚያ ስር እንዲያልፉ እናደርጋለን፤ ሰው ኃይል አቅም የማሳደግ ሥራዎችንም እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፡- ህብረተሰቡ መብራት ሲበላሽበት ወይንም በአካባቢው አደጋ ሲደርስበት በተቋማችሁ የጥሪ መስመር ላይ በተደጋጋሚ እንደሚሞክሩ ነገር ግን ምንም ዓይነት ምላሽ እንደማያገኙ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማል። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?
አቶ ሽፈራው:- እኛም በዚህ ጉዳይ ሃሳቦችን ለመሰብሰብ ሞክረናል። የጥሪ መስመሩ እንደማይነሳ ቅሬታዎች ይነሳሉ። እነዚህ ቅሬታዎች ደግሞ መፍትሔ እንዳልተሰጣባቸው ይነሳል። የጥገና አቤቱታ ሲመጣ በምን መልኩ ነው የሚፈታው? አንድ መብራት ተቋርጦብኛል ብሎ ያመለከተ ተጠቃሚ በምን ያህል ሰዓት ውስጥ የጥገና አገልግሎት ሊሰጠው ይገባል? እና መሰል ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት እየሰራን ነው።
በእኛ የዳሰሳ ጥናት እንዳረጋገጥነው ለደንበኞች ቅሬታ አንዱ ምንጭ የሆነው ከጥገና አገልግሎት ጋር የምንስጠው አገልግሎት ቀልጣፋ ያለመሆን ነው። ከጥገና ጋር ተያይዞ ለደንበኞች ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች ይስተዋላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንደኛው የጥገናው ስታንዳርድ ተጠቃሽ ነው። የጥገና ስታንዳርድ እንደየችግሩ ዓይነት ይወሰናል። ለምሳሌ በጣም ቀላል የሆነ ዝቅተኛ መስመር ላይ ደንበኞች ሰፈር ላይ የተከሰተ ችግር ካለ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል። ሲስተም ላይ ያለ ችግር ወይም ከትራንስፎርመር ብልሽት ጋር የተያያዙ እና የመሳሰሉት እቃን መተካት የሚጠይቁ ችግሮች ካሉ ከሁለት እስከ ሶስት ቀን ሊያስፈልግ ይችላል።
ምንም ይሁን ምንም ግን ችግሩ በቶሎ እንዲቀረፍ ለማስቻል ስለችግሩ ደንበኛው የሚከታተልበት ግልጽ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። በ2017 በጀት ዓመት ለመሥራት ከአቀድናቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ከጥገና ጋር በተያያዘ የሚነሱ የደንበኞችን ቅሬታ መፍታት መቻል ነው። ተቋሙ 904 እና 905 የተሰኙ የጥሪ ማዕከሎች አሉት። ጥያቄውን በእነዚህ የጥሪ መስመሮች ላይ ሊያቀርብ ይችላል። 904 ለኢንዱስትሪ ወይንም ቁልፍ ለሚባሉ ደንበኞች ነው። ይህ አዲስ ያመጣነው ሲስተም ነው። 905 ደግሞ የነበረ የጥሪ ማዕከል ነው። ነገር ግን ማዕከሉ በውስን አቅም ሲሰራ የነበረ ነው። ስለሆነም አሁን ላይ አንደኛ የጥሪ ማዕከሉ ራሱን የማሻሻል እና የማሳደግ ሥራ ያስፈልግ ስለነበር እሱን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራን ነው።
ከቴክኖሎጂው በተጨማሪም ጥሪን በሚቀበሉ ባለሙያዎች ቁጥር የማሳደግም ሥራዎችንም እየሰራን ነው። እስካሁን ከ80 በታች የጥሪ ማዕከል ሠራተኞች ነበሩን። አሁን ላይ ወደ 180 ለማሳደግ እየሰራን ነው። ለዚያ የሚሆን የግንባታ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው። በዚህ አንድ ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን። ያ ብቻም ሳይሆን እነዚህን ሠራተኞች የምንከታተልበት ሥርዓት ላይ ክፍተቶች ነበሩ። ጥሪ ላይነሳ ይችላል፤ ከውስንነትም ሆነ ከሌሎች ምክንያቶች በመነጩ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ያ ጥሪ ሲመጣ በስልክ ተደውሎ ለጥገና ቡድኑ ይነገራቸዋል።
ለጥገና ቡድኑ ከተነገራቸው በኋላ ባለሙያዎች ደግሞ ቀልጠፍ ብለው ሰርተው ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ነገር ግን በዚያ መሠረትም የማይሰሩ አሉ። በመሆኑም ይህ ሥርዓት ሪፎርም መደረግ አለበት በሚል መግባባት ላይ ተደርሶ የሪፎርም ሥራ እየተሰራ ነው። በሪፎርሙም ደንበኛው ጥሪ ካደረገ እና ጉዳዩ ወደ ጥሪ ማዕከሉ ከመጣ በኋላ ክትትል ይደረጋል። ቀጥሎም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የጥገና ዲስፓች ቡድን ይልካል። የጥገና ክፍሉ ደግሞ ለሚጠግነው ቡድን ይሰጣል፤ የሚጠግነው ቡድን ጥገናውን ካከናነወነ በኋላ የሚያሳውቅበትን መተግበሪያ እየተሰራ ይገኛል። ይህም ሲስትም ደንበኞች ጥገና ስለመደረጉ የሚያረጋግጡበት ሥርዓት አለው። ይህ ሲሆን አሁን ያለውን ችግር ይፈታል ብለን እናስባለን።
በአዲስ አበባ ተወስኖ የነበረውን ይህን አሰራር ወደ ክልሎችም እንዲሄድ እናደርጋለን። ይህንንም በ2017 በጀት ዓመት ሁለተኛውን ሩብ ዓመት በኋላ እንጨርሳለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፡- የድርጅቱ ሠራተኞች ለጥገና በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ከማህበረሰቡ ገንዘብ ተሰብስቦ ይሰጠን ብለው በግልጽ ይጠይቃሉ። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ደግሞ በባለሙያዎች እቃዎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ነቅሎ የመውሰድ እና የስርቆት ሥራ ይሰራሉ። ለስርቆቶች የሠራተኞች ደሞዝ ማነስ እንደ ምክንያት ይነሳል። ይህንን ብልሹ አሰራር ማስቀረት ያልተቻለው ለምንድነው?
