በዓመት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል ፋብሪካ በድሬዳዋ ይገነባል
አዲስ አበባ፡- የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን ሲገነባ ከነበረው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር የነበረው ውል መቋረጡን የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡ በዓመት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል ፋብሪካ በድሬዳዋ ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተባባል ውድነህ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለይ እንደገለጹት፤ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካን ሲገነባ ከነበረው ሜቴክ ጋር የተገባው ውል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቋርጦ በሽርክና የሚቀጥልና የፋይናንስ ምንጭ ይዞ የሚመጣ አካል ተፈልጎ ሥራው እንዲሰጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በመስከረም 2011 ዓ.ም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ሜቴክም ውሉ መቋረጡን እንዲያውቀው ተደርጓል፡፡
እንደ አቶ ተባባል ገለጻ፤ ሜቴክ በ2004 ዓ.ም መገንባት የጀመረው የያዩ ማዳበሪያ በውሉ መሰረት በ2006 ዓ.ም መጠናቀቅ ቢኖርበትም እስካሁን አፈጻጸሙ ከ44 በመቶ አላለፈም፡፡ የፕሮጀክቱም ሂደት ተጠንቶ አዋጪነቱ አጠያያቂ በመሆኑ ውሉ የተቋረጠ ሲሆን፤ እስከ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሳይቱንም የሰነዱንም ርክክብ ለመጨረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና በድሬዳዋ በዓመት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለመገንባት ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት አቶ ተባባል፤ ግንባታው በሁለት ፌዝ (ዙር) የሚጠናቀቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በመጀመሪያ ዙር የሚገነባው ፋብሪካ በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን ዩሪያና 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን ኤንፒ ኤስና ኤን ፒኬ የሚባሉ የማዳበሪያ ዓይነቶችን እንደሚያመርት ጠቁመዋል፡፡
ለፋብሪካው ግንባታ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ በሞሮኮ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በግል ባለሀብቶች ሽርክና እንደሚገነባ የገለጹት አቶ ተባባል፤ የሞሮኮ መንግሥት በፋብሪካው 50 በመቶ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ 20 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ 30 በመቶውን የፋብሪካ ድርሻ አቅም ላላቸው ባለሀብቶች የተተወ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ተባባል ማብራሪያ፤ ለፋብሪካው ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ጥናቶች ተጠናቀዋል፡፡ ፋብሪካው በድሬዳዋ የት አካባቢ መገንባት እንዳለበት የቦታ ልየታ ተደርጓል፡፡ ከግንባታው በፊት በፋብሪካው አካባቢ እና በፋብሪካው አካባቢ በሚኖሩ ማህበረሰቦች ዙሪያ የሚከናወነው ጥናቱ ተጠናቋል፡፡ ለፋብሪካው ግብዓት የሚመላለስበት እና የፋብሪካው ውጤቶች የሚንቀሳቀሱባቸው መሰረተ ልማቶች ያሉበት ሁኔታ ልየታ ተደርጓል፡፡ ከሞሮኮ መንግሥት ጋር የሽርክና ስምምነትም ተጠናቋል፡፡ በቅርቡ የፕሮጀክት ኮንትራክተሩ ተለይቶ ግንባታው ይጀመራል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ እ.አ.አ በ2022 ተጠናቆ ማዳበሪያ ማምረት ይጀምራል፡፡
እስከ አራት ዓመት ድረስ ከኦጋዴን ወጥቶ በጅቡቲ በኩል ለዓለም አቀፍ ገበያ ይቀርባል ተብሎ የሚታሰበው የተፈጥሮ ጋዝ በድሬዳዋ ላይ ተጠልፎ ለፋብሪካው ግብዓትነት ለማዋል መታሰቡን የተናገሩት አቶ ተባባል፤ ከሞሮኮ የሚመጣ አሲድ ለግብዓትነት ጥቅም ላይ ይውላል ብለዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ኢትዮጵያ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን እስከ አንድ ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ያስፈልጋታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 4 /2011
መላኩ ኤሮሴ