በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ዕድሜያቸው የገፋ እና እይታቸው ገንዘብ ላይ የሆኑ ተጫዋቾች ይዞ ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን መፍጠር እንደማይቻል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች ኘሪሚየር ሊግ ውድድር የአፈፃፀም ግምገማ ሥነ-ሥርዓት ትናንት በኢትዮጵያ ሆቴል ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ የአገራችን እግር ኳስ ዕድሜያቸው በገፋ፣ እይታቸው ገንዘብ ላይ በሆኑ ተጫዋቾች ፤ እንዲሁም በጊዜያዊ መርሐ ግብር በተጠመዱ ክለቦች፣ አሰልጣኞች እና የክለብ ባለቤቶች የተከበበ ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን መገንባት የሚታሰብ አይደለም ብለዋል ።
እንደ ከሎኔል አወል ገለፃ፤ እነዚህ አካላት በተጨባጭ ምን አይነት ተጫዋች ለክለብም ሆነ ለብሔራዊ ቡድን እናፍራ በሚለው አስተሳሰብ ውስጥ አለመሆናቸው። የብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሰረት የሆኑት ክለቦች ትኩረት አድርገው ካለመሥራታቸው ጋር ተያይዞ ችግር ተፈጥሯል። በመሆኑም ስፖርቱ ውጤታማ እንዳይሆን ወደ መሬት ወርደን በተጠናና በታቀደ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በዚህ መሰረትም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የእግር ኳሱን ልማት ለማሳደግ በአራት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ የተጠና ዕቅድ በመዘርጋት ወደ ተግባር የሚገባ ይሆናል።
በ2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች ኘሪሚየር ሊግ እና ከዚያ በታች ለሚገኙ ውድድሮች የተለየ ትኩረት ተሰጥቷል። ፌዴሬሽኑ ከሁሉም ውድድሮች ቀዳሚው ትኩረት የሚያስፈልገው ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች መሆኑን በፅኑ ያምናል። ፌዴሬሽኑ ብቻም ሳይሆን ክለቦች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ማድረግ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ ከዚህ ውጭ ፕሪሚየር ሊግ ተብሎ ሌሎች ስሞችንም አውጥቶ መንቀሳቀሱ ለእግር ኳሱ ቁልፍ መፍትሄ እንደማይሆን አስገንዝበዋል።
«ፕሪሚየር ሊጉም ሆነ ብሔራዊ ሊጉ ምናልባትም ከዓለም አቀፍ ውድድር እንዳንነጠል ካልሆነ በስተቀር የተገኘ ውጤት የለም። ከሞራል፣ ከገንዘብ፣ የትውልድ ኪሳራ የተለያዩ ችግሮች ከማስከተል በቀር አገሪቷ የምትፈልገው የእግር ኳስ ዕድገትም አልመጣም። ምክንያቱም ያሉን ተጫዋቾች በተጨባጭ የሚታወቁ በመሆኑና፤ የተጫዋቾቹ ምንጭም ከየት እንደሆነ ድብቅ አይደለም። »ሲሉ ተናግረዋል
የብሔራዊ ፌዴሬሽን የውድድሩ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ዘለቀ በበኩላቸው፤ ፌዴሬሽኑ ክለቦች ከ20 ዓመት በታች ፣ ከ17 ዓመት በታች፣ 13 ዓመት በታች፣ በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በሰፈር ጨዋታዎች ላይ ጥናትን መሰረት ያደረገ ዕቅድ አውጥቶ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ወደተግባር ይገባል ብለዋል ። በተጨማሪም ዕቅዱን ተግባራዊ ከማድርጉ ጎን ለጎን በተለየ ሁኔታ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል። ውድድሩን እንደ ተለጣፊ ሳይሆን እንደ ዋና ውድድር በመመልከት የሚሠራ መሆኑና ክለቦችም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት እግር ኳሱን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገን ዝበዋል።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
ዳንኤል ዘነበ