“ስለኢትዮጵያ መቼም በእኛ በኩል የምንሰስተው፣ የማንሆነው፣ የማናደርገው ነገር አይኖርም፤ መነሻችንም መሰረታችንም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ማኖር፤ ሕዝቦቿም ከዚያ አንድነት እንዲጠቀሙ ማብቃት ነው፡፡ ርዕያችንም የነበረው ይኸው ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህም በተቻለን ሁሉ ባለን አቅምም ጥረት የምናደርገው ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡” የሀንሳር ጋራድ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ‘ስለኢትዮጵያ’ ካዘጋጃቸው መድረኮች በአንደኛው መድረክ ላይ የተናገሩት ነበር፡፡
ሀገር የብዙዎች መኖሪያ መሆኗ ግልጽ ቢሆንም በሀገር ግንባታ ሂደት ለታሪክ የሚቀመጥ ሕዝብና ሀገርን የሚጠቅም ሥራ የሚከውኑት ጥቂቶች ናቸው። ምክንያቱም ከራስ አስበልጦ ለሌሎችና ለሀገር መሥራት አነሰም በዛ የሚያስከፍለው መስዋእትነት በመኖሩ ነው። ኢትዮጵያም ዛሬ የደረሰችው ትናንት ብዙዎች በከፈሉት መስዋዕትነት ጭምር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የአስክሬን ሽኝት ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ፕሮፌሰሩን እንዲህ ገልጸዋቸዋል፡፡ ‹‹እጃቸው ደም የለበትም፤ ልባቸው ጥላቻ የለበትም። ቤተሰብን መውደድ ተግቶ መሥራትና በእንዲህ ያለ ክብር ለመሸኘት መብቃት ታላቅ እድል ነው። ቀጣዩ ትውልድ ይህንን መማር አለበት። ፕሮፌሰር በየነ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ታታሪና ሀገር ወዳድ ምሁር ነበሩ። ለሀገራቸውም በርካታ ሥራዎችን ሠርተው አልፈዋል፡፡ ይህ ሥራቸውም ከመቃብር በላይ ሲታወስ ይኖራል። ሁላችንም ጊዜ ሳናባክን ለሀገር ጠቃሚ ሥራዎችን ሠርተን ማለፍ አለብን ››ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ልጃቸውም ሚሻ በየነ ጴጥሮስ አባታቸውን የገለጹት እንዲህ ነበር ‹‹ሰው ወዳድ ነበር። የህይወት መርሁ የነበረው፤ እግዚአብሔርን የወደደበትን መንገድ ለሰዎች በመኖርና ሰዎችን በመውደድ ነው። ይህንንም በሥራው ፣ በቤተሰቡ በአባትነትና በባልነት ተግብሮታል። በማህበራዊ ግንኙነት ረገድ ከየትኛውም ማህበረሰብ ጋር ጠንካራ ቁርኝት ነበረው። ሰው ራስ ወዳድ ካልሆነ በቀር ጊዜው በቂ ነው ይቻላል ይለን ነበር። ››
ውልደትና እድገት
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከአባታቸው አቶ ጴጥሮስ ሎዳሞ ሰብሮ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሸዋዬ ኢብራሒም በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን በምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ አምቡርሴ ቀበሌ መጋቢት ሁለት ቀን 1942 ዓ.ም ተወለዱ። የፕሮፌሰር በየነ ወላጅ አባት ጴጥሮስ ሎዳሞ ወታደርና የክቡር ዘበኛ አባል፣ በኋላም የፖሊስ ሠራዊት አባል በመሆናቸው በሥራቸው ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ከቤተሰባቸው እርቀው ይኖሩ ስለነበር ፕሮፌሰር በየነ ልጅነታቸውን ያሳለፉት ከአያታቸው ጋር ነበር።
ፍትሕ ተዛብቶ ሲያዩ ዝም የማይሉት የፕሮፌሰር በየነ ወላጅ አባት የሆኑት አቶ ጴጥሮስ ሎዳሞ ከመንደራቸው ርቀው በፍትሕ አደባባይ ተሟግተው ፍትሕ ተበይኖላቸው ወደ ቤት ሲመለሱ ባለቤታቸው ወንድ ልጅ ወልደው በማግኘታቸው ደስታቸው ድርብ ሆነ። ያገኙትን ፍትሕ ለማስታወስ ሲሉም ልጃቸውን በየነ ብለው ሰየሟቸው። የልጅነት ጊዜያቸውን እንደማንኛውም የአካባቢው ልጅ ከብት በመጠበቅና በመወጫት ከቤተሰባቸው ጋር በመልካም እንክብካቤ አድገዋል።
የትምህርትና አካዳሚክ ጉዞ
ፕሮፌሰር በየነ አባታቸው ጴጥሮስ ሎዳሞ የክብር ዘበኛ አባል፣ የኮሪያ ዘማችና በኋላም የፖሊስ ሠራዊት አባል ስለነበሩ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው መንፈሳዊ ትምህርትን የቀሰሙ በመሆናቸው በለጋ እድሜያቸው ትምህርት ቤት እንዲገቡ እድል ፈጥሮላቸዋል። በሀዲያ ዞን ሾኔ ከተማ በሚገኘው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ የተማሩት ፕሮፌሰር በየነ ከልጅነታቸው ጀምሮ በጣም ጎበዝ ተማሪ በመሆናቸው በአንድ ዓመት ሁለት ሁለት ክፍሎችን እየደረቡ እየተማሩ በሦስት ዓመታት ብቻ ስድስተኛ ክፍልን ማጠናቀቅ ችለዋል።
የሰባተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሆሳዕና ከተማ በሚገኘው ራስ አባተ ቧያለው ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ ቀጥሎ ያለውን ትምህርት ለመከታተል ከቤተሰብ መለየት ግድ ነበርና ሻሸመኔ ከተማ ኩየራ ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ስምንተኛ ክፍል ያስመዘገቡት ውጤት ከፍተኛ በመሆኑ አዳማ በሚገኘው አፄ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ድረስ ለመከታተል ስኮላር ሺፕ አገኙ። በመቀጠልም የ12ኛ ክፍል (ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ መዘጋጃ) ትምህርታቸውን በዕደማርያም ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለው አጠናቅቀዋል።
የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በከፍተኛ ማዕረግ ያጠናቀቁት ፕሮፌሰር በየነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀሉ አንድ ሰው በአእምሮአቸው ይዘው ነበር የገቡት። አፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት ሲማሩ በሳይንስ ክለብ አማካኝነት እውቁ ተመራማሪ ዶክተር አክሊሉ ለማ በእንግድነት ተጋብዘው ንግግር ሲያደርጉ ሰሙ። ዶክተር አክሊሉ በሠሩት ጥናትና በሳይንስ ዘርፍ ባካሔዱት የምርምር ሥራ በመመሰጣቸው ዶክተር አክሊሉ ለማን የትምህርት ምሳሌያቸው አድርገው ወሰዱ።
እናም ወጣቱ በየነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀል የዶክተር አክሊሉን ፈለግ በመከተል በባዮሎጂ (ስነሕይወት) ትምህርት ክፍል ትምህርታቸውን በመከታተል እሳቸውና ጓደኞቻቸው የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ሥርዓት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ምሩቆች ሆነው በ1965 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
በወቅቱ የውጪ ሀገር መምህራንን ለመተካት እንቅስቃሴ ላይ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደ በየነ ጴጥሮስ ያሉ የላቀ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎች በጀማሪ መምህርነት እንዲሠሩ እድሉን አመቻችቶ ነበርና እሳቸውም አንድ ብለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመሩ። ለሁለት ዓመት በዩኒቨርሲቲው ካስተማሩ በኋላ በ1967 ዓ.ም የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ አሜሪካ ዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ በማምራት በ1970 ዓ.ም የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን በትሮፒካል ዲዚዝ አጠናቅቀዋል። ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ በመሆናቸውም እዚያው አሜሪካን ሀገር የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከቱላን ዩኒቨርሲቲ በመከታተል በማህበረሰብ ጤና (ፐብሊክ ሄልዝ) የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ፕሮፌሰር በየነ በርካቶችን ከቀረጹበት የመምህርነት ህይወታቸው በተጨማሪ በተላላፊ በሽታዎች (ትሮፒካል ዲዚዝ) ላይ በርካታ ምርምሮችን ከሥራ አጋሮቻቸው እና ተማሪዎቻቸው ጋር አከናውነዋል። በተለይም በወባ በሽታ፣ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ላይ፣ በሳምባ ነቀርሳ፣ እንዲሁም በርከት ባሉ ሌሎች ህዋስ ወለድ በሽታዎች ላይ ሰፊ ምርምር አድርገዋል። ባልተሟሉ ቤተ ሙከራዎች እና ሁኔታዎች ውስጥ በተለይ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ከሌሎች በሽታዎች ጋር ስላለው ግንኙነት ሰፊ ምርምር አድርገዋል። በዚህም ከ193 በላይ ጥናቶችንና የምርምር ጹሑፎችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ይፋ አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ፕሮፌሰር በየነ በርካታ ወጣት ተመራማሪዎችን በመምራትና በማስተባበር ለውጤት ያበቋቸው ምርምሮች በስነ ሕይወት ሳይንሱ ምርምር ዘርፍ በዓለም አቀፍና በሀገር ቤት ላበረከቱት ድርሻም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል።
ፖለቲካዊ ሕይወትና ትግል
የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የፖለቲካ ሕይወት እጅግ ልዩ ህይወት ነው። የብርቅዬ ልጆቿን ደም በሚጠጣው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በእሳት የተፈተነ፣ ለአፍታም ያልተሸነፈ፣ በመላው ኢትዮጵያ ለሦስት አስርት ዓመታት ያንጸባረቀ፣ በፖለቲካ እሳት ተፈትኖ ያልተበገረ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል አሻራ አስቀምጠው አልፈዋል። በመሆኑም ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ስነ ምህዳር ውስጥ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ምልክት ተደርገው የሚወሰዱ አንጋፋ ፖለቲከኛ ነበሩ። ተወልደው ባደጉበት የገጠር መንደር አርሶ አደሮች የለፉበትንና ላባቸውን ያፈሰሱበትን የማሳ ፍሬ ለበዝባዦች ሲገብሩ እያዩ ያደጉት ፕሮፌሰር በየነ፤ የሕዝብ በደል የገባቸው በለጋ እድሜያቸው ነበር።
ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ ደግሞ የተበደሉ አርሶ አደሮችን አቤቱታ ለመጻፍ እድል በማግኘታቸው የማህበረሰቡን የመከራ ጥልቀት ለመገንዘብ አስቸሏቸዋል። እንዲህ በልጅነታቸው የሕዝብን በደል የተረዱት ፕሮፌሰር በየነ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሲቀላቀሉ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በወቅቱ የሚያነሱትን የመብት ጥያቄ በፍጥነት ተረድተው ወደ ትግሉ ለመግባት አፍታም አልፈጀባቸውም።
ፕሮፌሰር በየነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ደጅ ከረገጡ አንስቶ የኢትዮጵያ የለውጥ ጠያቂዎችን
ሃሳብ ተጋርተው ታግለዋል። የገበሬውን ምሬት በቅርብ ማወቃቸው እና የአስተዳደር ብልሹነቱን መታዘባቸው፣ እንዲሁም መሠረታዊ የሚባሉ የማህበራዊ ግልጋሎቶች ቅንጦት ከሆኑባቸው የገጠር መንደሮች በአንዱ ማደጋቸው ብዙ መሻሻል ያለበት ጉዳይ እንዳለ ለፕሮፌሰር ግልጽ ነበር። በዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት መምህርነታቸው ወቅት ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት ይመስረት›› የሚል ደብዳቤ ይዘው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጋራ በመሆን ለደርግ ጽህፈት ቤት በማስገባት ቁርጠኛ የሕዝብ ልጅ መሆናቸውን በተግባር ያስመሰከሩ ታላቅ የፖለቲካ መሪ ነበሩ።
