ዓውደ ዓመት ሲመጣ እንደፈካች ፀሐይ ውበታቸው የሚስቡ ፀአዳ የሀገር ባህል ልብሶችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ በተለይም በዘመን መለወጫ በሀገር ባህል ልብስ ደምቆ መታየት፣ ከምግብ ዝግጅቱ፣ ቤት ከማስዋቡና ከዘመድ አዝማድ ጥየቃው ባልተናነሰ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
ወቅቱ ባመጣው አማራጭ መሰረት ምቹና ቀለል ባሉ ዲዛይኖች የተዘጋጁ የሀገር ልብሶችን ከበዓል ውጪም የመልበስ ልምዱ እያደገ ቢመጣም በዓልን አስታኮ ደግሞ ሰፊ የአልባሳት ግብይት ይከናወናል።
አዲሱን ዓመት በደመቀና በደስታ ለማክበር ደግሞ በአብዛኛው የመዲናዋ ነዋሪዎች አዲስ የባህል አልባሳት ለመግዛት የሚያቀኑት ወደ ሽሮ ሜዳ ገበያ ነው። እኛም የበዓል ድባቡ ምን ይመስላል የሚለውን ለመቃኘት ወደገበያ ስፍራው አቅንተናል።
ሽሮ ሜዳ የበዓል ድባቡን በሚያንጸባርቅ መልኩ በሀገር ባህል አልባሳት፣ በመዋቢያ ጌጣጌጦች እንዲሁም በሸማቾች ግርግር ተሞልቷል።
የሻጭና የሸማቹ የገበያ ዋጋ ክርክርና ድምጻቸው ከፍ ተደርጎ የተከፈቱ የበዓል ሙዚቃዎች አካባቢውን ሞቅ ደመቅ አድርገውታል። በየመደብሩ የተሰቀሉ በህብረ ቀለማት የተዘጋጁ የባህል ልብስ ጥበቦች ቀልብን ይስባሉ።
በሽሮ ሜዳ የገበያ ማዕከል አልባሳትን ሲሸጡ ያገኘናቸው አቶ ልሳነወርቅ ያሬድ፤ በብዛት የጎንደር ፣ የወሎና የራያ የተሰኙ የባህል አልባሳትን ይዘው መቅረባቸውን ያስረዳሉ፡፡
ገበያው ከአምናው ጋር ሲነጻጸር መቀዛቀዙን የሚናገሩት አቶ ልሳነወርቅ፤ ይህም የሆነው የሀገር ልብስ መልበስ ካለመፈለግ ሳይሆን ሰው የመግዛት አቅሙ በመቀነሱ ነው ይላሉ።
አቶ ልሳነወርቅ እንደሚሉት፤ ሰዎች የሀገር ልብስን ሲያስቡ ዋጋው ከፍ ያለ እንደሆነ ይገምታሉ። ሆኖም በገበያ ማዕከሉ አቅምን ያማከለ የሀገር ባህል አልባሳትን ማግኘት ይችላሉ፡፡
በሱቃችንም ዝቅተኛ ከአንድ ሺህ 500 መቶ እስከ ከፍተኛው 15 ሺህ ብር የዋጋ አማራጭ ያላቸው አልባሳት ይገኛሉ። ሆኖም የገበያው መቀዝቀዝ ከኑሮ ውድነቱ ጋር የመጣ ሊሆን ይችላል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
አሁን ላይ እያቀረብን የምንገኘው የሀገር ልብሶች ቱባውን ባህል የሚያሳዩ ናቸው ያሉት አቶ ልሳነወርቅ፤ በቀጣይ ቀለል ባሉ ዲዛይኖችና የዋጋ አማራጮች ለማቅረብ አስበናል ብለዋል፡፡
በገበያ ማዕከሉ ብሎም በእርሳቸው የንግድ ቤት ለበዓል የሚሆኑ አልባሳት በበቂ ሁኔታ የቀረቡ ቢሆንም የዘንድሮ አዲስ ዓመት የገበያ ድባብ የተወሰነ መቀዛቀዝ አለው ያሉት ደግሞ አቶ ዳባ በቀለ ናቸው፡፡
ከአልባሳቱ ዋጋ ጋር በተያያዘ የተወሰነ ጭማሪ መኖሩን ጠቁመው፤ ያለፈው ዓመት እስከ አምስት ሺህ 500 ይሸጥ የነበረ የባህል ቀሚስ ዘንድሮ እስከ ስምንት ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ሸማቹ በዚህ ወቅት በብዛት የባህል አልባሳትን የሚገዛበት ወቅት ነው ያሉት አቶ ዳባ፤ በእሳቸው ሱቅ የሚገኙ አልባሳትን ከሶስት ሺህ 500 ብር ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሺህ እየተሸጡ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
በተለምዶ በበዓላት ወቅት የባህል አልባሳትን የመሸመት ልምድ እንዳላቸው የገለጹት ወይዘሮ እቴነሽ ግደይ በበኩላቸው፤ ገበያው ካለፉት ጊዜያት የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ቢያሳይም አልባሳቶቹን በሚፈልጉት መልኩ ተዘጋጅተው ማግኘታቸውን ይናገራሉ።
አልባሳቱ ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ በተለያዩ ዲዛይንና ቀለማት በስፋት መኖራቸውን ያስተዋሉት ወይዘሮ እቴነሽ፤ ይህም የአሁኑ ትውልድ የባህል አልባሳትን ከዘመኑ ጋር አቀናጅቶ እንዲሄድ ይረዳል ይላሉ።
ሌላዋ በገበያው ከጓደኖቿ ጋር በሸመታ ላይ ያገኘናት ወይዘሪት ሒሩት ለማ በበኩሏ፤ አዲሱን ዓመት በማስመልከት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን በቡድን የሚለበሱ ባህላዊ አልባሳትን በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን ታስረዳለች።
በሽሮ ሜዳ ገበያ በተለያየ ቀለማትና የዲዛይን አማራጭ የቀረቡ አልባሳትን ለመምረጥ የአይን አዋጅ ሆኖባቸው እንደነበር አንስታ፤ በመጨረሻም የመረጡትን አልባሳት የገዙበት ሂሳብ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር የተመጣጠነ ዋጋ ያለው መሆኑን ተናግራለች።
በአጠቃላይ ሸማቾችም ሆኑ ነጋዴዎቹ እንዳስታወቁት፤ በዓላትና ልዩ ልዩ ኹነቶች የባህል አልባሳት ገበያው እንዲነቃቃ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
ዳግማዊት አበበና ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም