ሕዝባችን የባንዳዎችን ተልዕኮ ማምከን የሚያስችል ሁለንተናዊ አቅም ባለቤት ነው!

የአንድን ሀገር እና ሕዝብ ብሄራዊ ጥቅም በሁለንተናዊ መንገድ ማስከበር ከማንም በላይ የዚያች ሀገር ሕዝቦች ትልቁ ኃላፊነት ነው። ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ የመወጣት እና ያለመወጣት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ተደርጎም ይወሰዳል። ከዚህ የተነሳም ከብሔራዊ ጥቅሞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለየትኛውም ሀገር ዜጋ ከዜግነት ጋር የተያያዙ ፤ ወደማንም የማይገፋ አጀንዳዎች ሆነው ለዘመናት ቆይተዋል።

በተለይም የብሔራዊ ጥቅሞች አልፋ እና ኦሜጋ / ዋነኛ ማዕቀፍ ተደርጎ የሚወሰደው የሉዓላዊነት ጉዳይ የየትኛውም ሀገር ዜጋ ፤ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚደራደርበት ጉዳይ አይደለም። እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አንድ ማኅበረሰብ የመቆም እና ጸንቶ የመቀጠል መሠረት በመሆኑ ፤ የየትኛውም ሀገር ዜጋ እና በየትኛውም ዘመን ያለ ትውልድ በጽናት የሚቆምለት ሀገራዊ አጀንዳ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ለዚህ እውነታ ባዕድ አይደለንም ፤ ዘመናት ስለሚያስቆጥረው የሀገረመንግሥት ታሪካችን ስናወራም ፤ የምናወራው ሉዓላዊነታችንን ለማስከበር እና አጽንቶ ለትውልዶች ለማስተላለፍ ያደረግናቸው የተጋድሎ ታሪኮች ፤ ስለ ነጻነታችን እና ከዚህ ስለሚመነጨው ሉዓላዊነታችን የከፈልናቸው በድል ያሸበረቁ መስዋዕትነቶች ነው።

በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ለብሔራዊ ነጻነታችን / ሉዓላዊነታችን ዘመኑ የጠየቀውን መስዋዕትነት ያለ ማቅማማት ፤ ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር ስሜት ከፍለዋል ። በዚህም የሀገር ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ ለትውልዶች አስ ተምረዋል ። እንደሀገርም የነጻነት ፋና ወጊ የሆ ንበትን በጎ ትርክት ፈጥረውል ን አልፈዋል።

ይህ የቀደሙት አባቶቻችን ከሀገር ፍቅር የሚመነጭ የነጻነት ተጋድሎ ትርክት ፤ ዘመናትን በነጻነት መሻገር የቻለች ሀገር ባለቤት ከማድረግ ባለፈ ፤ በየዘመኑ ስለሀገሩ ነጻነት ቀናኢ የሆነ ትውልድ በማፍራት ዛሬም በሀገሩ ሉዓላዊነት የማይደራደር ፤ ሁሌም ለሀገሩ ክብር መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጀ ትውልድ እንዲኖር አስችሏል።

ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ሆኑ በየወቅቱ የሚፈጠሩ በብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ የሚሰለፉ ኃይሎች፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚፈጥሩብንን ፈተናዎች ተሻግረን ዛሬ ላይ የደረስነውም ሁሌም በሀገር ጉዳይ ለመስዋዕት ዝግጁ በሆነው ትውልድ እና በተጨባጭ በተግባር በተፈተነው የተጋድሎ የአሸናፊነት ትርክት ነው።

ይህም ሆኖ ግን የሀገር ሉዓላዊነት እና ከዚህ የሚመነጨው ብሔራዊ ክብራችን ትርጉም የማይሰጣቸው፤ ብሔራዊ ክብርን ከግል እና ከቡድን ፍላጎት አሳንሰው የሚያዩ ፤ በዚህም ለሀገር እና ለሕዝብ ፈተና የሆኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች በየዘመኑ አጋጥመውናል። የጠላቶችንን አጀንዳ ተሸካሚ በመሆንም ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል።

እነዚህ በግልጽም ይሁን በስውር ፤ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት የባንዳነት ተልዕኮ ተሸክመው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ፤ እንደሀገር የተጀመሩ የለውጥ /የመለወጥ መነቃቃቶች ስኬታማ እንዳይሆኑ አድርገዋል። የሕዝባችን በልማት የመለወጥ መሻት እውን እንዳይሆንም ፈተና ሆነው ቆይተዋል።

የኛ እንደ ሀገር መልማት እና መበልጸግ ለብሔራዊ ጥቅማቸው ፈተና አድርገው የሚወስዱ የታሪካዊ ጠላቶቻችን የአስተሳሰብ ጥላ በመሆን ፤ ሀገር ከአንድ የግጭት ምዕራፍ ወደ ሌላ የግጭት ምእራፍ እንድትጓዝ፤ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር አድርገዋል።

እነዚህ ኃይሎች ለጠላቶቻችን ዘመን ተሻጋሪ የጥፋት ተልእኮ መሣሪያ በመሆን ፤ ዛሬም ከሕዝባችን የለውጥ/የመለወጥ መነቃቃት ማግስት ጀምሮ በገዛ ሕዝባቸው የመልማት ፍላጎት ላይ በተቃርኖ ቆመው ባልተለመደ መንገድ ያለእፍረት ብሔራዊ ክብራችንን በሚፈታተን መልኩ በአደባባይ በባንዳነት ተሰልፈዋል።

በብዙ መስዋዕትነት ዛሬ ላይ የደረሰውን የሀገርን ሉዓላዊነት ጨምሮ የሕዝባችንን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ውስጥ የሚከቱ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን የጥፋት ተልዕኮ ተሸክመው ፤ ለተግባራዊነቱ ያለ ዕረፍት ሲቃትቱ ፤ በዚህ የባንዳነት ሥራቸው ከማፈር ይልቅ ሲኩራሩ እያየን ነው ።

በሕዝባችን የዘመናት በመልማት የመለወጥ ፍላጎት ላይ ብቻ ሳይሆን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ እውን ያደረጋቸውን ህልሞችን በማንቋሸሽ እና በማሳነስ ፤ ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት አብሮ እንዲቀጥል ፤ ግጭት እና ግጭት ቀስቃሽ ተልዕኮዎችን ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ሳይቀር ተቀብለው ለመስፈጸም ባላቸው አቅም ሁሉ እየሠሩ ነው።

እነዚህ በሉዓላዊነታችን እና በብሔራዊ ጥቅሞቻችን ላይ በአደባባይ በተቃርኖ በባንዳነት የቆሙ ግለሰቦች እና ቡድኖች፤ ለሕዝባችን በልማት በልጽጎ የመገኘት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ፈተና ከመሆን ባለፈ የሚያመጡት ነገር አይኖርም ። ምክንያቱም ትውልዱ እንደቀደሙት አባቶቹ የነዚህን ባንዳዎች ተልዕኮ ለማምከን የሚያስችል የሁለንተናዊ አቅም ባለቤት ነውና!

አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You