ቅድመ -ታሪክ
አዲስ አበባ ቢወለዱም ዕድሜያቸው በወጉ ሳይጠና ወደ ገጠር ሊሄዱ ግድ ሆነ። የዛኔ ስልጤ አካባቢ የሚኖሩት ዘመዶቻቸው አቅም ደህና የሚባል ነበር። ይህ መሆኑ ደግሞ ለሕፃኑ አስተዳደግ የሚበጀው ገጠር መሆኑን ታምኖበት ወደ ስፍራው እንዲጓዙ ተወሰነ።
ወቅቱ እንደ አሁኑ ሥልጣኔና ዘመናዊነት የሚታይበት አልነበረም። ከተሞች በወጉ ያልሰፉበትና መንገዶች ሁሉ በአግባቡ ያልተሰሩበት 1936 ዓ.ም። በወቅቱ ካሰቡት ለመድረስ ረጅሙን መንገድ በእግር መኳተንና በበቅሎና ፈረስ መጓዝ ግድ ነው። ሕፃኑ መሀመድም በእናታቸው እቅፍ ሆነው ስልጤ ከሚገኙ አያቶቻቸው ዘንድ የደረሱት በዚህ መልኩ ተጓጉዘው ነበር።
ትንሹ መሀመድ ከዚህ በኋላ ቀሪው ዘመናቸው በዚህ ስፍራ እንዲሆን ተወስኗል። በቦታው ደግሞ ያሻቸውን ለማግኘትና የገጠሩን ሲሳይ ያለአንዳች ከልካይ ለመውሰድ ይቻላቸዋል። አያቶቻቸውም ቢሆኑ እሳቸውን መሰል የልጅ ልጅ ማሳደጋቸውን ወደውታል።
በሁለት አያቶች እጅ ተሞላቀው ያደጉት መሀመድ ልጅነታቸውን ጨርሰው ክፉ ደጉን መለየት ሲጀምሩ የአዋቂዎች ጨዋታ ይስባቸው ያዘ። ለእሳቸው ይህ ዕድሜ ዘመዶቻቸውን ይበልጥ ያውቁበትና ስለ አዲስ አበባ መልካምነት ሲወራ የሰሙበት ድንቅ ጊዜ ሆነ። በተለይም የቤቱ ታላቅ ልጅ በአዲስ አበባ ይኖራል መባሉ ጆሯቸውን ሳበው። ነጋ ጠባ ስለ ከተማዋ ሲወራ የሚሰሙት ታሪክም ያጓጓ ያስደስታቸው ጀመር።
አሁን መሀመድ ዕድሜያቸው ከፍ ማለት ጀምሯል። በየጊዜው የሚመዘዘው ቁመታቸውም ያሉበትን ለውጥ ይመሰክር ጀምሯል። ይህን ያወቁት የአዲስ አበባው ታላቅ ወንድም ታዲያ ስለሳቸው ብዙ ጉዳዮችን አሰቡ። ከገጠር ኑሮ ይልቅ የከተማው እንደሚሻል አምነውም ሌሎችን አማከሩ። ምክራቸውን ሰምተው በሀሳባቸው የተስማሙ ዘመዶችም መሀመድን ይዘው አዲስ አበባ እንዲጓዙ ፈቀዱላቸው።
ትንሹ መሀመድና ታላቋ አዲስ አበባ በአጭር ቀናት ውስጥ ተግባቡ። የገጠር ኩራዝ የለመዱ የሕፃኑ ዓይኖች የከተማውን ብርሃን ባዩ ጊዜ በእጅጉ ተማረኩ። ይህ በሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥም መሀመድ ትምህርት ቤት ተመዝግበው ቀለም ሊቆጥሩ ወደ ትምህርት ቤት ተላኩ። ይህ ጊዜ ሺህ ዘጠኝ መቶ አርባዎቹ አካባቢ ነበር። ወቅቱ በጥቂት ትምህርትቤቶች ጥቂት ተማሪዎች የነበሩበት በመሆኑ ለገጠሩ ሕፃን መልካም የሚባል አጋጣሚ ሆነ።
የእነ መሀመድ ቤተሰቦች የሕይወት መክሊት የተቃኘው በንግድ ሥራ ላይ ሆኗል። ብዙዎቹ ከተማ ዘልቀው ኑሮን ሲጀምሩ መነሻ ሰበባቸው መነገድና ከፍ ሲልም አትርፎ መክበር ነው። መሀመድ ይህን እውነት በቅርብ እያዩት አድገዋል። የእሳቸው የኑሮ መንገድ ደግሞ ከሌሎች ተለይቶ በትምህርት ተጀምሯል። ይህ ደግሞ ከልብ እያስደሰታቸው ነው።
አሁን መሀመድ እንደሌሎች ዘመዶቻቸው በላባቸው ወዝ እንዲያድሩ አልተገደዱም። በእሳቸው ዕድሜ ያሉ ባልንጀሮቻቸው ሕይወትን ለመግፋት በጉልበታቸው ማደር የሚጀምሩት ገና በማለዳው መሆኑን ጠንቅቀው ያውቋታል። ገንዘብ ለማግኘትና ጥቅሙን ለማጣጣም ልፋቱን የሚጀምሩት በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ግፊት ነው። እሳቸው ግን መንገዳቸውን ለይተው ትምህርት ቤት መመላለስ ይዘዋል።
መሀመድ ኑሯቸውን በወንድማቸው ቤት አድርገው መማር ከጀመሩ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁን ደግሞ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ከጊዜያት በኋላ ዓመታቱን አጠናቀው በዝና እንደሚያውቋቸው አንዳንዶች ታዋቂ መሆን ይፈልጋሉ። ይህን ትኩስ ስሜት በወጉ አጣጥመው ሳይጨርሱ ግን የመሀመድ የሕይወት መንገድ ሊቀየር ግድ ሆነ።
ድንገት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ የወሰኑት መሀመድ ባልታሰበ ጊዜና ቦታ ራሳቸውን ከንግድ ሥራ ላይ አገኙት። ይህ በሆነ ማግስትም ትምህርት ይሉትን ጉዳይ እርግፍ አድርገው ሩጫቸውን በአዲሱ ሥራ ላይ አፈጠኑ። በወቅቱ ፒያሳ አካባቢ በጣልያኖች ተከፍቶ በነበረ አንድ ኬክ ቤት ተቀጥረው አስተናጋጅ መሆናቸው ለኪሳቸው ገንዘብን አረጠበ። የሚከፈላቸው ደመወዝ ራስን ከማስቻል አልፎ ለሌሎች መትረፉን ሲያውቁትም ሙያውን ከልብ ወደዱት።
አሁን መሀመድና ትምህርት ዳግም ላይገናኙ ተለያይተዋል። ልክ እንደ ዘመዶቻቸው ሰርቶ ማደርን የመረጡት ወጣት የተሻለ ነገን እያሰቡ የጀመሩትን ሥራ አጠንክረዋል። ይህ ህልማቸው ደግሞ ጥቂት ቆይቶ በራሳቸው እንዲቋቋሙ ዕድል ሰጣቸው። የጀመሩትን የመስተንግዶ ሥራ ተወት አድርገውም የወንዶች ጸጉር ቤት ከፈቱ። ደንበኞችን እያከሉና፣ አቅም እየፈጠሩም በቂ የሚባል ጥሪት ያዙ።
ይህ ከሆነ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ትዳር መስርተው ጎጆ የቀለሱት መሀመድ ሕይወታቸው በልጆች በረከት ታጀበ። ቤተሰብ በማስተዳደርና ሌሎች ዘመዶቻቸውን በማገዝም ዓመታትን ቆጠሩ። ዘመን ተለውጦ ጊዜ ሲሻሻል ደግሞ በከተማዋ ዘመናዊ ቤት ገንብተው የተሻለ ሀብት አፈሩ። አሁንም ከንግድ ሥራ ያልራቁት ሰው ቀሪውን ዕድሜያቸውን የሚገፉበት አማራጭ አላጡም። በመርካቶ ገበያ አንድ መደብር ከፍተው የቡና ንግድ ጀመሩ። በነዚህ የድካምና የልፋት ዓመታት መሀል አስራ ሁለት ልጆችን ያፈሩት አንጋፋ በልጅ ልጆቻቸው ጭምር ታጅበው ደስታን ማጣጣም ያዙ።
መሀመድ የንግድ ሥራቸውን በጀመሩበት አጋጣሚ ራሳቸውን ለመጠበቅ በሚል የያዙት ካሊቨር ሽጉጥ ዓመታትን አብሯቸው ገፍቷል። ሁሌም ስለንብረታቸውና ስለራሳቸው ደህንነት ስጋት በገባቸው ጊዜም ይህን ሽጉጥ ያስቡታል። በግቢያቸው ያለሰዓት የሚሰማ ኮሽታን ቀድመው የሚለዩት አዛውንት ከሁሉም በፊት ወጥተው ግቢያቸውን ቃኝተውና ሰላሙን አረጋግጠው መመለስን ልምድ አድርገዋል።
ጠንካራው ሽማግሌ መቼውንም ቢሆን ግቢያቸውን ሌባ ደፍሮት አያውቅም። እሳቸው ሰርተው በማደር ያምናሉና «ሰርቀው ተያዙ» በሚባሉ ሰዎች ማንነት ይናደዳሉ። ለእሳቸው ሌብነትና ዝርፊያ ሁሌም ነውርና ሊሰሙት የማይሹት ጉዳይ ነው።
የ2000 ዓ.ም አዲስ ዓመት እንደባተ የተለየ ድባብ ይስተዋል ጀምሯል። ይህ ጊዜ በመላው ሀገሪቱ የአዲስ ክፍለ ዘመን ማብሰሪያ ሆኖ የታወጀበት ነበር። በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዓመቱን በተለየ አስበው የኮሩበትና የተደሰቱበት የሚሌኒየም ዘመን።
ይህ ጊዜ በርካቶቹ የተለየ ጥቅም ለማግኘት የተሯሯጡበትና ማንነታቸውን ጭምር ለማስተዋወቅ የተጉበትም ነበር። የዚያኑ ያህል ደግሞ አንዳንድ ዘራፊዎች፣ የመንደር ሌቦችና ሌሎችም አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ሲጣጣሩ ታይተዋል።
ግንቦት 9ቀን 2000 ዓ.ም ሌሊት
ቀን በሥራ ሲተጉ የዋሉት መሀመድ ከድካማቸው አረፍ ለማለት ከአልጋቸው የተገናኙት ገና በጊዜ ነበር። አስቀድሞ እንቅልፍ በሚጥላቸው ጊዜ ደግሞ በድንገት መንቃትን ልምድ አድርገዋል። ሁሌም ቢሆን ከእኩለሌት በኋላ ያለውን ጊዜ አምነውት አያውቁም። ይህ ሰዓት ቤት ሰባሪ ሌቦች የሚመርጡት ጊዜ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ።
የዚያን ዕለት ሌሊትም በተለመደው ሰዓታቸው ነቅተው ነበርና ልባቸው ውጭ አድሮ ጆሯቸው ኮሽታን ሲለይ ቆይቷል። እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በእሳቸው ግቢም ሆነ በአካባቢው ምንም የተለየ ነገር አልነበረም። ሌሊቱ በጭርታ እንደተዋጠ በዝምታው ቆይቷል።
አስር ሰዓት አካባቢ ግን የአካባቢው ውሾች ድምጽ ከወትሮው የተለየ ሆነ። ያለማቋረጥ የሚያሰሙት ኃይለኛ ጩኸትም ለብዙዎች ትኩረት የሚስብ ነበር። አቶ መሀመድ ይህ ዓይነቱን ድምጽ በደንብ ያውቁታል። አብዛኞቹ ውሾቹ ሌሎችን ውሾች ሲያዩና ሰዎችን ሲመለከቱ የሚያሰሙት ድምጽ የተለያየ ነው። በእሳቸው ግምትም የውሾቹ ሁኔታ ውሾችን ስላዩ ሳይሆን ሰዎችን ስለተመለከቱ ነው።
አዛውንቱ ጆሯቸውን ጣል አድርገው እንቅስቃሴዎችን ማድመጥ ቀጥለዋል። በግቢያቸው ልጃቸው ለሥራ የሚጠቀምባት ቶዮታ መኪና መቆሟን ያውቃሉ። የሰርቪስ ቤቶችና ከደጅ የተረሱ ዕቃዎችም ቢሆኑ በቀላሉ ለዝርፊያ ተጋላጭ እንደሚሆኑ አልጠፋቸውም። ይህን እያሰቡ የሳሎናቸውን በር ከፈቱ። መብራት ሳያበሩም ከበረንዳቸው ቆመው ኮሽታና ኮቴ ስለመኖሩ አደመጡ።
መሀመድ ሁሌም አካባቢያቸውን በጠረጠሩ ጊዜ ባዶ እጃቸውን አይወጡም። እንደ ብዙዎቹ ዱላ ቢጤ የመያዝ ልምድም የላቸውም። በእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ለክፉ ቀን ብለው ያኖሩትን ሽጉጥ ከጎናቸው አይለዩትም። እሱን ከያዙ ልጆቻቸውን መቀስቀስና ሌሎችንም መጥራት አያሻቸውም።
የዚያን ዕለት ሌሊትም የሆነው እንዲሁ ነበር። «ካሊቨር» ሽጉጣቸውን ይዘዋል። ዓይኖቻቸው በርቀት እያስተዋሉ ኮሽታ የሚያደምጡ ጆሮዎቻቸው ነቅተዋል። እርግጠኛ ባይሆኑም መኪናዋ በቆመችበት አካባቢ ድምጽ መኖሩን ገምተዋል። ይህን ለማረጋገጥም በወጉ ማድመጥ ይኖርባቸዋል።
አሁንም ትንፋሻቸውን ሰብስበው ወደጠረጠሩት አቅጣጫ አነጣጠሩ። ቆየት እያለ የሚሰማው ኮሽታ የሰዎች ሹክሹክታ ታክሎበት ወደ ጆሯቸው ደረሰ። ይህን ሲያውቁ ቀስ እያሉ ተራመዱ። እንደገና ቆም ብለውም የድምጹን መኖር በጥንቃቄ ለዩ። አልተሳሳቱም፤ ሦስት ሰዎች ከመኪናዋ ሆድ ስር ሆነው መላው አካሏን እየበረበሩ ነው።
መሀመድ ልባቸው በድንጋጤ ይመታ ያዘ። ወዲያው ደግሞ ንዴትና እልህ ተናነቃቸው። አሁን ግቢያቸው በሌቦች መደፈሩን አውቀዋል። ከእነሱ ጋር ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ሌላ ምርጫ የላቸውም። ቀረብ ሲሉ ሦስቱም ፊታቸውን እንደሸፈኑ አስተዋሉ። አጠገባቸው ደርሰውም ሌባ… ሌባ.. ቁም ቁም ፣ ቁም፣ ሲሉ በጨኸት አንባረቁ። ድንገት የተደረሰባቸው ሌቦች ድምጽ ሲሰሙ የያዙትን ጣሉት። ፊት ለፊት ሰው መኖሩን ሲመለከቱም በእጃቸው የገባውን ሰብስበው በትልቁ በር ለመውጣት በብረቱ ላይ ተንጠላጠሉ። ከሦስቱ ጎረምሶች አንደኛው ግን ወደ ኋላ ቀረት አለ። ጥቂት ቆይቶ ግን እነሱ ጥለውት የሄዱትን ቀሪ የመኪና ዕቃ ሰብስቦ ተከተላቸው።
ሁለቱ ግንቡን ዘለው ከመሬት እንዳረፉ ሦስተኛው ባልንጀራቸው የዘረፈውን እንደያዘ ከግቢው ባለቤት ጋር ተፋጠጠ። መሀመድ አሁንም ቁም… ቁም… ሌባ፣ሌባ፣ሌባ እያሉ ተከተሉት። ያልገመተው ነበር። ደርሰው ሲይዙት ሊታገላቸው ሞከረ። ወዲያው አንድ ጥይት ወደሰማይ ተኩሰው ከግብግቡ ተላቀቁ። ይህኔ በድንጋጤ በርግጎ ወደ ጓደኞቹ መሮጥ ጀመረ።
አቶ መሀመድ ሌባው ከእጃቸው አፈትልኮ ግንቡን መዝለሉን ሲያዩ በፍጥነት የግቢውን በር ከፍተው ከፊት ለፊት ቀደሙት። ይህኔ ደጅ የነበሩት ሁለቱ ካሉበት ሆነው ለጓደኛቸው አስቸኳይ ትዕዛዝ ሰጡ። በያዘው ጩቤ ፈጥኖ እንዲጠቀም ሲሉም «ውጋው… ውጋው…እያሉ ጮሁ።
ጓደኛቸው ምክራቸውን ሰምቶ አዛውንቱን ለመያዝ ተንደረደረ። ይህን ከማድረጉ በፊት ግን አቶ መሀመድ ካሊቨር ሽጉጣቸው ከእጃቸው ገባ። ሊወጋ የተዘጋጀውን እጅ መንገዱን ለማሳትም ወደጎን ተነጣጠረ። ጥይቱ እንደታሰበው ሆኖ ወደ እጁ አላመራም። አቅጣጫውን ስቶ በቀኝ ጡቱ ላይ አረፈ ።
የጥይቱ ድምጽ እንደተሰማ የአቶ መሀመድ ቤተሰቦች በድንገት ደረሱ። ይህን ተከትሎም በአካባቢው የነበሩ ሁለቱ ዘራፊዎች እየተሯሯጡ አመለጡ። ተመቺው ከመሬት እንደወደቀ የደረሱት የመሀመድ ልጆችም በእጆቹ ላይ የነበሩትን የመኪና ዕቃዎች ተመልክተው ሰውዬው ሌባ መሆኑን ገመቱ።
ልጆቹ ወደወደቀው ሰው ቀረብ ብለው ትንፋሹን ሊያደምጡ ሞከሩ። ግለሰቡ በሕይወት አለመኖሩን ለማረጋገጥ አልቸገራቸውም። ሁሉም በድንጋጤ ክው ቢሉም ቀጣዩን ለማድረግ ጊዜ አላባክኑም። አባታቸው እጃቸውን ለሕግ ይሰጡ ዘንድ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመሩ።
የፖሊስ ምርመራ
አቶ መሀመድና ቤተሰቦቻቸው ኮልፌ ቀራንዮ ፖሊስ ጣቢያ ደርሰው ስለሆነው ሁሉ አስረዱ። አዛውንቱ ነጋዴም በሰጡት ቃል ያጋጠማቸውንና የፈጸሙትን አንድም ሳያስቀሩ ተናገሩ። በእጃቸው የነበረውንና በሕጋዊ ፈቃድ ያወጡትን ካሊቨር ሽጉጥም ለሚመለከተው አካል አስረከቡ።
ፖሊስ ከስፍራው ደርሶ የሟችን አስከሬን አንስቷል። በኪሱ ከነበረው የሞባይል ስልክ በቀር ስለማንነቱ የሚገልጽ አንዳች መረጃ ግን አላገኘም። በወደቀበት አካባቢ የተገኘው አንድ የጥይት እርሳስና የብሎን መፍቻዎች በኤግዚቢት ተመዝግበዋል። በወቅቱ በግቢው ከነበረችው ቶዮታ መኪና የግራና ቀኝ ስፖኪዮ፣ አራቱም መብራቶች፣ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ጌጅ፣ የዳሽ ቦርድና ሌሎችም ንብረቶች መዘረፋቸው ተረጋግጧል። ሟች መልኩ ጠይም፣ ቁመቱ ረጅምና ቀጭን ነው። ጸጉሩ ከርዳዳ ሲሆን አዲስ ሰማያዊ ጂንስ ሱሪ በአዲስ ጫማ አድርጓል።
ፖሊስ በኪሱ በተገኘው ሞባይል ወደ እርሱ የደወሉ ሰዎችን ለማግኘት በሚል ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። በወቅቱ እሱን ፈልገው የደወሉም ሆኑ እሱ የደወለላቸው ሰዎች አልነበሩም። አብረውት ለዘረፋ ወደ ግቢው የገቡ ጓደኞቹን ለማሰስ የተደረገው ሙከራም ለጊዜው ምንም የተሳካ አልነሆነም።
በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 09/01/2000 የተከፈተው ሰነድ ዕለታዊ መረጃዎችን እየመዘገበ ነው። በመርማሪ ፖሊስ ረዳት ሳጂን ፈቃዱ ገዛኸኝ የሚመራው ቡድን በስፍራው ደርሶ ተገቢውን የቴክኒክ ምርመራዎች በማድረግ ለሚመለከተው ክፍል አስተላልፏል። ሟችን «አውቀዋለሁ» የሚል ወዳጅ ዘመድ አለመገኘቱም በከተማዋ ማዘጋጃ በኩል የቀብር ሥርዓቱ እንዲፈጸም ተደርጓል።
ይህ ድርጊት ካለፈ ከጥቂት ቀናት በኋላ የሆነውን ከሰሙት መካከል አንዲት አዛውንት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ደረሱ። በእጃቸው ያለውን ጉርድ ፎቶግራፍ አሳይተውም በጥገኝነት አብሯቸው ይኖር የነበረ ወጣት ጓደኞቹ ቤት ለማደር እንደወጣ ያለመመለሱን አስታወቁ። ፖሊስ ፎቶግራፉን ካየ በኋላ ከሟቹ ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን አረጋገጠ። ሴትዬዋን ለተጨማሪ ጥያቄዎች አቆይቶም ሁኔታዎችን መረመረ።
ሟች ጎይቶም ሀጎስ ከሦስት ዓመት በፊት ከትውልድ ሀገሩ ትግራይ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ነበር። በነዚህ ዓመታትም ከቤተሰቦቹ ጋር ግንኙነት አልነበረውም። አዛውንት አባቱ የልጃቸውን መሞት ሰምተው ካገራቸው ሲመጡም የተናገሩት እውነት ይህንኑ ነበር።
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2011
መልካምስራ አፈወርቅ