አቶ ሽፈራው፡- የሠራተኞችን ደሞዝ በተመለከተ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆኑ በጣም ጥሩ ነው ባይባልም የተሻለ ደሞዝ እንከፍላለን። እንደ ኢትዮጵያ ሀገራችንንም ካለችበት ሁኔታ አንጻር መጥፎ ነው የሚባል አይደለም። ተቋሙ ባለው ገቢ ልክ ለሠራተኞቻችን ደሞዝ ይከፍላል። በሂደትም ያሉ ነገሮችን በዚያ መሠረት ነው የምናስተካክለው።
አንድ ሰው ደሞዙ አነስተኛ ስለሆነ አይደለም የሚሰርቀው፤ አባቶች ሲተርቱ ‹‹ ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል›› ይላሉ። ስለዚህ አንድ ሰው ደሞዙ ስላለነሰ አይደለም የሚሰርቀው አመል ሆኖበት እንጂ።
በነገራችን ላይ ስርቆቱን ሠራተኞቻችን ብቻቸውን ሳይሆን ከተቋማችን ውጭ የሚገኙ ደላሎችም ተሳታፊ ናቸው።
በመርህ ደረጃ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደዚህ ዓይነት ተግባርን የሚታገስበት አሰራር የለም። በስርቆት ተግባራት ላይ በተገኙ ሠራተኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል። ከዚህ ቀደም በበርካታ ሠራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዶም ያውቃል። ነገር ግን ይህንን ተግባር መከላከል የሚቻለው በአንድ ወገን ብቻ አይደለም።
ዜጎች እና ደንበኞቻችንም ስለመብቶቻቸው ማወቅና መታገል መቻል አለባቸው። ደንበኞች እንዲህ የሚያደርጉ ደላላዎችን እና ከተቋማችን የሚገኙ ተባባሪ አጋልጠው መስጠት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ተግባር የተሰማሩ እና ወደ ሕግ ቦታ ቀርበው የእርምት እርምጃ የተወሰደባቸው ላይ ሁልጊዜም በየዓመቱ በሪፖርቶቻችን ላይ እናወጣለን። በዚህ ዓመትም የምናወጣ ይሆናል።
ደንበኞች መረዳት ያለባቸው ይህንን ሥራ የሚሰሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጣም ጥቂት ናቸው። ነገር ግን ይህንን ሥራ የሚሰሩ በርካታ ደላሎች አሉ። በአንድም ይሁን በሌላም ምክንያት ውስጥ ካሉ ሠራተኞች ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ ደላሎች እና ደንበኞች ከሌባ ጋር ተባብሮ መሥራት ወንጀል መሆኑን ተገንዝበው ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል።
በተጨማሪም ከሠራተኞች ሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ሞባይል አፕሊኬሽን እየተተገበረ ነው። ይህ አልቆ ሥራ ሲጀምር ለደንበኞች ይፋ ይደረጋል። ነገር ግን ሕዝቡ ለብልሹ አሰራር የሚጠየቀውን ገንዘብ እምቢ ማለት አለበት። ችግሩ ሊቀረፍ የሚችለው ደንበኛውና ተቋሙ ተቀናጅቶ ሲሰራ ነው። ይህ ሲሆን ሌቦችን ከሲስተም ማስወጣት ይቻላል። አሁን ላይ እየተሰራ ያለው ሥራ እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ያስወግዳል። የሌብነት ሱስ ያለባቸውና ከሌቦች ጋር ግንኙነት ያላቸው ካልሆኑ በስተቀር ደንበኞች በእጅ ስልካቸው ለአገልግሎት ሰጭው በጥሪ ማዕከሉ አማካኝነት መደወል የፈለጉትን አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ።
የመልካም አስተዳደር እና ምርመራ ቡድን
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2017 ዓ.ም