እጣ ፈንታ፣ ፍርቱና ፣የአርባ ቀን ዕድል ፣…. የመሳሰሉት አባባሎች ሰው በህይወቱ አንዳች ነገር ሲያገኘው እና ሲያገኝ የሚባሉ አገላለጾች ናቸው። በተፈቀደልን የህይወት ጉዞ ውስጥ “ዕድላችን” አንዴ ሲቃና አንዴ ሲጣመም እናሳልፋለን፤በሌሎችም ላይ ይሄንኑ አይተናልም ።
በየትኛውም የህይወት ጫፍ ካስተዋልን ግን ትምህርትም አስተማሪም የሚሆን ነገር አለ። ለዛሬ ከህይወታቸው እንማር ዘንድ ብዙ ውጣ ውረድ ያሳለፉ እንግዳ ጋበዝን። በአሁን ወቅት በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ ይገኛሉ።የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› እንግዳችን አቶ ተስፋዬ ከበደ ናቸው። መልካም ንባብ!
የስራ ላይ ቆይታን በትውስታ
ለረዥም ዓመታት በባህር ሐይል በውትድርና ዓለም አሳልፈዋል። በውትድርና ወቅትም ተማርከው ለአንድ ዓመት ከአምስት ወር በአስመራ እስር ቤት ቆይተዋል። ከ1983 ዓመተ ምህረት የመንግስት ለውጥ ከተደረገ በኋላ ነጻ ወጥተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
አቶ ተስፋዬ ከባህር ኃይል የሙዚቃ ቡድን መሪነት እስከ ቼሻየር ኢትዮጵያ በተለያዩ የስራ መስኮች በተለያየ የስልጣን እርከን ላይም አገራቸውንና ህዝባቸውን አገልግለዋል።በአጋጠማቸው የጋንግሪን በሽታ እግራቸው ተቆርጦ በዊልቸው እየተንቀሳቀሱ እንኳን ለቁጥር የሚታክቱ የስዕል እና የጽሑፍ ስራዎችን ሰርተዋል። በበሽታ ምክንያት እግራቸው ቢቆረጥም መንፈሰ ጠንካራ፣ የጽናት እና የአሸናፊነት ምሳሌ ናቸውና እጅ አልሰጡም።
ልጅነት እና ትምህርት
የተወለዱት በአዲስ አበባ ብዙ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች ከፈለቁበት ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነው።አቶ ተስፋዬ ከበደ በ1949 ዓ.ም ሐምሌ 17 ቀን ይህችን ምድር ተቀላቀሉ። በልጅነታቸው ሳቂታ እና ቀልደኛ የጨዋታ አድማቂ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ በልጅነታቸው ያልወጡት ዳገት ያልተጫወቱት ጨዋታ እንደሌለ ይናገራሉ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ወይዘሮ ዘርፈሽዋል የህዝብ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ ስደተኛ ክፍል ተምረዋል ።በመቀጠልም ከሰባተኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ዑራኤል መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።አስረኛን ክፍል ደግሞ በቀድሞ ዳግማዊ ምንልክ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
የሀሳብ ጥንስስ
የአስረኛ ክፍል ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የቀድሞ ዳግማዊ ሚንልክ ትምህርት ቤት በመሆኑ የሚመላለሱትም ባህር ኃይል ዋናው ቢሮ በሚገኝበት አካባቢ ነበር።