በ1967 ዓ.ም የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ለመከታተል አሜሪካን ሀገር በነበራቸው ቆይታ በሰሜን አሜሪካ የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳታፊ ነበሩ። በ1970 ዓ.ም የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ፕሮፌሰር በየነ ሀገራቸውን ለማገልገል ካላቸው ጥማት እና የፖለቲካ ትግሉን በቅርበት ሆኖ መታገል ያስፈልጋል ብለው በማመናቸው በወቅቱ በሀገር ውስጥ ከነበረው የፖለቲካ ትኩሳት አንጻር ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንደ እብደት በሚቆጠርበት ጊዜ የብዙ መካሪዎችን ምክር ወደ ጎን በመተው አሻፈረኝ ብለው ሀገራቸውን ለማገልገል ተመልሰዋል። ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው የማስተማር ሥራቸውን እንደቀጠሉ ከሙያ ሥራቸው ጎን ለጎን በወቅቱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሊስተካከሉ ስለሚገባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች አስተያየት ከመስጠትና ለለውጥ ከመወትወት ቸል ብለው አያውቁም።
በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ በሽግግር መንግሥት ምስረታ የሀዲያን ሕዝብ የሚወክል የፖለቲካ ቡድን በማደራጀት የፊት ለፊት የፖለቲካ ትግላቸውን ማካሔድ የጀመሩት ፕሮፌሰር በየነ፤ በሽግግር መንግስቱ የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል። በሽግግር መንግስቱ ላቅ ያለ አስተዋጽኦም አበርክተዋል። ከእዚህም መሀከል፤ የቀድሞ ሠራዊት እንዳይበተን ከፍተኛ ትግል ማድረጋቸው፣ የወቅቱ አየር ኃይል ህልውናው እንዲቀጥል የበኩላቸውን ሚና መወጣታቸው፤ በሰብአዊ መብት አያያዝ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ያለ ምንም መሸራረፍ በሕገመንግሥቷ እንድትካተት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማታቸው እንዲሁም የፕሬስ ነጻነት እንዲከበርና የሕግ ከለላ እንዲያገኝ የበኩላቸውን ሚና መወጣታቸው ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህ ለአብነት ተነሱ እንጂ ፕሮፌሰር በየነ ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ በትምህርትና እውቀት ስርጸት፣ በብሔር ብሔረሰቦች መብት፣ መልካም አስተዳደርና ብልሹ አሠራሮች ወዘተ.. ላይ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። ከፖለቲካ ህይወት ፍልስፍናቸው የሚቀዳው ሰላማዊ የትግል እና የሙግት ሥርዓትን ለማስፈን አጥብቀው ታግለዋል። የሀዲያን ሕዝብ ወክለው የሽግግር መንግሥቱን የተቀላቀሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የደቡብ ሕብረት ፓርቲን በማቋቋም ከ1983 ዓ.ም እስከ 1987 ዓ.ም በነበረው የሽግግር መንግሥት ወቅት የተደራጀ ፖለቲካዊ ትግል በማድረግ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳቦችን አቅርበዋል።
ከ1987 ዓ.ም አንስቶ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባልተገባ መንገድ መጓዝ ሲጀምር ፕሮፌሰር በየነ በገዢው ፓርቲ አምባገነናዊ አካሔድ እና በተቃዋሚዎች የኃይል እና የእልህ መስመር መካከል ሰላማዊ መስመርን እየፈለጉ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን አድርገዋል። የምርጫ ቅስቀሳ በሚያካሂዱበት ወቅት በተወለዱበት መንደር ጭምር እንደ ባዳ እየተንገላቱ ምርጫን ደጋግመው በማሸነፍ የሕዝብን ድምጽ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያሰሙ ቆይተዋል። በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አማራጭ ላይ የማይናወጥ አቋም ያላቸው ፕሮፌሰር በየነ፤ የሕዝብን ድምጽ ለማሰማት ሁልጊዜም ቢሆን ተገቢው ቦታ ላይ ይገኛሉ። ጠባብ እድሎችን ታግሎ ማስፋት፣ ሰላማዊ መንገድን መከተል፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መልዕክት ማስተላለፍና መታገል የፕሮፌሰር በየነ ልዩ መገለጫቸው ነበር።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዋልታ ረገጥነትና ጽንፈኝነት ተላቅቆ በሰከነ መንገድ እንዲጓዝ ብዙ ደክመዋል። የተበታተኑ ኃይሎች እንዲሰባሰቡና የሃሳብ ውህደት ለመፍጠር በሀገር ውስጥና በውጪ ያሉ ከ50 በላይ የፖለቲካ ኃይሎችን በማሰባሰብ የኢትዮጵያ የሰላምና ዲሞክራሲ አማራጭ ኃይሎች ምክር ቤት በመመስረት በመምራት የተረጋጋ ፖለቲካ ለመፍጠር የመሪነት ሚናቸውን ተወጥተዋል። በአንድነትና ሕብረት ጠንካራ እምነት ያላቸው ፕሮፌሰር፤ ከምክር ቤቱ ምስረታ በተጨማሪ አስራ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማደራጀት “የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያ ኃይሎች ሕብረት” በማቋቋም የተደራጀና የተረጋጋ የፖለቲካ ትግል አካሂደዋል።
በደቡብ ክልል ይህ ነው የሚባል የተቃዋሚ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ባልነበረበት ወቅት ቀድመው የነቁት ፕሮፌሰር በየነ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ሕብረት ፓርቲን መስርተው በክልሉ መንግሥትን የሚሞግት የፖለቲካ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በወቅቱ ገዢውን ፓርቲ በምርጫ ማሸነፍ እንደሚቻል ለሀገርም ሆነ ለደቡብ ክልል የፖለቲካ ኃይሎች በተግባር አሳይተዋል።
ማህበራዊ ፍትሕ በሀገራችን ውስጥ ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ አድርገው የሚታገሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ ሃሳባቸውን ለመተግበር እንዲያስችላቸው የርዕዮተ ዓለም መሰረቱ ማህበራዊ ፍትሕ የሆነውን የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲን በመመስረት ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ፓርቲያቸውን ከፊት ሆነው ሲመሩ ቆይተዋል። በዚህ ሁሉ የፖለቲካ ትግል ውስጥ በብሄር በሃይማኖትና ሌሎች ሰብአዊ ልዩነቶች ውግንና ሳይዙ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ የነበሩ የሰብአዊ መብት ተሟጋችም ነበሩ። በሀገራችን ለሦስት አስርት ዓመታት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን በማካሔድ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የእውቅና ኮሚቴ ተቋቁሞ በ2013 ዓ.ም የእውቅና ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በዋና ዳይሬክተርነት ተቋሙን ሲመሩ ነበር።
የሥራ ባህል
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እጅግ የተለየ የሥራ ባህልና ልማድ ያላቸው ሰው ነበሩ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ጊዜ መምህርና በአማካሪነታቸው ለተማሪዎቻቸው፣ የጥናት ወረቀቶች እርማትና ግምገማ፣ ለሳይንሳዊ ምርምር ሥራዎች በቂ ጊዜ መድበው ይሠራሉ። ምርምሮቻቸውን በጥልቀት ይፈትሻሉ፤ ማሻሻያዎችን ለተማሪዎቻቸው ይሰጣሉ። ሙሉ የሥራ ሰዓታቸውን ለመደበኛ ሥራቸው ከማዋል በተጨማሪ ቤታቸውም ወስደው ያርማሉ፤ያስተካክላሉ።
በፖለቲካው መስክ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ፕሮፌሰር በየነ ለንባብ ጊዜ ይሰጣሉ። የሀገር ቤት እና የዓለም ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታን በመመርመር እና በመተንተን የፖለቲካ አሰላለፍን ለይተው የትግል ስልትን ይቀምራሉ። በዚህ ስልት የፖለቲካ ፓርቲያቸውን ያደራጃሉ፣ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ይደራደራሉ፣ ገዢው ፓርቲን ይሞግታሉ። በማህበራዊ ሕይወት የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ። ለቤተሰባቸውም ጊዜ አላቸው። ይህን ሁሉ ሥራ መሥራት አይከብድም ወይ ተብለው በአንድ ወቅት የተጠየቁት ፕሮፌሰር በየነ ‹‹24 ሰዓት ለሁሉም ነገር በቂ ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ቤተሰብና ማህበራዊ ሕይወት
