አዝማሪ ወታደር ነው። አዝማሪ ሽማግሌ ነው። አዝማሪ መካሪ ነው፤ አዝማሪ ጠብ አጫሪ ነው። አዝማሪ ነብይ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አዝማሪ ይሄን ሁሉ ነበር። ነበር የምንልበት ምክንያት አሁን ላይ እንኳን ይሄን ሁሉ አንዱንም ስላልሆነ ነው።
አሁን ላይ ‹‹ነው›› የምንለው ዘፋኝነቱን ብቻ ነው፤ ለዚያውም አልፎ አልፎ እና በተሰወኑ ቦታዎች።
‹‹አዝማሪ ወታደር ነው›› ስንል፤ በኢትዮጵያ የንጉሳዊ ሥርዓት ዘመን ከወታደር እኩል የጦርነት ተሳታፊ ነበር። ወኔ ቀስቅሶ ወደ አውደ ውጊያ ይቀላቅላል፤ የደከመውን በነገር ጎሸም እያደረገ እንዲበረታታ ያደርጋል። ከጦር አዛዦች ያላነሰ ሚና ነበረው ማለት ነው። ይሄ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተደጋግሞ የተነገረ የአዝማሪ ሚና ነው።
‹‹አዝማሪ ሽማግሌ ነው›› ስንል፤ ከዚያና ከዚህ ያሉ ባለንጣዎችን ለማስማማትም ይሠራ ነበር። ሰላምን ይሰብካል፤ እርቅን ያወርዳል። በዚያው ልክ ግን ጠብ አጫሪም ነበር። አንዱን ወገን እያሞገሰ ሌላውን ወገን እያንኳሰሰ፤ ተሰዳቢውን እልህ በማስገባት ለበቀል ያነሳሳው ነበር፤ ወይም ደግሞ አንዱን ወገን ይዞ ‹‹የእገሌን ወገን በለው! ውጋው!›› እያለ ያሞጋግስ ነበር።
‹‹አዝማሪ ነብይ ነው›› ስንል፤ ነገ ምን ሊከሰት እንደሚችል ይናገራል፤ እንዲህ ሊሆን ይችላልና እንዲህ አድርጉ እያለ ይዘፍናል። የንጉሦስን ስም እየጠራም ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ፣ ምን እንደሚገጥማቸው ይተነብያል!
ይሄ ሁሉ የአዝማሪ ሚና አሁን ላይ ‹‹ነበር›› እያልን ነው የምንጠቅሰው። በአሁኑ ወቅት ያለው ከዚህ የተለየ ነው። አዝማሪዎች የሚገኙት በምሽት የባህል ቤቶች ብቻ ነው። ለዚያውም የግጥም ይዘታቸው ጥልቅ መልዕክት ያለው ሳይሆን ለማሳቅ ብቻ ተብሎ የሚገጠም ነው።
አብዛኞቹ የአዝማሪ ምሽት ቤቶች ግጥሞች ወሲባዊ ቃላት በመጠቀም ለማሳቅ ብቻ ተብለው የሚገጠሙ ናቸው። ከዚህ አለፍ ካለም የታዳሚውን አካላዊ ቁመና እና ባህሪ ላይ በመመስረት ለማዝናናት የሚባሉ ናቸው። ድሮ የነበሩት ግን ቀጥተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። ውስጠ ወይራ ሀሳብ የያዙ በሰም እና ወርቅ የተሰደሩ ናቸው።
አዝማሪዎች በፖለቲካ ውስጥ ምን ሚና እንደነበራቸው አንድ ጥናት ዋቢ አድርገን እንመልከት። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሚያዘጋጀው ዓለምአቀፍ የአዝማሪዎች ጉባኤ ላይ በ2008 ዓ.ም የቀረበ ነው።አጥኚው የታሪክ ባለሙያ እና በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኛ የነበረ አቶ አየለ አዲስ ነው::