ታዲያ የያኔው ወጣት ተማሪ ተስፋዬ በባህር ኃይል መስሪያ ቤት በኩል ሲመላለስ የሰራተኞቹ መለዮ እና የደንብ ልብስ ልቡን ሳበው፤ ወታደራዊ ስሜት በውስጡ ቀረ። እንግዲህ ይህንን ዘርፍ ለመቀላቀል ማስታወቂያ ሲወጣ መመዝገብና መወዳደር ያስፈልጋልና ሀሳቡና ምኞቱን በልቡ ይዞ ማስታወቂያውን በጉጉት ሲጠባበቅ ያሰበው ደረሰና ተመዘገበ። እንደተመኘውም ብቻ አልቀረም በ1967 ዓ.ም ፈተናው ተፈተነ ፤ ከውስጥ በመነጨ ፍላጎት የተቀሰቀሰ ነውና ፈተናውን በጥሩ ውጤት አልፎ ተቋሙን ተቀላቀለ።
ባህር ሀይል ከየት ወደየት
አቶ ተስፋዬ ዛሬም ስለባህር ሐይል ተርከው አይጠገቡም፤ በየጭውውታችን መሃል ባህር ሐይልን ሳያነሱ አይሆንላቸውም።እናም ባህር ሐይልን ከምስረታ ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ያለው ታሪኩን ሲተርኩ በቁጭት እና የማይመለሰውን ጊዜ በመመኘት ነው። አቶ ተስፋዬ ስለባህር ሀይል የሚያውቁትን እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ። (የተጻፉት ቀኖች በሙሉ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መሆኑን ልብ ይባል)። የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በ1955 ተመስርቶ እስከ 1996 ቆይቷል።
3ሺ500 የሰው ኃይል 26 መርከቦች ነበሩት። የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አካል ነበረ። ከ1955 እስከ 1990 ዋና መስሪያ ቤቱ ምጽዋ የነበረ ሲሆን ከ1990 እስከ 1996 አዲስ አበባ ተዘዋውሯል። የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የ መ ጀ መ ሪ ያ ው አዛዥ ማለትም ከ1955 እስከ 1974 ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ። እአአ ከ1958 እስከ 1974 ድረስ ምክትል አዛዡ ሪር አድሚራል እስክንድር ደስታ የሚባሉ ሰው ናቸው።በንጉሱ ዘመን ባሕር ኃይሉ የራሱ የሆኑ ኡኤችአይ ኢሮኩይስ እና ሚ8 ሚ14 የተባሉ የጦር ሄሊኮፕተሮች እንደነበሩት አቶ ተስፋዬ ያስታውሳሉ።
አቶ ተስፋዬ ቀጠሉ። የንጉሰ ነገሥቱ ባሕር ኃይል የተመሰረተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1950 ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ሲወሰን ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ጠረፍና ወደብ በማግኘቷ ነው። በ1955 የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባሕር ኃይል የመጀመሪያ ጦር ሰፈሩን (ቤዙን) ምጽዋ ላይ አቋቋመ።በ1960ዎቹ መጀመሪያ ወርክ ሾፓችና የሙሉ ባሕር ኃይል አቅም እንዲኖረው ግንባታቸው በምጽዋ ተጀመረ።
በ1958 ባሕር ኃይሉ ሙሉ በሙሉ ራሱን ችሎ ተቋቋመ። እንደ ምድር ጦርና አየር ኃይል ሁሉ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዞር ሹም ስር ሆነ።የባሕር ኃይሉ ምክትል አዛዥ ቢሯቸው በአዲስ አበባ ሲሆን የጠረፍ ባሕር ኃይል ሆኖ ቀይ ባሕርን እንዲቃኝ እንዲጠብቅ ነው የተቋቋመው።
ትምሕርትና ስልጠናን በተመለከተ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሠራዊት አባላት በአለማችን እጅግ በጣም ምርጥ ከሚባሉት ባሕር ኃይሎች ውስጥ ነበሩ። ኢትዮጵያ ኤርትራን በፌዴሬሽን ከመቀላቀሏ በፊትም ቢሆን የእንግሊዝ ባሕር ኃይል (ሮያል ኔቪ) ኢትዮጵያውያንን ምጽዋ በሚገኘው ቤዙ ወስዶ በሚገባ ተምረዋል። በ1956 በአስመራ ከተማ የባሕር ኃይል ኮሌጅ ተመሰረተ።
በዚህ ኮሌጅ ኢትዮጵያውያን እጩ መኮንኖች ለ52 ወራት ከፍተኛ የባሕር ኃይል ትምህርት ተምረው በመኮንንት ይመረቃሉ። በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ በአማካይ ከ30 እስከ 40 ተማሪዎች ይማሩ የነበረ ሲሆን ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በናቫል ከሚሽንነትና በባችለር ኦፍ ሳይንስ ዲግሪ ይመረቃሉ። በ1957 ደግሞ በምጽዋ የባሕር ኃይል በታች ሹሞች ማስልጠኛ ተከፈተ። ከ1950 በኃላ እስከ 1960 ድረስ የባሕር ጠለቆች (ፍሮግማን ዳይቪንግ) እና የልዩ ኮምንዶ ክፍል፤ እንዲሁም የባሕር ኃይል ወታደሮች (የባሕረኞች) ማሰልጠኛ ተመስርቶአል።
ጃንሆይ የኖርዌጅያን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ባሕር ኃይል መኮንኖች አዲስ የሚቋቋመውን የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል እንዲረዱና እንዲያደራጁ ሾመዋል። በአብዛኛው ስልጠናና ትምህርቱን የሚሰጡት በአማካሪነት ያገለግሉ የነበሩት ጡረታ የወጡ የእንግሊዝ ባሕር ኃይል(ሮያል ኔቪ) መኮንኖች ነበሩ።
ጥቂት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መኮንኖች ሊቮርኖ በሚገኘው የጣሊያን ባሕር ኃይል አካዳሚ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ሌሎች የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መኮንኖች ደግሞ በአሜሪካን ባሕር ኃይል አካዳሚ ሜሪላንድ ሚኒያፖሊስ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የአሜሪካን ባሕር ኃይል ንብረት የሆነችው ሲ ፕሌን ቴንደር ዩኤስ ኤስ (ኦርካ ኤቪፒ 49 ከሀውተን ዋሽንግተን የካቲት 6 /1944 የተሰራች ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የማስተማርያና የማስልጠኛ መርከብ ሆና ከ1964 እስከ 1993 አገልግላለች።ትልቋም መርከብ ነበረች።እስከመጨረሻው ድረስ ባሕር ኃይላችን በተለያየ ኃላፊነትና የስራ መደብ ውስጥ የነበሩ በእጅጉ የተማሩ በአለም አቀፍ ደረጃ የባሕረኛ ሰፊ እውቀት በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ 3ሺ500 ባሕረኞች ነበሩት።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የቅኝት ጀልባዎችን፣ ቶርፔዶ ጀልባዎችን እና የጦር መርከቦችን መጠነኛ ደረጃ ያላቸውን ከውሃ በታች የሚሄዱትን ጭምር ከአሜሪካና ከሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ተላልፈውለት የራሱ ንብረት ሆነው ይጠቀምባቸው ነበር።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የመጀመሪያዋ መርከብ የቀድሞው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ፒሲ 1604 መደብ ሰብ መሪን ቼሰር የቀድሞዋ ዩኤስ ኤስ ፒሲ 1616 መርከብ ስትሆን በጥር 2 ቀን1957 ለኢትዮጵያ በብድር ገንዘብ የተላለፈች ነበረች። በኋላም መርከቧ በኢትዮጵያዊው አርበኛ በዘርአይ ደረስ ስም ተሰየመች። በ1962 አሜሪካ ሲ ፕሌን ቴንደር ኦርካን የተባለችውን መርከብ ለኢትዮጵያ አስተላለፈች። መርከቧ ኢትዮጵያ ተብላ ተሰየመች። በ31 አመታት አገልግሎቷ ውስጥ የኢትዮጵያ የማሰልጠኛና ትልቋም መርከብ ነበረች።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አነስተኛ የባሕር ኃይል አየር ኃይል አቋቋመ። 6 ስት ዩኤች 1 ኢሮኩይስ ሄሊኮፕተሮች የነበረው ሲሆን የሚንቀሳቀሱት አስመራ ከሚገኘው የባሕር ኃይል አየር ጣቢያ ነበር። ባሕር ኃይላችን አራት የጦር ሰፈሮች ነበሩት።
ምጽዋ የባሕር ኃይሉ ዋና መምሪያና የባሕረኞች ማሰልጠኛ፤ የባሕር ኃይሉ አየር ኃይል ጣቢያና የባሕር ኃይል አካዳሚው (ኔቪ አካዳሚ) አስመራ፤ አሰብ የባሕር ኃይሉ ጣቢያና የበታች ሹማምንት ማሰልጠኛ እንዲሁም የጥገና ቦታ፤ በቀይ ባሕር ዳህላክ ደሴቶች የባሕር ኃይሉና የመገናኛ ኮሚኒኬሽን ጣቢያም ይገኝበት ነበር።
ንጉሡ ከስልጣን ከወረዱ በኃላ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በሶቭየት ሕብረት ባሕር ኃይሎች ሞዴልና አደረጃጀት መስራቱን ቀጠለ። የተወሰኑ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መኮንኖች ሶቭየት ሕብረት ባሕር ኃይል አካዳሚ ሌኒን ግራድና እንዲሁም ባኩ ከተማ የባሕር ኃይል ትምህርት ተከታትለዋል። ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ባሕረኞች የባሕር ኃይል ትምህርት የሚወስዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር።
ሶቭየት ሕብረት በሶማሊያና ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ጎን በመሰለፏ ከሶማሊያ እንድትወጣ ሲደረግ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት አሰብና ዳህላክ ላይ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር አቋቋመች።የሶቭየት ሕብረት ባሕር ኃይል አውሮፕላኖችን አስመራ አየር ማረፊያ ማከማቸት ጀመረች። የሶቭየት ባሕር ኃይል መኮንኖች በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ የአስልጣኝነት ቦታዎችን ያዙ። አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የጦር መሳሪያ እርዳታ በ1977 (እኤአ) ስታቋርጥ ባሕር ኃይላችን የሚታጠቃቸው አዳዲስ መሳሪያዎች በሶቭየት ሕብረት መሳሪያዎች ተተኩ።
የቀድሞዎቹ እንዳሉ ሆነው።ሶቭየት ሰራሽ የቅኝት ጀልባዎችና ሚሳኤል የታጠቁ ጀልባዎች የቀድሞዎቹን የአሜሪካና የአውሮፓ መርከቦች መተካት ጀመሩ። በ1991(እኤአ) የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሁለት ፍሪጌቶች (ተዋጊ መርከቦች) ፤8 ሚሳኤል ክራፍቶች(ተዋጊ መርከቦች)፤ 6የቶርፔዶ ክራፋቶች(ተዋጊ መርከቦች) ፤ 6 የቅኝት ጀልባዎች፤ 2 አምፊቢየስ ክራፍቶች እንዲሁም ሁለት የድጋፍና የማሰልጠኛ ክራፍቶች አብዛኛዎቹ የሶቭየት ስሪት የሆኑ ባለቤት ሆነ።
ደርግ ስልጣን ከያዘ በኃላ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አየር ኃይል ንብረቶች የነበሩት 6ስቱ ዩኤች 1 የተባሉት ሄሊኮፕተሮች ወደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል እንዲተላለፉ ተደረገ። ከንጉሱ በኃላም ባሕር ኃይሉ በኔቶ ሪፖርት መሰረት 2 ሶቭየት ሰራሽ የሆኑ ሚሊሚ 14 የተባሉ ሄሊኮፕተሮችን አግኝቷል። ባሕር ኃይሉ የጠረፍ ጥበቃ ብርጌድ የነበረው ሲሆን ይህም ሁለት በመኪና ላይ የተጠመዱ ፒ 15 ተርማይት ወይንም ኤስኤስ 3 በኔቶ አጠራር የጠረፍ ጥበቃ ጸረ መርከብ ክሩስ ሚሳኤል አስወንጫፊዎችን የታጠቀ ነበር።
መርከቦቻችንም ቀን ጥሎአቸው እንደ ሰው ወደ ጅቡቲ የመንና ሳኡዲአረቢያ ተሰደዋል። የመን የሄዱት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መርከቦች የመን እንዲወጡ ስላደረገች 16 ያህሉ ጅቡቲ ገብተው ነበር።በኃላ ላይ ጅቡቲ መርከቦቹ የቆሙበት ኪራይ አልተከፈለኝም ሽጩ እወስዳለሁ በሚል መርከቦቹን ለጨረታ አቀረበች።
ኤርትራ አራቱን ስትገዛ ሌሎቹን ጅቡቲ ሸጠች። ይሄንንም አንረሳም።ለካስ ቀን ሲጎል ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ሀገርም ሀገርን ይከዳል ጃል !! ለታሪክና ለትውልድ የቀረው ብቸኛው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መርከብ የቅኝት ጀልባ የነበረው ጊቢ 21 ተብላ የምትጠራዋ ስትሆን በኢትዮጵያ ሰራዊት ወደ ጣና ሐይቅ ተጭና ተወስዳ ዛሬ ጣና ሐይቅ ላይ ትገኛለች።
በ2009 ከተከሰተው ከዚያ ሁሉ ጦርነት፤የመርከቦች ስደትና ሽያጭ ውስጥ ተርፋ ያለች ብቸኛዋ የኢትዮጵያ ሠራዊት መርከብ ነች። እንግዲህ ይሄ ሁሉ ሀገራዊ ቀውስ ትርምስና ጦርነት ያስከተለው ውጤት ሀገራችንንም ባህር ኃይል ፤ወደብ አልባ አደረጋት።ዛሬ ይሄ ቁጭት የሚሰማው አመራር ተፈጠረ። ደስ ይላል። ደግሞ እጠብቃለው ባህር ሀይል ተመልሶ እንደማየው ተስፋ አለኝ።
“እኔም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1967 በዚህ ታሪኩም ስራውም ሰፊ ወደ ሆነው ተቋም ተቀላቀልኩኝ። የሙዚቃ አባል ቀጥሎም ይህንኑ ቡድን በመምራት እና በተለያዩ ግዳጅ በመሰለፍ ለዚህ ለተከበረው አገር አገልግሎቴን ሰጥቻለሁ” ይላሉ።
አቶ ተስፋዬ “እኔም ሆንኩ ሌሎች የባህር ሀይል አባላት ያለን መተሳሰብ፣መዋደድ፣ታናሽ ለታላቁ የሚታዘዝበት መንገድ አለቆቻችንን የምናከብረበት ሁኔታ እጅግ ድንቅ አሁን ላለው ማንኛው ሲቪል ሆነ ወታደር ምሳሌ የሚሆን ነው። ድሮ ቀረ ከሚሉት ወገን አይደለሁም ፤ይህ የባህር ሐይል ልምድ ግን ሊወሰድ የሚገባው እንደቤተሰብ የሚኖርበት ብሔር፣ ሀይማኖት ለወዳጅነት መስፈርት የማይሆኑበት ተቋም ነበር።”
ታዲያ አዲስ አበባ ሲመጡ ነገሩ ሁሉ ለእሳቸው አዲስ ነበር። እናም ወደ ባህር ዳር ለስራ በሄዱበት ጋንግሪን በሽታ ታመው እግራቸው ተቆረጠ።
ፈታኝ ጊዜ
ከምርኮ በኋላ ወደ አገራቸው የተመለሱት አቶ ተስፋዬ ቼሻር ሰርቪስ ኢትዮዽያ በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት እየሰሩ እህል ውሃ ከውሃ አጣጫቻውን ጋር አገናኛቸው። በ1991 ዓ. ም ከወይዘሮ ገነት ጸጋዬ ጋር ጋብቻቸውን ፈጸሙ። ከአንድ ዓመት በኋላ ከባለቤታቸው የበኩር ልጃቸውን አገኙ፤ ደስታው ግን አልቀጠለም፤ ወይዘሮ ገነት ከሶስት ዓመት በኃላ በሞት ተለዩዋቸው። እርሳቸውም ከሚሰሩበት መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በጡረታ ተሸኙ።
እሳቸው ይሰሩበት የነበረው ቼሻየር ሰርቪስ ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም በተለያየ ቁሳቁስ መቄዶንያን ይረዳ ነበርና መቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን እንዴት አድርጎ እንደሚደግፍ ያውቃል። ስለዚህ አቶ ተስፋዬም እዛ ቢገቡ ለድርጅቱም ይጠቅማሉ፤ ለራሳቸውም ይጠቀማሉ ብሎ በማሰብ ከመቄዶንያ እንዲቀላቀሉ አግዟቸዋል። አሁንም እንደታሰበው ራሳቸውም ተጠቅመው ድርጅቱንም በማገልገል ላይ ናቸው።
“አርት ቴራፒ”
አቶ ተስፋዬ መቄዶንያን ሲቀላቀሉ ባላቸው ክህሎት አንዳንድ ስራ ለመስራት ሀሳብ ነበራቸው። ይህንንም ሀሳባቸውን እውን ለማድረግ የስዕል ስራ የሚሰሩበትን ብሩሽ እና ቀለም ይዘው ጎራ አሉ። እየተደገፉ እንዲደግፉ የሚያስቻላቸውን ተግባር እንዲከውኑ ያነሳሳቸው በመቄዶንያ ተደራጅቶ ያገኙት “የአርት ጋለሪ” ነበር። የአባቷን ስም የዘነጉት ፍሬህይወት በምትባል ትውልደ ኢትዮጵያዊት ዲያስፖራ የአርት ጋለሪው እንደተቋቋመ ነግረውናል።
“ለእኔ ይህ የተመቻቸ እድል ነው” የሚሉት አቶ ተስፋዬ ለአእምሮ ህሙማንም ሆነ በተለያየ የነርቭ በሽታ ለተጠቁ ተረጂዎች “አርት ቴራፒ” ትልቅ መፍትሄ ነው። እናም ብዙዎች እየታከሙበት መሆኑን ነግረውናል። አረጋውያኑ በስዕል ክፍሉ ”አርት ጋለሪ“ ውስጥ ባለው ሸራ፣ ቀለም፣ ብሩሽ ተጠቅመው ስዕል በመሳል ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። የስዕል ስሜትና ችሎታ ያላቸውም ይሄንኑ ስሜታቸውን ይወጣሉ።
ችሎታው የሌላችው ደግሞ ሌሎች በሰሩት ስዕል ይዝናናሉ። በአርት ጋለሪ ክፍሉ ውስጥም የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምስል ተሰርቶ ተመልክተናል።ሌሎችም ስዕሎች በክፍሉ ውስጥ ይታያሉ። የደነዘዘ አእምሮን የተጨበጡ ጣቶችን አፍታቶ ሰውነትን በማዝናናት የሚያክም መድሀኒት መሆኑን ካየነው ተነስተን መመስከር አይከብድም ።
አሁን ግን አቶ ተስፋዬ ህመም ሳይገድባቸው ሌላ እጅግ ትልቅ የሥራ ኃላፊነትን እየተወጡ ነው። በማእከሉ የአርት ቴራፒ ክፍል ተጠሪ በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው። በተጣለባቸው ወገንን የመርዳት ሃለፊነት ለራሳቸውም እየተደገፉ ሌሎችን መደገፋቸውን ቀጥለዋል። ‹‹አሁንም አገለግላለሁ፤ በዚህ ማዕከል መሳተፍ ሀገርን ማገልገል ነው።
ሀገርን ሲያገለግሉ ኖረው ዛሬ በእርጅና በድካም፣ በሕመም፣ በማጣት ለመረዳት በማእከሉ የገቡትን ማገልግል ያስደስታል። ብዙዎቹ ትናንት ቤተሰብ ነበሯቸው፣ እኔ ነኝ ያሉ ጉልበታም፣ እውቀት ያላቸው እና ባለሙያ፣የሀገር ባለውለተኛ ነበሩ፤ እነሱን በማገልገል እበረታለሁ።›› ብለውናል። ያላቸውንም ቀሪ የሕይወት ዘመን ለዚህ በጎ ሥራ መስጠታቸውን ይገልጻሉ።
አቶ ተስፋዬ አንድ በሕይወታቸው የተረዱት ታላቅ ነገር አለ፤ ‹‹የአካል መቆረጥ ወይም ማጣት የሕይወት ፍጻሜ አለመሆኑን ተረድቻለሁ።›› ይላሉ። የአካላቸው መቆረጥ ከፈጠረባቸው የስነልቦና ቀውስ ምን እሆናለሁ ከሚለው ጭንቀት ወጥተው በከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ ይገኛሉ ።‹‹ትናንት ሞቼ ነበር። ዛሬ ከዚያ ተነሥቼ አሁን ባለሁበት ደረጃ ከደረስኩ አረጋውያንን በማገዝና መቄዶንያን በማገልገል እኖራለሁ፤ ይህ ለእኔ አዲስ ሕይወት ነው፤ ከዚህ በላይም ደስታ ሊኖረኝ ወይም ላገኝ አልችልም።›› ይላሉ።
ምስክርነት
ሊዲንግ ሲማን የሺ በቀለ ይባላሉ። የኢትዮጵያ ባህር ሐይል የ1977 ዓ.ም ቅጥር ናቸው። ብሊንክ ሲማን የሺ እንዳሉን በባህር ሐይል ካገለገልን በኋላ ብዙ ውጣ ውረድ አይረሴ የደስታም የሀዘንም ጊዜ አሳልፈን፣ ተሰደን፣ ለአገራችን በቅተናል።አሁን የቀድሞ ባህረ ሐይል አባላት በመሰብሰብ “ኑር” የሚባል ማህበር አቋቁመናል።ተስፋዬን የማውቀው አስመራ ነው። የባህር ሐይል አባል የነበረ እና በተለይ ለኔ የቅርብ አለቃዬም ነበር። ከተለያየን ረጅም ጊዜ ቢሆንም ያ የቀድሞ ፍቅርና መተሳሰብ አይጠፋምና ሁሌም አስበው ነበር።
ታዲያ መቄዶኒያ እንደገባ ስሰማ ልጠይቀው መጣሁ። ተስፋዬ በጣም አሳቢ ፣በስራው ጎበዝና ታታሪ ተግባቢም አለቃ ነበር። ባህር ሐይልም እያለን ከሙዚቃ ክፍል ሃላፊነት በተጨማሪ የመርከብ ስዕሎችን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን በመሳልም ይታወቅ ነበር። ሲሉ አጫወቱን ስለ አቶ ተስፋዬ።
ሌላኛው የአቶ ተስፋዬ የስራ ባልደረባው የነበሩት የኢትዮዽያ ፕሬስ ድርጅት የፎቶ ግራፍ ባለሙያው አቶ ዳኜ አበራ ናቸው። እሳቸውም እንዲህ አሉ” ተስፋዬ ለሰው አሳቢ፣ወንድምም ጓደኛም መሆን የሚችል ብዙ ነገሮችን አብረን ያሳለፍን ጥሩ ሰው ነው። በህይወት ቆይተን መተያየታችን እጅግ ያስደስታል። ይህንን ተመኝተው በመንገድ የቀሩ አሉ።እናም ተስፋዬን በማየቴ ደስተኛ ነኝ “ብለዋል።
ምስጋና
የምታመሰግኗቸው ሰዎች ካሉ እድሉን ልስጥዎት ?”እኔም እናንተን (ጋዜጠኞችን) በጣም አመሰግናለሁ፤ ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። የዚህን ድርጅት መስራች አቶ ቢኒያምን እና በጐ ፈቃደኛ ሆነው እኛን የሚያገለግሉትን ሁሉ በጣም አመሰግናቸዋለሁ። በአንድ ወቅት የአገር ባለውለታ የነበርን ሰዎች ነን መንገድ ላይ ወድቀን የነበርነው። አሁን ከየቦታው ተሰብስበን ቀሪ ዘመናችንን በደስታና በጤና እንድናሳልፍ ሆነናል፤ ደስተኞች ነን።” አሉ።
መልዕክት ለትኩስ ሀይል
“እናንተ ወጣቶች ከሚያለያያችሁ ብዙ ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧችሁ በጣም ብዙ ነገሮች አሉ። ስለዚህ መገፋፋቱን ትታችሁ ለአገር አንድነት፣ ሰላም እና ብልጽግና እንድትሰሩ እመክራለሁ።“አሉ። እውነት ነው ከምንም ነገር በፊት መቅደም ያለበት የሀገር ሰላም ነው። አረጋውያኑ ተጡረው፤ ቢታመሙ አስታማሚ አግኝተው መኖር የሚችሉት እና ሲሞቱም በክብር የሚቀበሩት የሀገር ሰላም ሲኖር ነው።
ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ተምረው ለቁም ነገር የሚበቁት ሀገር ሲኖር ነው፤ ሀገር ሰላም ሲሆን ነው።ይሄ ለማንም ግልጽ የሆነ ሁሉንም የሚያስማማ ሀሳብ ነውና ምክራቸውን ተቀብለን እሳቸውም ቀሪ ዘመናቸው እንደተመኙት መቄዶንያን የሚያገለግሉበት በመቄዶንያ የሚገለገሉበት እንዲሆንላቸው ተመኝተን ተሰናበትናቸው። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2011
አብርሃም ተወልደ