በ1970 ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለው እንደተመለሱ ትዳር የመሠረቱት ፕሮፌሰር በየነ 47 ዓመታትን ባስቆጠረው ትዳራቸው የሁለት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ አስር የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል። ከልጆቻቸው ጋር የጓደኝነት ግንኙነት የነበራቸው ፕሮፌሰር በየነ፤ ለቤተሰባቸው ጊዜ የሚሰጡ በተለይም ልጆቻቸው ትምህርትን አጥብቀው እንዲይዙ ሁሌም የሚጎተጉቱ አባት ነበሩ። በማህበራዊ ሕይወትም የሚያውቋቸውን ሰዎች ሀዘንም ሆነ ደስታ በመካፈል ረገድ ያላቸው የጊዜ ጥበት ሳይገድባቸው ሰው ጠያቂ ነበሩ። በተለይ ደግሞ ሀዘንተኛን በማጽናናት ሁልጊዜም ቢሆነ ፈጥነው የሚደርሱ የሰው ሁሉ ወዳጅ ነበሩ። በሀዲያ ሕዝብ ባህል በማህበራዊ ህይወት ተሳትፎ ለሚያደርግ፤ የተጣላ ለሚያስታርቅና ለሁሉ ሰው ወዳጅ ለሆኑ ሰዎች የሚሰጠውን ባህላዊ ሹመት «የሀንሳር ጋራድ » ባህላዊ ሹመት አግኝተዋል። «የሀንሳር ጋራድ» ማለት የሰላም ሰው የሁሉ ወዳጅ እና በማህበራዊ ህይወት ለሰው ደራሽና ጠያቂ ማለት ነው።
የግል ባህሪይና ስብዕና ፤
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ታላቅ የሳይንስ ምሁርና ጉምቱ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ምልክት መሆናቸው በአደባባይ የሚታይ መታወቂያቸው ነበር። ፕሮፌሰሩ በሙያ ሥራቸውም ሆነ በፖለቲካ ትግላቸው ወቅት ያሳዩት የነበረው ባሕሪይ፣ ኑሮአቸውን ለመምራት የመረጡበት መንገድ፣ ለሌሎች ጥለው ያለፉት ተምሳሌታዊ ህይወት በርግጥም ፕሮፌሰር በየነ የታላቅ ስብዕና ባለቤት እንደነበሩ የሚያረጋግጥ ነው።
ፕሮፌሰር በየነ ኑሮን ቀለል አድርገው መኖር የሚመርጡ፣ ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ ለትውልድና ለሀገር የሚጨነቁ ስብዕና ነበራቸው። ትሁት እና ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ የሚታወቁ ነበሩ። በፖለቲካ ትግላቸውም ሆነ በምርምር ሥራዎቻቸው ግልጽ አቋም በመያዝ ሥራን የሚሠሩ፣ ላመኑበት ነገር ዋጋ መክፈልና ኃላፊነትን መውሰድ፣ እውነትን ይዘው ፊት ለፊት የሚጋፈጡ ቁርጠኛም ነበሩ። በመርህና በምክንያታዊነት መታገል የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሌላው መለያቸው ነው። ሲቃወሙ ግልጽ እና ተጨባጭ ነጥቦችን በማንሳት እንደሆነ ሁሉ መልካም ብለው ለሚያምኑት ሥራም ምስጋና ለመስጠት ንፉግ አይደሉም።
በአንድ ወቅት “መልካም ስትሰሩ እደግፋለሁ፣ ስታጠፉ እቃወማለሁ” ብለው ሲናገሩም ተደምጠዋል። ራሳቸውን የሚገዙ፣ በማህበራዊ ሕይወት የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉና የወዳጅ ዘመዶቻቸውን ሀዘንና ደስታ የሚጋሩ ማህበራዊ ሰውም ነበሩ። በፖለቲካ ትግላቸውም ሆነ በግል ሕይወታቸው ወጥ የሆነ ማንነት የነበራቸው ተገማች ባህሪይ ያላቸው ሰው ነበሩ። ሕዝብን የሚወዱና እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ታላቅ ስብዕና ነበራቸው። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው መስከረም ስድስት ቀን 2017 ዓ.ም በተወለዱ በሰባ አምስት ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። መስከረም ዘጠኝ ቀን 2017 ዓ.ም ጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ሥርዓተ ቀብራቸው ወዳጅ ዘመድና በርካታ ወዳጆቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በእኒህ ምሁር እና ተመራማሪ፤ጉምቱ ፖለቲከኛ እና ሀገር ወዳድ ዜጋ እረፍት የተሰማውን ሀዘን መግለጽ ይወዳል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም