በብዙ ምክንያት ራሳቸውን በፍርሃት አጥር ውስጥ ያጥራሉ፡፡ ፍርሃት የብዙ ጉዞዎቻችን መሰናክል፣ የዓላማችን እንቅፋትና የጥያቄዎቻችን ሁሉ አጉል ምክንያት ነው፡፡
ሰው የራሱ በሆኑ ምክንያቶች ወደ ፍርሃት አዘቅት ራሱን ይከታል፡፡ አንዳንዶች በአስተዳደጋቸው ተጽዕኖ፣ አንዳንዶች በውሎ አጋጣሚዎቻቸው ገጠመኝ፣ ሌሎች ደግሞ በሰሟቸው ታሪኮች ሳቢያና ድንገቴዎች ምክንያት ነው፤ የሚፈሩት፡፡ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን የፍርሃት ምክንያቶች በልምድ እናዳብራቸዋለን እንጂ አብረውን አይወለዱም ፡፡
በፍርሃት አጥር የታጠረ ሰው ወደሚፈልገው አቅጣጫ ለመሄድ ሰበባ ሰበብ መደርደሩ የታወቀ ሲሆን በአንዳንድ ሰዎች ላይ ደግሞ ፍርሃታቸውን በአካላዊ ግብረ-መልስ ሲያንፀባርቁ ማየት የተለመደ ነው፡፡
ፍርሃት በርካታ ምክንያቶች ይሰጠዋል ፤ ሰውን ፣ ተፈጥሯዊ ክስተቶችን ፣ እንስሳትን …ወዘተ የሚያካትት ነው፡፡
ታላቁ መጽሐፍ እንደሚለን ደግሞ ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ የሰው ልጅ በልዩ ልዩ ሰበባ ሰበብ ነው ያንን ፍራቻውን የሚያሳየው፤ ወይም የሚያንጸባርቀው፡፡
አይጥ እቤቱ በመግባቷ መፈጠሩን የጠላው ወዳጄ ይህንን መሰል ፍርሃት እንዳለበት ማወቄ አስገርሞኝ ምክንያቱን ስጠይቀው ፣ “እጠላታለሁ፤ እጠላታለሁ….አስቀያሚ ነገር ናት ደግሞ ጥርሷን አይተሃል ዘግኛን እኮ ነው” አለኝ፡፡ የሆኖ ሆኖ ምክንያትህ ግን አስቂኝ ነው፤ የጠላኸውን ሁሉ እኮ አትፈራውም ፤ የፈራኸውን ነገር ግን ትጠላለህና ምክንያቱ ፍርሃትህ ይመስለኛል፤ አልኩት፡፡
በረዥሙ ከተነፈሰ በኋላ፣ ምን መሰለህ ልጅ ሆኜ ቤተሰባችን ውስጥ ብዙ ልጅ ስለነበረ የምንተኛው መሬት ላይ በፍራሽ ነውና ፤ ከዕለቶች በአንዱ ቀን በከባድ ጩኸት መነሳቴን አስታውሳለሁ፤ አለኝ ፡፡
እናስ? አልኩት፡፡
እና…ምን መሰለህ ብልቴን ማለት …እ…. (በረዥሙ እንደገና ተንፍሶ) ነክሳኝ በጣም ደም ፈሰሰኝ ፡፡ ስለዚህ እንዴት ልወዳት እችላለሁ፤ ብሎ ጠየቀኝና ከምድር ላይ አይጦች የሚባሉ ነገሮች መጥፋት አለባቸው፤ አለኝ፡፡ መጥላቱን እንኳን ብንፈቅድለት ፍራቻው ግን ከመስመር ያለፈ ነው የሚመስለው፡፡
የእኔም ምላሽ፣ አትውደዳት ግን አትፍራት ነው፤ አልኩት፡፡ ተው፣ ተው ተው «ያልደረሰበት ግልግል ያውቃል» ሲል ተረተብኝ፡፡
ለዚህ ወዳጄ የፍርሃቱ ምንጭ የተጠበቀ ቢሆንም ለዘላለም በአይጥ ፍራቻ መከራውን ማየትና አይጥን በዓይነ ቁራኛ ማየት አይገባውም፡፡
እሱን የሚያህል ሰው እኮ አይጥን በመፍራት ብቻ በአንድ ዓመት ውስጥ ስምንት የኪራይ ቤቶች መቀያየሩን ነግሮኛል፡ ፡ እና የአይጥ ምስል እንኳን ፊልም ላይ ሲያይ እግሮቹን ይሰበስባል፡፡ ሰውን መፍራት ብቻ ሳይሆን ሁሉን መፍራት በራስ ላይ ወጥመድ ያመጣል፡፡ አላግባብ የሆነ ፍራቻ ሁሉ ዋጋ ያስከፍላል፡፡
ለዚህ ለወዳጄ ታዲያ ያልኩት ልጅ ሆነህ ከስንት ሰው ጋር ተደባድበሃል፤ ከስንት ሰው ጋርስ ተጣልተሃል? እነዚህ ጸቦች ያስከተሉብህ ቁስል፣ ያስከተሉብህ ጠባሳ ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ይሁንናም የዚያን ጊዜ የተደባደብከውን ልጅ ባየህ ቁጥር አሁን ትቆጣለህ? ትፈራዋለህ? ንዴትህ ይቀሰቀሳል? ወይስ የልጅነትህን ወይም የጉርምስናህን ረብሽ ረስተህ አብረሃቸው ትጨዋወታለህ? ስል ጠየቅሁት፡፡
ይህንና ያንን እንዴት ታወዳድረዋለህ፤ እንዴት እንደሚናፍቁኝ አታውቅም፤ ሲል ነገረኝ፡፡ እስቲ ቆም ብለህ አስብና አይጧ እናንተ ቤት ውስጥ አንተ ሳትኖርም ነበረች ፤ አንተ ኖረህም አለች፤ ያን ቀን ግን ድንገት ተኝተህ መጣችና ትንሽ ጥሬ ያገኘች ስለመሰላት ነከሰችህ እንጂ፣ ከሰይጣን ወይ ከሌላ ነገር ጋር አያይዘህ በማሰብ ለምን ትጨነቃለህ፤ አልኩት፡፡
እሱስ ልክ ነህ ፤ግን አሁንም ቢሆን ደባሪ ነገር ናት ፤ አለኝ፡፡ ግን ወንድሜ በአይጥ የተነሳ ስንት ቤት ስትቀይር ወደ አእምሮህ ያልመጣው ነገር አይጢቱ የኑሯችን አካል እንጂ እኛ ወድደን የምናጠፋትና የምናኖራት አይደለችም ፡፡ ልንቀንሳት እንችላለን ከቶውንም ከምድር ላይ ግን ልናጠፋት አንችልም፡፡
አይጥ በመኖሯ በርካታ ተረፈ እጽዋትና እንስሳት ምግቧ ይሆናሉ፤ አይጥ በመኖሯ በርካታ ላቦራቶሪዎች መድኃኒት ይፈትሹባታል፤ አይጥ በመኖሯ ተፈጥሮ በራሷ ኡደት የሕይወት ክቦሽ ውስጥ ሊወገዱ የሚገባቸውን ተሃዋሲያን ታጠፋለች፤ አይጥ በመኖሯ ታላላቅ የወፍ ዝርያዎችና ድመት ምግብ ይኖራቸዋልና፤ አይጥ ከምድር ላይ እንድትጠፋ የምታደርገውን ፀሎት አቁም ፤ አልኩት፡፡
ኧረ፣ ባክህ እውነትህን ነው? አለኝ ፡፡
አዎ እውነት ነው ፡፡ በሕይወት ኡደት ውስጥ የማይጠቅም የሚባል ነገር የለም፡፡ እና ከአይጥ ዲኤንኤ 92 ከመቶ ያህል የሰው ልጆች እንደምንቀራረብ ታውቃለህ ? ስል አረጋጋሁት::
ይገርማል፤ ማለት ብቻ ነበር መልሱ፡፡
ከዚህ ፍርሃት ለመውጣት ቆም ብሎ ማሰብና ፍቱን የሆነ መድኃኒት መፈለግ ይገባናል፡፡ ለአንዳንዶች የሥነ አእምሮ ለሌሎች የሕይወት ተመክሮ ለአንዳንዶች ደግሞ ጸሎት ፍቱን መፍትሔ አለው፡፡ እምነት ያድናልና :: በእግዚአብሔር እታመናለሁ፤ እያሉ አይጥን መፍራት ግን አስቂኝ ነው፡፡
ወደዋናው ነገራችን እንመለስና ፍርሃት ብዙ መገለጫዎች አሉ፡፡ እጅግ በጣም ታላላቅ የተባሉ መሪዎች እንኳን ይህን መሰል ባህሪ አያጣቸውም ነው የሚባለው፡፡ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት የሆነው ሒትለር የፍርሃት መነሻው ይሆን የነበረው ድመት እንደነበረ አንዳንድ መዛግብት ያወሳሉ፤ አጋሩ የጣሊያኑ ሙሶሊኒም እንዲሁ ጨለማን አጥብቆ ይፈራ እንደነበረና የኮሪደር ብርሃን ካነሰ እንኳን ጠባቂዎቹን ያንቆራጥጥ እንደነበረ ይነገርበታል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እነዚህ ሰዎች ሥልጣናቸውን የማጣት ፍርሃት አለቅጥ ጨካኝ አድርጓቸው እንደነበረ ታሪክ ምስክር ነው፡፡
ፍርሃት የጭካኔ ወላጅ አባት የመሰሪነት ክፉ እናት ነው የሚሉት አለምክንያት አይደለም፡፡ ፈሪ ሰው ተጠራጣሪ ስለሆነ በህልሙ ያሳደደውን ሰው እንኳን በእውን ከመግደል አይመለስም:: ኡጋንዳን ለስምንት ዓመት ያስተዳደሩትንና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ኡጋንዳውያን እየገደለ ቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ የጣለው ሰው ከሁሉም ጭካኔው የከፋው ጭካኔ ደግሞ አንድ ቀን የተከሰተው ነው፡፡
የመጀመሪያውን ትልቋን ሚስቱን መፍታት ይፈልግና አንድ የሞኝ እቅድ ያቅዳል፡፡አንዱን ወታደሩን በትዕዛዝ ሄደህ አባብላት አሽኮርምማት ብሎ ያዝዘዋል፡፡ ጌታዬ ይቅርብኝ ይላል፤ አድርግ ስልህ ማድረግ ነው፤ ይልና ወታደሩ ሴትየዋ ላይ ጥላ ይሆንባቸዋል፡፡ ከዚያ ቀጥሎም «አጠገቧ ሁን አልኩህ እንጂ ንካት ብዬሃለሁ ወይ» ብሎ ሴትየዋን ያባርርና ያንን ምስኪን ወታደር ይገድለዋል፡፡ ሊገለብጠን ሲያስብ በህልሜ አይቼዋለሁ፤ ሲል አሳብቧል:: በሌላ ጊዜ የፕሮፓጋንዳ ሚኒስትሩን «በህልሜ ልትገድለኝ ስታሴር አይቼሃለሁ» ብሎ በአሰቃቂ ሁኔታ አጥፍቶታል፡፡ ለእያንዳንዱ የጭካኔያቸው ድርጊት ሰበብ አያጣቸውም፤ እንዲህ ያሉ ሰዎች:: ሳዳም ሁሴንም ይህን ባህሪ ይጋራል ፡፡ ወደ ኢዲ አሚን ልመልሳችሁ፡፡
ኢዲ አሚን፣ በበታችነት የፍርሃት ስሜት በእጅጉ ይሰቃይ ስለነበረ፤ ከምሁርነት እንዳይቀርበት ራሱን ዶክተር ብሏል፤ ከእምነቱ እንዳይቀርበት ራሱን አልሐጂ አስብሏል፤ ከውትድርናው እንዳይቀርበት ፊልድ ማርሻልነት ማዕረግ ለራሱ ሰጥቷል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ፍርሃቱ ስለሚያንጠረጥረው ቦቅስ ተጫውቶ የሀገሪቱ የከባድ ሚዛን የቦቅስ ቻምፒዮን ራሱን አድርጓል፡፡ የሁሉን እችላለሁ ፍርሃት ነው እንዲህ የሚያባትለው፡፡
ኢዲ አሚንን እንዲሁ አነሳሳን እንጂ የቀደሙ ባለዝና መሪዎችና ታዋቂ ሰዎችም በአንድ ወይም በሌላ የፍርሃት አዙሪት ውስጥ መመላለሳቸውን ማስታወሻዎቻቸው ይነግሩናል፡፡
ለመሆኑ የአንተ የፍርሃት መንስኤ ምንድነው? አለመሳካት ነው፣ አለመጀመር ነው፣ አለማቀድ ነው፣ አለመጨረስ ነው ወይስ ምን ስም ያለው ፍርሃት አለህ? አንዳንዶቹ ስምና ቅርጽ ሰጥተው ነብር ፈራለሁ፣ ጨለማ ፈራለሁ፣ ዝናብ ፈራለሁ፣ ከፍታማ ስፍራ ፈራለሁ፣ ሊሉ ይችላሉ ያም ሆነ ይህ ፍርሃት ባለበት በዚያ ወጥመድ አለ፡፡
ወደ መንፈሳዊው ሕይወት ስንመጣም የቀደመ ልምምድ የሚያስከትለውን ድህረ ጫና መቋቋም አቅቷቸው ለመተው የሚፈሩ ሰዎች አሉ፡፡ «ቀይ ዶሮ አስለምደነዋልና ይበቀለናል» ፤ «ገብስማ ዶሮ ሳይ፣ የሚያርበተብት ስሜት አለብኝ»፤ «ቦቃ በግ ሳይ ….ወዘተ የሚሉ ያለፈ ሕይወት ምርኮኞች አሉ፡፡
ሁሉንም የፍርሃት ተገዢነታችንን መቆጣጠርና በነፃነት መራመድ ግን እንደምንችል ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡ ፍርሃት ወደውስጣችሁ ከውጭ ገባ እንጂ ከውስጣችሁ ወደውጭ አልወጣም፡፡ ይሁንናም የተገላቢጦሽ ይሰማችኋል፡፡
ጅቡ ይበላሃል ተብለን ስላደግን ፤ ስለ ጅብ ሳናይ እንኳን ስሙ ሲነሳ ፍርሃት የሚያድርብን ስለተነገረን ነው፤ እስራኤላውያን ጎልያድን ስላዩት ነው፤ ፍርሃት የተፈጠረባቸው፤ ዳዊት ግን የሚታየው ሳይሆን የማይታየውን ኃያሉን እግዚአብሔር ስለተረዳ ወጣና የማይሸነፍ የሚመስለውን የእስራኤልን ፍርሃት መትቶ ጣለው፡፡ ያንን ፍርሃት ማስወገድ የምንችለው በውስጣችን ያለውን የአሸናፊነት ኃይል አውጥተን ለመጠቀም ስንችል ነው፡፡
የማይፈጸም የመሰለንን እቅድ አቅርበን በግምታችን ፍርሃት ተውጠን ካሰብን አንሰራውም፤ ፍርሃቱ ይተበትበናልና፡፡ ይሁንናም የመስሪያ ስትራቴጂዎች ከቀየስን እንችላለን፤ የመስኖ ውኃ የሌላት ግብጽ በአባይ ላይ የመደራደሪያ ግዙፍ አቅም መገንባቷን እንዳትረሱ፡፡ ሲጀመር የሚቻል የማይመስለው ነገር ሁሉ የሚጀመረው አንድ ተብሎ በትንሹ ነው፡፡ ከዚያም እነዚያ እርምጃዎች እያደጉ ታላላቅ እመርታዎችን ያስከትላሉ፡፡
ከልዩ ልዩ ሱሶችና ደባል ባህሪያት የሚላቀቁ ወጣቶችና ጎልማሶች የሚያስፈራቸው ድህረ መጫጫኖችን (ድብርቱን) የመፍራት አባዜ ነው፤ የሚጠናወታቸው፡፡
አንድ ቀልድ ሲነገር አስታወስኩና ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
አንድ ሰው ለሙሉ ምርመራ ሐኪም ዘንድ ይቀርብና ደም ግፊቱ ፣ ደም ማነሱ፣ ኮሌስትሮል መጠኑ፤ ኩላሊቱ፤ ጉበቱ ወዘተርፈው…. ሁሉ መልካም መሆኑን ሐኪሙ ይነግረውና ክብደትህ ከቁመትህ ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ከተሽከርካሪህ ሌላ በእግር መጓዝ ይገባሃል ሲል ይመክረዋል፡፡
ይህን የሰማው ሰውም ለምንድነው የሚያመኝ ታዲያ ሲል መልሶ ይጠይቀዋል፣ ህመሙን የፈጠርከው አንተ ነህ ሰላም ነህ ሲለው ሰላም አይደለሁም ሲል ሐኪሙ ይሰማና ቀልደኛም ቢጤ ስለነበረ እንዲህ ይለዋል፡፡
ጫት ትቅማለህ ? ሐኪሙ ፡፡
እንደውም በዞረበት አልዞርም ይላል አመመኝ ባይ ፡፡
መጠጥ ትጠጣለህ ?
ምን አረኩህ ዶክተር? ይላል ፡፡
ሲጋራስ ታጨሳለህ ?
ዶክተር ያምሃል እንዴ? እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር አይነካካኝም ሲለው ፤ ዶክተሩ መልሶ ታዲያ፣ ይህን ሁሉ ካላደረግክ ለምንድነው የምትኖረው ሲል ፤ ሰውየው ደንግጦ ጥሎት ሄደ ይባላል፡፡
አንዳንዴ ሳያመን በፈጠርነው ህመም ያልሆነ ህመም ታስረን የሰው ጊዜ፤ ጉልበትና አቅም የምንፈታተን የራሳችን የፈጠራ ህመም እስረኞች አለን ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ግልጽ ነው ፤ ሰዎች አሞታል ብለው ከንፈር እንዲመጡልንና በእዝነት እንዲያዩን ከመፈለግ የሚመነጭ ፍርሃት ነው፡፡
ፍርሃቱ ስጋቱ ጨለማው አንድ ላይ፤
እየተባበሩ በጠራራ ፀሐይ፤
በፍርሃት አለንጋ ያድርጉታል ብካይ!! እንዳለው ገጣሚው ፤ ሰው ሲፈራ በማያውቀው ጨለማ ላይ የማያውቀውን ስጋት ፈጥሮ ወደማያውቀው የፍርሃት አዘቅት ውስጥ በመግባት ራሱን በሽንፈት ውስጥ ያገኘዋል፡፡
ወደ ኢትጵያችን ታሪክ ስንመጣ ደግሞ በሁለቱ ጸረ ወረራ ታሪኮቻችን ውስጥ በውጊያው አውድ ላይ ነው ፤ ጀግኖች የተፈጠሩት:: እጅግ ታጥቆ የመጣው ጠላት በቅድሚያ የፈጠረው ፍርሃት ነበረ፡፡ ወራሪነቱን፣ ባርነትን በማስወገድ፣ በሥልጣኔና በሁሉን አዋቂነት ካባ ለብጦ ለነፃነታችሁ መጣሁ እንጂ ለወራሪነት መጣሁ አላለም፡፡
ያኔ ታዲያ ሁሉም ሕዝብ ተቃውሟቸው ነበር ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ በሁለተኛው የኢትዮ ኢጣሊያ ጦርነት (በ1928-1933 ) ወቅት ከጠላት ጎን ያደሩ ሰዎች ይሠጡት የነበረው ምክንያት አንደኛ ጣሊያን በማይገመት ሁኔታ የመሣሪያ የበላይነት አላት፡፡ ሁለተኛ ስልጡኖች አይደለንም፡፡ ሦስተኛ በነበረው የኢትዮጵያ አስተዳደርም አልተደሰትንም የሚሉ ምክንያቶች እንደሚያቀርቡ ጥርጥር አልነበረውም ፡፡
በወቅቱ በአማርኛ እየታተመ «የቄሳር መልዕክተኛ» ተብሎ ይሰራጭ በነበረው ጋዜጣቸው ላይም ይኸው ሃሳባቸው በስፋት ተገልጾ ይጻፍ ስለነበረ ብዙዎች እጃቸውን በፍርሃት ሰብስበው ተቀምጠው ነበረ፡፡ ያልተገነዘቡት ነገር ግን እነዚህም ሰዎች በሃሳቡ እንኳን ቢስማሙም ጣሊያን ራሱ በባእድ መሬት ስላለ ፍርሃቱ እንደነበረበት አለማስተዋላቸው ነው፡፡
ምንም ቢሆን በሰው አደባባይ ላይ ብትጎማለልም በየሰው ጓሮና ጓዳ ምን እየተዶለተ እንዳለ መጠርጠር የአባት ነው፡ ፡ እንዲያውም እኮ «የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም» ብቻ ሳይሆን «የተወጋ ዝም ቢልም የወጋ እረፍት የለውም» ፍርሃት አለበት ፡፡ እሰው ቤት ገብቶ ምን እረፍት ይኖራል ፡ ፡ ይህም ፍርሃት በየካቲት 12 /1929 በአዲስ አበባ በአንዲት ጀንበር በጣሊያን ፋሺስቶች የተፈጸመውን ዘግናኝ እልቂት ያስታውሷል፡፡
ያም እልቂት የተነቀነውን የጣሊያንኖች የወራሪነት ጥርስ አነቃንቆት ከሦስት ተጨማሪ ዓመታት በላይ በአትዮጵያ ምድር እንዳይቆዩ ነው፤ ያደረጋቸው፡፡
ፈርተው ለጠላት ያደሩትም በጊዜው የወጣላቸው ቀንና የሰጡት የሰበብ ድርደራ ፉርሽ ሆኖባቸው በመጨረሻ ሃፍረት ውስጥ ጨምሯቸዋል፡፡ የስጋታችን ምንጭ ጠላት የምንለውን ኃይል በአእምሯችን አግዝፈን ከማየት የሚመነጭ የተኳለ ፍርሃት ነው፡፡
በዚያ የወረራ ዘመን ፣ ጎንደርን ይገዛ የነበረው «ጄኔራል ናዚ» ሀገር ሁሉ በ1933 ዓመተ ምህረት ሚያዝያ 27፣ ነፃ ሆኖ ባንዲራችን ሲውለበለብ እርሱ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1934 ዓመተምህረት ነው ፤ ጎንደርን የለቀቀው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ኃይለኛ አርበኞች ዙሪያውን ከብበው ስላስጨነቁት መውጫ አጥቶ ጭምር እንደነበረ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? ፍርሃትህን ወዲያ ጥለህ ስትደፍር ያስጨነቅህን ፍርሃት ታስጨ ንቀዋለህ እንጂ እንደፈራህ አትቀርም ፡፡
ብዙ ጊዜ የፈራናቸውን ነገሮች ስንገልፃቸው ውስጣቸው ባዶ ሆኖ የምናገኛቸው፣ ቀደም ሲል ግን ሕይወትን በተስተካከለና ከፍርሃት በጸዳ ዓይን ሳንመዝናት በመቆየታችን ነው፤ ፍርሃት ቤቱን ሰርቶ የወዘወዘን ፡፡
ልብ ካልን ፍርሃታችንን አሸንፈን ፤ በጀግንነት ብልሃት የምንጓዛቸው መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ ወጣቱ የሁልጊዜ ፍርሃቱ የ«አልችለውም» እና «እኔ ገና ነኝ» የሚል መንፈስ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር የሚያስጠላውን ደፍሮ የሚወደደውን ፈርቶ ነው፤ የሚኖረው፡፡ የሚያስጠሉትና የማያዋጡትን ነገሮች ለመድፈር ያበቃው «እችላለሁ ባይነት» እንዴት ተገቢ ለሆኑ ነገሮች ፍርሃትን አዳበረ፤ ስንል መልሱ፣ በትንሹ ለማስተዋል ያለመቻል ጉዳይ የፈጠረበት ክፍተት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በፊደል እንኳን ብናየው «አይቻልም» ን ለማስቀረት ከፊት «አ» ን እና ከኋላ «ም» ን ማውጣት በቂ ነው፡ ፡ የሚቀረው «ቻል» ነው፡፡
የማይቻል መልካም ነገር እንደሌለ ሁሉ ፤ የማይወጡት ጋራ የለም ፤ የማያልፉት ማዕበል የለም ፤ የማይደፈር ግንብ የለም ፡፡ ጋራውም ፣ ማዕበሉንም ግንቡንም በግል ባይቻል በተባበረ ኃይል መውጣት ይቻላል፡፡ ወደ አሰብነውም ግብም እንደርሳለን ፡፡ እርሱም የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ የሆነውን ፣ እግዚአብሔርን ከመፍራት ፣ ውጪ ክፉ ፍርሃትን ሁሉ ወጋሁ!!
ለሳምንት በሌላ መጣጥፍ ወደ እናንተ እደርሳለሁ እስከሳምንት፣ ቸር እንሰንብት !!
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2011
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