ጥናቱ ‹‹የአዝማሪዎች ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ (1845-2007 ዓ.ም)›› በሚል ርዕስ ነው የተሰራው። በቅንፍ ውስጥ የተጠቀሰው ዓመተ ምህረት ከዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ እስከ ኢህአዴግ ያለውን ዘመን ያሳየናል፤ 162 ዓመታት ማለት ነው። በዘመነ ኢህአዴግ፤ በንጉሣዊ ሥርዓት የነበረውን የአዝማሪ ሚና ማግኘት የሚቻል አይመስልም። ለማንኛውም አጥኚው የሚነግረን ነገር እንየው።
አዝማሪነት ከዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ድረስ የቤተ መንግስት ሹመት ነበረው፤ ይሄውም ‹‹ሊቀመኳስ›› የሚል ማዕረግ ይሰጠዋል። የሊቀመኳስ ሚና ንጉሡን ማሞካሸትና በጦር ሜዳ ደግሞ ወታደሩን ማበርታት ነው። በደል ከተፈጸመም ‹‹ተው! እንዲህ አይደረግም›› እያለ የመገሰጽ ሥልጣን ነበረው።
ንጉሣዊ ሥርዓት በወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ሲተካ አዝማሪዎች ወደ ህዝብ ተቀላቀሉ። በደርግና በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት አዝማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቤተ መንግስት ወጥተው ከህዝብ ጋር ተቀላቀሉ። ግጥሞቻቸውም ከአመስጋኝነትና ከተችነት ወደ አዝናኝነት ተቀየሩ።
አጥኚው እንደሚነግረን፤ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥም ስላልተካተተ የመጫወቻ መሳሪያዎችም እየተረሱ መጡ፤ የአዝማሪዎች ጨዋታም በዘመናዊ የውጭ አጨዋወት ስልቶች ተበረዘ፤ በዚህ ከቀጠለ ይህ አገር በቀል የሙዚቃ መሳሪያና ጨዋታ ሙሉ በሙሉ የመረሳት ዕድል እንደሚገጥመው አጥኚው ስጋቱን አስቀምጧል::
እንግዲህ በዘመነ ኢህአዴግና በደርግ ያዝማሪነት ሁኔታ ይህን ይመስላል፤ አሁን ጥናቱን ዋቢ አድርገን በድሮው ዘመን ምን ይመስል እንደነበር ነው የምናየው።
አንድ አዝማሪ ራሱን ችሎ ‹‹አንድ ሙሉ ባንድ ነው›› ይባላል፤ ምክንያታቸው ደግሞ መሳሪያውን በቀላሉ ያንቀሳቅሳል፤ ድምጹም የመጫወቻ መሳሪያውም በእጁ ነው:: አዝማሪነት ሃይማኖታዊ መነሻ ቢኖረውም ‹‹አንድ ካህን ለነፍስህ መማፀኛ፤ አንድ አዝማሪ ለነፍስህ መዝናኛ›› ይባል ነበርና መዝናኛ እንደነበርም ያሳየናል።
በነገሥታቱ ዘመን አዝማሪዎች የገዥዎችን ጀግንነት ያወድሳሉ። ለዚህም ብራና መዳመጥና ቀለም መበጥበጥ ሳያስፈልግ በቃል ብቻ በመግጠም የየዕለቱን ውሎ ይዘግቡ ነበር።
መቸ ሞተና፤ መቸ ተረሳ
መቅደላ ያለው፤ የቋራው ካሣ
እንግዲህ እኔ፤ ሌላ አላነሣ
ከፈረስ ታጠቅ፤ ከጎበዝ ካሣ
‹‹የቋራው ከሣ››፤ ልበልህ እንዴ?
የለህም ዘመድ፤ ያለ ጐራዴ!
ይህ ግጥም እንግዲህ አጼ ቴዎድሮስን የሚያሞግስና ለንጉሡ የገጽታ ግንባታ የሚሰራ ነው። እንዲህ አይነት በወቅቱ በአዝማሪ የተባሉ ግጥሞች በቃል ሲወራረሱ መጥተው አሁን የጽሑፍ ግጥም ሆነዋል። ዘፋኞችም የራሳቸውን ሃሳብ እየጨመሩ ይዘፍኗቸዋል።
አዝማሪዎች የጠብ አጫሪነት ሚናም ነበራቸው። አንድ ስሙ ጣፋጭ የተባለ አዝማሪ ህዳር 19 ቀን 1845 ዓ.ም ጎርጎራ ላይ በደጃች ካሣ እና በደጃች ጎሹ መካከል ወሳኝ የነበረው የጎርጎራ ጦርነት ሲደረግ ለደጃዝማች ጎሹ ወግኖ፤ አጼ ደጃች ካሣን (በኋላ አጼ ቴዎድሮስ) እያጣጣለ እንዲህ ብሎ ነበር።
አያችሁት ብያ የእኛን እብድ
አምስት ጋሞች ይዞ ጉር አምባ ሲወርድ፤
ያንዣብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሣ
ወርደህ ጥመድበት በሽምብራው ማሣ!
ወዶ ወዶ
በሴቶቹ በነ ጉንጭት ለምዶ
ሐሩ፣ ቋዱ፣ ለውዙ፣ ገውዙ አለ ከቋራ
መንገዱ ቢጠፋ እኔ ልምራ!
በማለት እስከ ጦር አዝማችነት ሊያዋጋ እንደሚችል በመመፃደቅ የ‹‹ፕሮፖጋንዳ›› ሥራ ሰርቷል።
ምን ዋጋ አለው! ነገሩ ተገለባበጠ:: በጦርነቱ፤ የተወደሱት ደጃች ጎሹ በጥይት ተመተው ወደቁ፤ ሠራዊታቸውም ተማረከ። ደጃች ካሣ(አጼ ቴዎድሮስ) አሸነፉ። ያ ‹‹ያንዣብባ እንጂ መች ይዋጋል ካሣ›› ያለው አዝማሪ ተይዞ ደጃች ካሣ ፊት ቀረበ። ‹‹ለምን ነበር የሰደብከኝ?›› ብለው ሲጠይቁት፤ ያ! ሲሳደብ የነበረ አዝማሪ እንዲህ ብሎ ዘፈነ።
አወይ የአምላክ ቁጣ
አወይ የእግዜር ቁጣ
አፍ ጌታውን ያማል የሚሰራው ሲያጣ
ሽመል ይገባዋል የአዝማሪ ቀልማጣ
ሲል ገጠመ። አዝማሪውም የአፉን ነው ያገኘ። ለመለማመጥ ‹‹ሽመል ይገባዋል የአዝማሪ ቀልማጣ›› ብሎ ጥፋተኝቱን ቢናገርም እንዳሰበው አልሆነም። በሽመል ተደብድቦ ተገደለ።
በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመናትም ይሄው የአዝማሪዎች ሚና ከፍተኛ ነበር። እንዲያውም በዘመናዊ የሚኒስትሮች አደረጃጀት ‹‹ሊቀመኳስ›› ከተማ የሚባሉ አዝማሪ ‹‹የአገር ግዛት ሚኒስትር›› ተብለው በአዝማሪነት ደረጃ ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው።
በአጼ ምኒልክ ጊዜ አንድ የ‹‹ራስ››ነት ማዕረግ የነበረው በንጉሱ ላይ አመጽ ማንሳት ጀምሮ ነበር። ይህንኑ ክስተት የወቅቱ አዝማሪዎች እንዲህ ሲሉ በሰም ለበስ ቅኔ ተናግረውታል።
ጃንሆይ ምኒልክ ጠጉራቸው ሳሳና፤ በራ ገለጣቸው
እንግዲህ ንጉሱ፤ ምን ራስ አላቸው?
የራሳቸውን (የጭንቅላታቸው) ፀጉር መሳሳት ግልጽ ትርጉም በማድረግ የራስነት ማዕረግ ያለው የንጉሱ ታማኝ መክዳቱ በቅኔ ተነግሯል።
አጼ ምኒልክ ሲሞቱም ለውደሳ እንዲህ ተብሎ በአዝማሪዎች ተዘፍኗል።
ምኒልክ ተጉዞ፤ የምትጠይቁኝ
ፊትም አላለፈ፤ በኋላም አይገኝ!
አጼ ምኒልክ ከተጓዙ (ከሞቱ) መጎዳታችን ምንም ጥርጥር የለውማ እንደማለት ነው። እንደ እርሳቸው አይነት መሪ ካለፉትም፤ ወደፊት ከሚመጡትም አይገኝም የሚል መልዕክት ያዘለ ነው።
በ1909 ዓ.ም የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ገዥ የነበረት የንጉሥ ተክለሃይማኖት ልጅ ራስ ኃይሉ ይባሉ ነበር። ራስ ኃይሉ የቀረጥ ሥርዓት በህዝቡ ላይ በመጣላቸው የህዝቡን ምሬት የሰማ አዝማሪ እንዲህ ብሎ ነበር።
ከብቱንም ወሰዱት
ሀብቴንም ዘረፉት
ራስ የቀረዎ ትንሽ አማርኛ
ሆዴን በወሰዱት አርፌ እንድተኛ!
እንግዲህ በወቅቱ አዝማሪ እንዲህ የህዝቡንም ስሜት ያስተጋባ ነበር ማለት ነው። ልክ በአሁኑ ወቅት ህዝብ ብሶቱን በመገናኛ ብዙኃን እንደሚያሰማው ያኔ የህዝቡ ዓይንና ጆሮ አዝማሪ ነበር ማለት ነው። መንግስት በህዝቡ ዘንድ ምን እንደሚወራ በአዝማሪዎች በኩል ይደርሰዋል።
በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ የነበረው የጉልት ገዥዎች አለመስማማት አርሶ አደሩን ለአመጽ አነሳስቶ ነበር። አርሶ አደሩም በአመጹ ወደ ገዥነት በመምጣቱ የነገሩን መገለባበጥ የወቅቱ አዝማሪዎች እንዲህ አስተጋብተውታል።
እንዲህ ነው ነፃነት፤ እንዲህ ነው ክብር
ሲሆኑ መታዘብ፤ ባላገሩ ገዥ ገዥው ባላገር።
ከዚሁ ከባላገሩ አመጽ የወጣውና የባላገሩ አመጽ አሸንፎ ጎጃም ውስጥ የብቸና መሪ የነበረ አምላኩ የተባለ የአመጹ መሪ ድል ሲቀናው እንዲህ ተባለለት።
በአምላኩ አባ ግዮን፤ የበረሃው መናኝ
በአንድ ዓይኑ ፀዳቂ፤ በአንድ ዓይኑ ተኮናኝ
ተብሏል። የገባሩን ባላገር መብት በማስከበሩ ጥሩ እንደሰራ፣ የንጉሱን ፊውዳላዊ ሥርዓት በመቃወሙ ደግሞ ሊኮነን እንደሚችል የሚናገር ግጥም ነው።
በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ ይሁን፤ የባለሥልጣናቱን ሙሰኝነት፣ የፍትሕ እጦት፣ አድሎዓዊነትና የመሳሰሉት በአዝማሪዎች እንዲህ ተነግረዋል።
በአንዲት ሉክ ጀምሬ አቤቱታ
ስንት ዓመት ልኑር ስንገላታ
በሸንጎ ስወጣ ስወርድ
አለቀ ስንቄ በመንገድ!
አንተ የበታች ሹም መዝገብ ቤት ያለኸው
ዶሴዬን ወደታች አርገህ የቀበርከው
እንዲታይ ነው እንጂ ወደበላይ ቀርቦ
እንዲኖር አይደለም መዝገብ ቤት አጣቦ!
በማለት የህዝቡን ብሶትም ተናግረዋል። አንባቢዎቻችን! ከዚህ በላይ ለመሄድ የዚህ ዓምድ ቦታ ስላልፈቀደልን ለሳምንት ቀጠሮ እንያዝ። በሚቀጥለው ሳምንት የዚህን ቀጣይ ክፍል እና በአሁኑ ጊዜ በምሽት የባህል ቤቶች የሚባሉትን ይዘን እንመለሳለን፤ መልካም ሳምንት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011
ዋለልኝ አየለ