የጊፋታ በዓል ዜጎች ለሀገር አንድነትና ዕድገት ተባብረው እንዲሠሩ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል

አዲስ አበባ፡– ጊፋታ በዓል ዜጎች ለሀገር አንድነትና ዕድገት ተባብረው እንዲሠሩ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የወላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ምህረቱ ሳሙኤል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር እንደመሆኑዋ መጠን ጊፋታን እና መሰል በዓላትን በጋራ ተሰባስቦ ማክበር ዜጎች ለሀገር አንድነትና ዕድገት ተባብረው እንዲሠሩ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

ይህም በህብረ ብሔራዊነት ውስጥ ያሉ አንድነቶችን በማጠናከር የባህል ቅብብሎሽ እንዲዳብር እና ሕዝቦች በጋራ ተዋደውና ተከባብረው ለሀገር አንድነትና ዕድገት ተባብረው እንዲሠሩ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡

የጊፋታ በዓል የወላይታ ሕዝብ ጥንት በአንድ ቦታ ሰፍሮ መኖር ከጀመረበት ጊዜ እንስቶ የፀሐይና የጨረቃ ኡደትን ተከትሎ በሚያደርገው የዘመን አቆጣጠር አሮጌውን ዓመት ሸኝቶ አዲሱን ዓመት የሚቀበልበት የዘመን መለወጫ በዓል መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለበዓሉ የሶዶ ከተማን ከማስዋብ ጀምሮ የጊፋታ ሩጫና የኤግዚቢሺን ዝግጅቶች የተከናወኑበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓሉ በዛሬው ዕለት ‘’የጊፋታ ዕሴቶች ለሁንተናዊ ብልጽግና’’ በሚል መሪ ቃል በሩጫ ውድድር፣ በቋንቋና የባህል ሲምፖዚየም፣ በባህላዊ ሙዚቃ ዝግጅትና የባህል ትርኢቶች በሚቀርቡበት ሁኔታ እንደሚከበር ገለጸው፤ በተመሳሳይ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ታዋቂው የወላይታ ቁርጥን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ የምግብ ዓይነቶች ለበዓሉ ድምቀት ይቀርባሉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተዘጋጁ ምግቦችና መጠጦች ከተመገቡ እና ከተጠጡ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ በመሰባሰብ በአካባቢው በአንድ ታዋቂ ሰው ደጃፍ ላይ ከወራት በፊት ያቆሙትን ጉሊያ የበዓሉ ዕለት (ሹሆ ዎጋ) አመሻሽ ላይ ካቀጣጠሉ በኋላ በጋዚያ ጨዋታ ይዝናናሉ፡፡

እንዲሁም በዓሉን ሕዝቡ በጋራ በአንድ ላይ ተሰባስቦ እንዲያከብር በማሰብ በወላይታ ሶዶ ስቴዲየም የሙዚቃ እና የመዝናኛ ዝግጅቶች የሚቀርቡ ሲሆን የጉሊያ ዝግጅትም በዚያው ሥፍራ የሚከናወን ይሆናል፡፡

የጊፋታ በዓል በውስጡ ለማህበረሰቡ በርካታ ጠቀሜታ ያላቸውን ዕሴቶች የያዘ መሆኑን አቶ ምህረቱ አንስተው፤ በዓሉ መከበሩ እነዚ ዕሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲጎለብቱ እና ይዘታቸውን ሳይለቁ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በበዓሉ ለመታደም ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ወላይታ የሚመጡ ግለሰቦች በዓሉን ከማክበር የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ በማድረግ የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የጊፋታ ዕሴቶች የህብረ-ብሔራዊነት ዋነኛ መገለጫ እንደመሆናቸው መጠን በመላው ዓለም ያሉ ዜጎች አንድ ላይ ማክበራቸው፣ በአንድ ማዕድ መጋራታቸው የባህል ቅብብሎሹ እየዳበረ እና እየጎለበተ እንዲዘልቅ የሚያችል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You