የያዝነው የመስከረም ወር ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ልዩ ትርጉም አለው። የአዲስ ዘመን መለወጫ በሆነው በዚህ ወር በርካታ የቱሪዝም መስህብ ሁነቶች ይካሄዳሉ። እነዚህ ሁነቶች ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስነስርአቶች ሲሆኑ ፣ በመላው ሀገሪቱ በሚያሰኝ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ይከናወናሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና ምእመኖቿ የሚያከብሩት የመስቀል ደመራ ክብረ በዓል አንዱ ሲሆን፣ ይህ ታላቅ ሁነትና አከባበር በዩኔስኮ የማይዳሰስ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ በሚል የተመዘገበ ነው። ከዚህ ክብረ በዓል በተጨማሪ በኦሮሞ ብሄር ዘንድ በደማቅ ስነስርአት የሚከበረው የኢሬቻ በአልም እንዲሁ በወርሃ መስከረም ሰፊ ቁጥር ያለው የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎች የሚታደሙበት የምስጋና በዓል ነው።
ከእነዚህ ሁለት ዓመታዊ ክብረ በዓላት ባሻገር ቀድሞ ደቡብ በመባል በሚታወቀው አሁን በተለያዩ ክልሎች በአዲስ በተዋቀረው የሀገሪቱ ክፍልም እንዲሁ የማህበረሰቦችን ባህል፣ ወግ፣ እሴት፣ ሀገር በቀል እውቀት የሚያሳዩ የአዲስ ዘመን መለወጫ ሁነቶች ይካሄዳሉ። ሁነቶቹ ለውጪም ሆነ ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ልዩ ትውስታን የሚያጭሩ፣ እውቀትን የሚያስጨብጡና የሰው ልጆችን ማቀራረብ የሚያስችል ጥልቅ ጥበባዊ እሴት የያዙ ሆነው እናገኛቸዋለን። በማይዳሰስ የመስህብ ሀብት ውስጥ የሚመደቡት በዓላቱ ኢትዮጵያውያን በመስከረም ወር የሚያከብሯቸው ታላላቅ በዓላት ናቸው።
መስከረም ለሀገሪቱ ቱሪዝም ከዚህም ያለፈ ትርጉም አለው። በዚህ ወር የዓለም ቱሪዝም ቀን ይከበራል። ለተፈጥሮ፣ ለባህል፣ ለታሪክ፣ ለአርኪዮሎጂ፣ ለቅርስ እና መሰል እሴቶች መጠበቅና ውግንናን ለማሳየት ወሩ በልዩ ሁኔታ ለቱሪዝም ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት እንዲሆን ተሰይሞበታል።
ለሀገሪቱ የተለያዩ ማህበረሰቦች እሴቶች ከሆኑት ኢትዮጵያዊ ታላላቅ ሁነቶች የሚካሄዱ ከመሆናቸው ባሻገርም የተለያዩ ቱሪዝም ነክ ሁነቶች በወርሀ መስከረም ይካሄዳሉ። በያዝነው 2017 ዓ.ም ተመሳሳይ ሁነቶች ተካሂደዋል። ከእነዚህ መካከል የቱሪዝም ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያካሄደው አውደ ርዕይ ሲሆን፣ በዚህም የኢጋድ ሀገራት ተሳትፈውበታል። ሁነቱ በየዓመቱም ታስቧል፤ ቀስ በቀስም ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች ጭምር እንዲካተቱበት ለማድረግ ታቅዷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የመስህብ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ፣ አዳዲስ መዳረሻዎችን ይፋ በማድረግ እንዲሁም ዘርፉ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማፅደቅ እየሰራ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህን ተግባራት የሚያጠናክሩ ስራዎችም በዚህ በያዝነው የ2017 ዓ.ም ወርሀ መስከረም እየተካሄዱ ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይፋ ያደረገው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት (TSA) አውደ ርእይ አንዱ ነው፡፡ ይህም በቱሪዝም ዘርፉ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚያስችል ሳይንሳዊ ስልት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት አውደ ርእዩን ይፋ ከማድረግ ባሻገር የኢጋድ ሀገራት የዘላቂ የቱሪዝም ዘርፍ ልማት እቅድ የጸደቀበት ሁነትም ተካሂዷል።
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የመስህብ ሀብቶች እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አስተዋጿቸውን (በያዝነው የመስከረም ወር የሚከበሩትን የማይዳሰሱ ባህላዊ ሀብቶችን ጨምሮ) በሚመለከት ትክክለኛ መረጃ ይሰጣል። የቲኤስ ኤው የማስጀመሪያ መርሀ ግብርም ደማቅ ክብረ በዓላትን በሚያስተናግደው እንዲሁም የዓለም የቱሪዝም ቀን በሚከበርበት ወር ማስጀመሪያ ላይ ነው ይፋ የተደረገው።
በዚህ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በተደረገ ይፋ የማድረጊያ ሥነሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ፤ ኢትዮጵያ በታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ሀብቶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች የበለጸገች ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መሆን በዘርፉ ያለውን የተደራጀ መረጃ ውስንነት መፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን የአብሮነት መሰረታቸው፣ ባህላቸውና ወጋቸው የዓለም ጎብኚዎችን ትኩረት በመሳብ ለዓመታት ዘልቋል›› ያሉት አምባሳደሯ፤ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም በቱሪዝም መሰረተ ልማት ማበልፀግ ባለመቻሏ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ እንደቆየች አመልክተዋል።
ከለውጡ በኋላ መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ቱሪዝምን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን በመግለፅም፣ ቱሪዝም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መሰረታዊ በሆነ መንገድ መቀየር የሚችል አቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ቱሪዝም የውጭ ምንዛሪን በማሳደግና የሥራ ዕድል በመፍጠር የጎላ አበርክቶ አለው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመን እየተሰራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ለቱሪስቶች የተደራጀ መረጃ በመስጠት የተሳለጠ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ፤ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም በመስከረም ወር ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ማድረጓን አስመልክቶ ስለ ጉዳዩ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል። የዝግጅት ክፍላችንም የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ምንነት እንዲሁም የሚሰጠውን ጠቀሜታ በሚከተለው መልኩ አቅርቦታል።
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት (TSA)
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንቱ መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም በዓድዋ ሙዚየም ይፋ ተደርጓል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎች እና ሀብቶች የመጠበቅ፣ የማልማትና የማስተዋወቅ ተልእኮ እንደተሰጠው ይገልጻሉ፡፡ ይህንን አስመልክቶም መስሪያ ቤቱ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በቅጡ ተገንዝቦ ለመተንተን እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ቀረጻ እና ስልታዊ የእቅድ ዝግጅትን እውን ለማድረግ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት (TSA) ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱን ይናገራሉ፡፡
‹‹የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መደረጉ ኢትዮጵያን የቱሪዝም ሳተላይት አካውንትን በስኬት አጠናቀው ተግባራዊ ካደረጉ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል›› የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ፤ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ምንድነው?
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የተመድ /ዩኤን/ ቱሪዝም ተቋም፣ ከተመድ ስታቲስቲክስ ክፍል፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የስታቲስቲክስ ማእቀፍ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ስለሺ፤ የሳተላይት አካውንቱ ቱሪዝም በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አዎንታዊ ተጽእኖ ወጥነት ባለው ሁኔታ የሚለካ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ በጥልቀት እንደሚያሳይ ያብራራሉ፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንቱ ማስረጃን መሰረት ላደረገ ፖሊሲ ቀረፃ፣ ውሳኔ አሰጣጥ እና ስልታዊ እቅድን እውን ለማድረግ የሚያስችል የመረጃ ምንጭ ሲሆን፣ ይህም ከቱሪዝም ዘርፍ የሚያገኘውን ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው፡፡
የስታቲስቲክስ ማእቀፉ ቱሪዝም ለጠቅላላ አመታዊ ምርት (GDP) የሚያበረክተውን ቀጥተኛ ድርሻ፣ ዘርፉ ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች አንጻር ያለውን አንጻራዊ ግዝፈት (መጠን) ፣ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ግብይት መጠንን እንዲሁም መንግሥታት ከቱሪዝም ክንውኖች የሚያገኙትን የገቢ መጠን ለመረዳት የሚያስችል እንደሆነም አቶ ስለሺ ይናገራሉ። ዘርፉ ለስራ ፈጠራ እና ለኢንቨስትመንት የሚያደርገውን አስተዋጽኦም ለማወቅ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ለምን አስፈለገ?
‹‹ኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በትክክል ለመለካት የሚያስችል ጠንካራ የስታቲስቲክስ ማእቀፍ አልነበራትም›› የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህ የመረጃ ክፍተት ሀገሪቱ ቱሪዝም የሚያስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አሟጣ መጠቀም እንዳትችል አድርጓታል ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍን የተመለከተ የመረጃ ውስንነት መኖሩን በመግለፅም፤ በዋናነት ወደ ሀገር የሚገቡ የቱሪስቶችን ቁጥር እና ጎብኚዎች ለዳሰሳ ጥናት የሚሰጡትን ምላሽ መሰረት ያደረገ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
ካሁን ቀደም የነበረው የተበታተነ የመረጃ አሰባሰብ ሂደት አመርቂ የፖሊሲ ቀረጻ እና አተገባበር እንዳይኖረን ምክንያት ሆኖ ቆይቷል የሚሉት አቶ ስለሺ ግርማ፤ ለዚህ ተገዳሮት እልባት ለመስጠት ቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን /ኢሲኤ/ ቴክኒካል ድጋፍ በመጠየቅ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ማዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
ዝግጅቱ መቼ ተጀመረ?
የቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው ያደረሱን መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ዝግጅት ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ በ2023 የካቲት ወር ነው የተጀመረው፡፡ በቅርቡ ይፋ በተደረገበት ሥነሥርዓት ላይም የኢጋድ ሀገራት ዘላቂ ቱሪዝም ልማትን የተመለከተ ዝግጅት ተደርጓል።
ኢጋድ እና አባል ሀገራቱ ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን በቀጣናው እውን ለማድረግ የሚያስችላቸው ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላንም ተዋውቋል፡፡ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢጋድ ሴክሬታሪያት እና ዩኤን ኢሲኤ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የዘላቂ ቱሪዝም ማስተር ፕላኑ መስከረም 9 ቀን መርሀ ግብሩ ተከናውኗል፡፡
የኢጋድ ዘላቂ ቱሪዝም ማስተር ፕላን (STMP) የኢጋድ አባል ሀገራት ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን ለማረጋገጥ በጋራ ያዘጋጁት የ10 ዓመት ማስተር ፕላን ነው፡፡ ማስተር ፕላኑ የቀጣናው ሀገራት የተቀናጁ እና ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻዎች መሆን እንዲችሉ የሚረዳ የቱሪዝም ልማት ማእቀፍ ነው፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ይህንን ርእሰ ጉዳይ በቀጣይ እትም የሚመለከተው ይሆናል።
እንደ መውጫ
በመግቢያችን ላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርነው ኢትዮጵያ የበርካታ መስህቦች ባለቤት ነች። በመስከረም ወር የሚካሄዱትን ቱሪዝም ነክ ሁነቶች ብቻ ነጥለን ብንመለከት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ጉልህ የሆነ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ በርካታ መስህቦችን መጥቀስ እንችላለን።
ከተፈጥሮ ሀብት እስከ ታሪካዊ ቦታ፣ ከዱር እንስሳት መኖሪያ ፓርክና ጥብቅ ቦታዎች እስከ አርኪዮሎጂካል ስፍራ አያሌ ለጉብኝት ምቹ የሆኑ ሀብቶችን መዘርዘር እንችላለን። ይሁን እንጂ እነዚህን የመስህብ ሀብቶች በትክክለኛው መረጃ አደራጅቶ፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውንና ጠቀሜታቸውን ለይቶ ለመተንተን የሚያስችል የመረጃ ሥርዓት አልነበረም። በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ አሀዛዊ መረጃዎች ትክክለኛውን የኢትዮጵያን የቱሪዝም እድገት የሚለኩ፣ ክፍተቶችን የሚለዩ፣ ቱሪዝም በሀገሪቱ ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ የሚያሳዩ አልነበሩም።
ከዚህ የተነሳ ከታችኛው ማህበረሰብ ጀምሮ እስከ ሀገራዊ ጥቅል ጉዳይ የቱሪዝም ድርሻንና ተፅእኖን በትክክል መለየት ሳይቻል ቆይቷል። የመገናኛ ብዙኃንም እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎችን ይፋ ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ይህ የሆነው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንትን የመሰለ ሳይንሳዊ መለኪያ ተግባራዊ ባለመደረጉ ነው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሁን ይህንን ችግር ይፈታልኛል ያለውን ማእቀፍ በአዲስ ዘመን መባቻ የመስከረም መጀመሪያ ይፋ አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን ነግሮናል። በቀጣይ ተግባር ላይ የሚውለውን ይህንን ማእቀፍ ተንተርሰው የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችንም የዝግጅት ክፍላችን በመከታተል የሚያቀርብ ይሆናል።
ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም