ከከተሞች መስፋፋትና ፈጣን ዕድገት ጋር ለተያያዙ ተግዳሮቶች ወጥ የሆነ መፍትሔ መከተል እና ከአጋር አካላት ጋር በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑ ይነሳል፡፡ እንዲሁም ከተሞችን ማዘመንና ዘላቂ ዕድገት ያላቸው በማድረግ የበለፀጉ ከተሞችን በመገንባት ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ የትብብር ሥራ የሚሻ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
በአሁኑ ወቅት በርካታ የአፍሪካ ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመብራትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በአግባቡ ማግኘት እየቻሉ አይደለም፡፡ በተጨማሪም በአህጉሪቱ የከተማ ነዋሪ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል፡፡
ለዚህም በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርና በአፍሪካ ሕብረት አዘጋጅነት “ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ሃሳብ የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
በፎረሙ ማጠቃለያ የአፍሪካ ከተሞች ክትመት የቃልኪዳን ሰነድ የጸደቀ ሲሆን፤ የቃልኪዳን ስምምነቱ ከተሞች የሀገራት ኢኮኖሚ ማዕከል እና የብልፅግና መሠረት በመሆናቸው፣ በዕቅድና በሥርዓት የሚመሩ፣ ለኑሮ የተመቹና በቴክኖሎጂ የበለጸጉ ዘላቂ ከተሞችን ለመገንባት በማስፈለጉ እንደሆነ ተጠቅሷል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንደሚገልጹት፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ታሪካዊና ስኬታማ ነበር፤ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ነው፡፡ በዚህም ከ49 የአፍሪካ ሀገራት፣ የዘርፉ የሥራ ሃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ አጋር ድርጅት ተወካዮች፣ ምሁራንና የፋይናንስ ተቋማት ሃላፊዎችን ጨምሮ በፎረሙ ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች ታድመውበታል፡፡
የአፍሪካ ክትመት ቃልኪዳን ሰነድ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ማዕከል የሆኑ ከተሞችን ማዘመንና ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ የሚያነሱት ሚኒስትሯ፤ ፍትሃዊ የሆኑ የከተማ ልማት ሥራዎች አስገዳጅ እንዲሆኑ በማድረግ ከተሞችን ለሀብታም ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጎች መሠረተ ልማቶችን የሚቋደስበትና አካታችነት ያለውን ልማት የሚያበረታታ ነው ይላሉ፡፡
የቃልኪዳን ሰነዱም ፈጣን ምጣኔ ባለው የአፍሪካ ክትመት ሂደት ሁሉንም አፍሪካዊ ተጠቃሚ እንዲሆን በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ይዘት አካቷል፡፡ ከተሞችን በክላስተር በማደራጀት እንደየነባራዊ ሁኔታቸው የማደግ አቅማቸው ልክ በጋራ ማደግ እንደሚጠበቅባቸውና ይህንን የሚደግፍ መሆኑን ሚኒስትሯ ይናገራሉ፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ በልማት አፍሪካውያን ወደኋላ የቀሩ በመሆናቸው አጀንዳቸውን የጋራ አድርገው በዓለም መድረኮች ላይ ድምጻቸውን ካላስተጋቡ ተደማጭነት አይኖራቸውም፡፡ በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የጸደቀው አዋጅ እንደሕግ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ በማድረግ የትኛውም ዓለም አቀፍ ተቋም የሚያመጣቸው ሀብቶች በፍትሃዊነት ይሰራጫሉ፡፡
የዓለም የከተሞች ፎረም ከወራት በኋላ በግብጽ ካይሮ ይካሄዳል፤ ኢትዮጵያ ይህን ፎረም በማስተናገዷ ብዙ ልምዶች ማግኘቷን የሚጠቁሙት ሚኒስትሯ፤ በቀጣይም ከ20ሺህ በላይ ዜጎች የሚታደሙበትን የዓለም የከተሞች ፎረም ማዘጋጀት እንድትችል ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፣ ፎረሙ ትርጉም ያላቸው ውይይቶች፣ ተሳትፎዎች እና የልምድ ልውውጦች በመሪዎች መካከል የተካሄዱበት እንዲሁም መሪዎቹ ተሻጋሪ እሳቤዎቻቸውን ለአፍሪካ የከተሞች ፎረም ዲክላሬሽን ግብዓትነት ያቀረቡበት ነው። ይህ አዋጅ ሰነድ ብቻ አይደለም፤ ለሁሉም አፍሪካውያን ብሩህ ተስፋ ለመቅረጽ ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የምናሳይበት ቃልኪዳናችን ነው ብለዋል።
የከተሞች መስፋፋት ማኅበራዊ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት እምቅ አቅም እንዳለው የሚገልጹት አቶ ጃንጥራር፤ ይህን አቅም ለመጠቀም ግን ከቃላት ባለፈ የጋራ ግቦችን ለማሳካት ተግባርን፣ ትብብርን እና ያልተቋረጠ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ጃንጥራር ገለጻ፤ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የአካባቢ መራቆት፣ የመሠረተ ልማቶች አለመሟላት፣ ኢኮኖሚያዊ ኢ-ፍትሐዊነትን የመሳሰሉ ተግዳሮቶች የምንጋራቸው ናቸው። በጋራ በመሥራት፣ ልምዶችን በመለዋወጥ እና እርስ በእርስ በመማማር እነዚህን ተግዳሮቶች መሻገር እንችላለን።
የከተሞቻችን እድገት ከገጠር ማህበረሰባችን ደህንነት ጋር በቅርበት የተሳሰረ ነው። ከተሞች ሁሉን አቀፍ እድገት ላይ በማተኮር የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶችን፣ አገልግሎቶችንና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን በመፍጠር የከተሞች መስፋፋትን ዕድል በማድረግ ወደ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግናና ዘላቂ ልማት ለመለወጥ በጋራ ልንሠራ ይገባል፡፡ ገጠራማ አካባቢዎቻችንም በዚህ ጉዞ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይጠበቅብናል ይላሉ አቶ ጃንጥራር።
እንደ ምክትል ከንቲባው ንግግር፤ በአዋጁ ውስጥ ከተዘረዘሩት መርሆች እና ከተቀመጡ ግቦች በላይ መሥራት የእያንዳንዳችን ቀዳሚ ተግባር ነው። የከተሞች መስፋፋት ለሁሉም አፍሪካውያን ጥሩ የእድገት አንቀሳቃሽ ኃይል እንዲሆን ከድንበር ተሻግረን መሥራታችንን መቀጠል አለብን።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰፈራ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አና ክላውዲያ ሮዝባች በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ እ.አ.አ በ2016 በኢኳዶር በተካሄደው አዲሱ ዓለም አቀፍ የከተሞች አጀንዳ ሶስት መሠረታዊ ጉዳዮች ተነስተዋል። እነኝህም ዜጎችና መኖሪያ ቤት በከተማ ማዕከላት፣ መንግሥት ከተሜነትን የሚደግፍ አሳታፊና እስቲራቴጅካዊ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት፣ መሬትን የሥነምህዳርና ማህበራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መገልገል ይጠበቃል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ 50 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ሕዝብ በቂ የኤሌክትሪክ፣ የውሃና ሌሎች የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን በአግባቡ እያገኘ አይደለም፡፡ እንዲሁም በእርስ በእርስ ግጭት፣ ከአየር ንብረት ለውጥና ከሌሎችም ተግዳሮቶች ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎች ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡
በ2050 በአፍሪካ 60 ሚሊዮን አዲስ የከተማ ነዋሪዎች ይፈጠራሉ። ለዚህ ያለንን ሀብት በዋናነትም መሬትን በአግባቡ በመጠቀም፣ ተፈጥሮን በማክበርና ቅርሶችን በመጠበቅ ከተሞቻችንን መገንባት አለብን ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ለዚህም አዲሱ ዓለም አቀፍ የከተሞች አጀንዳ አዳዲስ እሳቤዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ በማነሳሳት በከተሞች ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እያደረገ ይገኛል፤ ይህም ለአፍሪካውያን ተሞክሮ ሊሆን የሚችል እንደሆነ ይጠቁማሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ ከተሞች እነኚህን ዜጎች ተቀብሎ የማኖር አቅም የሌላቸው በመሆኑ በተለይም የመሠረተ ልማትና መሠረታዊ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ ከተሞች በፍጥነት መገንባት እንዳለባቸው አንስተው፤ አፍሪካውያን ያላቸውን መልካም ተሞክሮች በመቀያየርና የመበልጸግ አቅማቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በርካታ የዓለም ከተሞች ለዜጎች የሚሆን የመኖሪያ ቤት እጥረት እያጋጠማቸው በመሆኑ ሀገራት በዚህም ዘርፍ በትኩረት በመሥራት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ችግሮችን ማቃለል እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም