አዲስ አበባ፡– የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የህብር ቀንን በማስመልከት ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መረጃ ማዕከል የዘጠኝ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት “አብረን ነበርን፤ አብረን እንኖራለን” በሚል መሪ ሃሳብ የኅብር ቀንን አስመልክተው በትናትናው ዕለት በማዕከሉ ማዕድ አጋርተዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ ከዘጠኝ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።
እንደ ሀገር የመስጠት ልምምድ ሊኖር እንደሚገባ የገለጹት ካሳሁን (ዶ/ር ፤ በመስጠት የሚጎል ነገር የለም ስለማይኖር ሁሌም መስጠትን ማስቀደም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተለያዩ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉን አውስተው፤ ዜጎች እንዲሁም ተቋማት የመረዳዳት ባህልን ማዳበር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ ጳጉሜን አራት የሚከበረውን የህብር ቀንን በማስመልከት በማዕከሉ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕድ አጋርተዋል።
ለአረጋውያን ማዕድ ማጋራት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ስላለው ሁሉም ዜጋ የአቅሙን መደገፍ እንደሚገባው አውስተው፤ ሚኒስቴሩ በየዓመቱ ጳጉሜን አራት በማዕከሉ ማዕድ ለማጋራት መወሰኑንም ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በማዕከሉ ማዕድ ሲያጋራ የመጀመሪያው አለመሆኑን ገልጸው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዲኤታ ያስሚን ውሃቢረቢ በበኩላቸው፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሕይወታቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ እራሳቸውን እንዲችሉና ለሌሎች እንዲተርፉ ማድረግ እንደሚስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ በህብር፣ በመተባበር እንዲሁም አብሮ በመቆም ቀን መደረጉ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አውስተው፤ ኢትዮጵያውያን ሁሌም መደጋገፍን ሊያስቀድሙ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የማዕከሉ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ውጪ በተለያዩ ክልሎች አገልግሎቱን በማስፋት ደጋፊ ያጡ አረጋውያን እና የአእምሮ ህሙማን ወገኖቻችን በመሰብሰብ እንክብካቤ ለማድረግ በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በማዕከሉ ከሰባት ሺህ 500 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን አገልገሎት እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ ማዕከሉ በመምጣት፣ በ8161 አጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክ እንዲሁም በጎ-ፈንድሚ ሁሉም ዜጋ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም