በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ግቢ ውስጥ አገልግሎት የማይሰጡ ተሽከርካሪዎችንና ቁሳቁሶችን ሳር በቅሎባቸው፤ ዳዋ ለብሰው ማየት የተለመደ ነው። እድሉን አግኝቶ ወደ አንዳንዶቹ ተቋማት ግምጃ ቤት ጎራ ላለ ሰው ደግሞ በርካታ አገልግሎት የማይሰጡ ብቻ ሳይሆን፤አገልግሎት መስጠት የሚችሉም ጭምር ጥቅም ሳይሰጡ ተከማችተው ያገኛሉ።
መንግስት ተቋማት በእጃቸው ያለን ንብረት በጥንቃቄ የመያዝ፣ የመጠቀም፣ የመቆጣጠርና ንብረቱ አገልግሎቱ ሲያበቃ በወቅቱና በተገቢው መንገድ የሚያስወግዱበት ሥርዓት ዘርግቷል።
ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ ተቋማት በየግቢያቸውና በየግምጃ ቤታቸው ውስት ካለ አገልግሎት ለዓመታት ያህል የተቀመጡ የተለያዩ መሳሪያዎች፣ ተሽከርካሪዎችና ቁሳቁሶች በርካታ ናቸው። የችግሩ ምንጭ ከግዢ እንደሚጀምር ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ እናም ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋልና የሚባክነውን ንብረት ለማስወገድ በመንግስት በኩል የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳስባሉ።
በፌዴራል የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ መቅደስ ብርሃኑ እንደሚያብራሩት በአሁኑ ወቅት በርካታ ንብረቶች እየተወገዱ ያሉት መወገድ ከሚገባቸው ጊዜ ዘግይተው ነው። በአንዳንድ ተቋማት ደግሞ በማስወገድ ወቅት ሙስና ይፈጸማል፡፡ በሙስና ምክንያትም አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ እቃዎችና ምንም አገልግሎት ያልሰጡና አዲስ ሆነው የሚወገዱም አሉ።
ለዚህ ችግር አንዱ መነሻ ደግሞ በግዢ ወቅት የሚፈጠር ግልጽኝነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሰራር ነው። በአንድ ወገን ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው እቃ አይገዙም፡፡ ይህም የሆነው ዕቅዳቸው ከበጀታቸውና ከሚሰሩት ስራ ጋር የተስማማ ባለመሆኑ ነው። አሁንም ድረስ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ተቋማት በወቅቱ ሊገለገሉባቸው የማይችሉ እቃዎችን ጭምር
ገዝተው ሲያከማቹ ይታያሉ። ግማሾቹም የሚገዟቸው እቃዎች ለሚጠበቅባቸው ተግባር የሚያበቃ ጥራት የሌላቸው በመሆኑ ወዲያው አገልግሎት ሳይሰጡ ይበላሻሉ፡፡ አልያም በስራ ወቅት ሰራተኛውን ለተለያዩ ችግሮች ይዳርጋሉ።
ተቋማት ጥራት ያለው የእቃ ግዢ እንዲፈጸሙ በኤጀንሲው በኩል የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። ከእነዚህም መካከል በቅርቡ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር 351 ለሚሆኑ ቋሚና አላቂ እቃዎች ደረጃ ወጥቷል። እነዚህ ደረጃዎች ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሲተገበሩ አልነበረም፡፡
አሁን ግን ተግባራዊ ለማድረግ ከስራው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ላላቸው ባለሙያዎችና ሃላፊዎች በመጀመሪያ ዙር ለ75 የመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ስለ ዕቃዎች ደረጃና ጥራት ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል። በቀጣይም በጀት ዓመትም ለሁሉም ተቋማት ባለሙያዎች ስልጠናው ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም መሰረት ማንኛውም የመንግስት ባለ ባጀት መስሪያ ቤት የእቃ ግዢ ሲፈጸም የምርቱን ዘመን፣ እቃው የተመረተበትን ግብአትና ሌሎችም በደረጃው የተቀመጡ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ መሆን ይኖርበታል።
ሌላው አዲስ እቃዎች ተገዝተው ምንም ጥቅም ሳይሰጡ ሲወገዱ ይታያል። አገልግሎት መስጠት እየቻሉም በመጋዘን ተቆልፎባቸው የተቀመጡ ጥቂት አይደሉም። ይሄ እንዴትና ለምን ተገዙ ምን ያህል ግዜ አገልግሎት ሳይሰጡ ቆዩ የሚለውን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።
በ2003 ዓ.ም የወጣው የፌዴራል የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር አዋጅና የንብረት አስተዳደር መመሪያ ማንኛውም ቋሚ እቃ ቢያንስ አገልግሎት እስከሚሰጥ በክምችት ሊቆይ የሚችለው ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ መሆኑን ያስቀምጣል። በአተገባበር ረገድ ሰፊ ክፍተት በመኖሩ ምክንያት ክትትልና ቁጥጥር በሚደረግበት ወቅት ለዓመታት ያለ ጥቅም የተቀመጡ እቃዎች ይገኛሉ። ይህ ለምን ሆነ ተብሎ ለተቋሙ ጥያቄ ሲቀርብ ከሰራተኛ መልቀቅና ሙሉ መረጃ ካለመገኘት ጋር በተያያዘ መቼና ለምን እንደተገዙ የማይታወቅበትም ሁኔታ ይስተዋላል ሲሉ ችግሩ ስር የሰደደ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል መወገድ ያለባቸው ንብረቶች በወቅቱ ካልተወገዱ ለጸሀይና ለዝናብ ይጋለጣሉ፤ ለዓመታት እየቆዩ ሲመጡ ደግሞ ተሽጠው የሚያስገኙት ዋጋ በጣም አነስተኛ ይሆናል። ጥቅም የማይሰጡ ዕቃዎች ሲከማቹ የተቋማት ግምጃ ቤትንም ያጣብባል። እነዚህ ችግሮችን ለመፍታት ኤጀንሲው በአዋጅ ቍጥር 649/2001 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተቋማት በእቅድና በህግ መሰረት ግዢ እንዲያከናውኑ ክትትል ያደርጋል።
የዕቃዎቹም አገልግሎት ጊዜ ሲያበቃ በሥርዓቱ እንዲያስወግዱ ደንብና መመሪያ በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ይህም ሆኖ ክፍተቱ ሰፊ በመሆኑ ለሙስናና ለመልካም አስተዳደርም ችግር የሚፈጥር ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም በመንግስት በኩል ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ደፋልኝ፤ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት አመት ከመንግስት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በሽያጭ ከተወገዱ ተሽከርካሪዎች፤ የቢሮ እቃዎችና የተለያዩ ቁሳቁሶች 93 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ይናገራሉ።
ይህም ሆኖ በየተቋማቱ ያለው የንብረት አወጋገድ ሥርዓት መፈተሽ እንዳለበት ያሳስባሉ። እንደ አቶ አቶ መልካሙ ገለጻ የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ንብረት የሚያስወግደው የተቋማት ሃላፊዎችን ውሳኔ ተቀብሎ በሽያጭ ብቻ ነው። ነገር ግን ከዚህ ውጭ እያንዳንዱ ተቋም የማይገለገልባቸውን ንብረቶች ሊያስወግድበት የሚችል ስድስት አይነት ሥርዓት አለው።
ከተቋማት በአገልግሎቱ በኩል በሽያጭ ንብረት እንዲወገድላቸው ሲጠይቁ የሚከተሉትን መስፈርቶች አሟልተው መሆን አለበት። በመጀመሪያ ደረጃ በስራቸው በሚያቋቁሟቸው ሁለት ኮሚቴዎች የሚወገደው ንብረት ይገመገማሉ። በዚህም የመጀመሪያው አምስት አባላት የሚኖሩት ኮሚቴ ንብረቱ አገልግሎት ላይ ሊውል አይችልም ብሎ ሲወስን፤ ሁለተኛው ደግሞ ገበያ ላይ ያለውን አዲሱን ተመሳሳይ ንብረት
መነሻ በማድረግ ለተወጋጁ ንብረት ያለበትን ደረጃ በተቀመጠው ቀመር መሰረት አይቶ ዋጋ የተምናል። ከዚህ በኋላ ተቋሙ ለአገልግሎቱ ሲያሳውቅ አገልግሎቱ በሚልካቸው ባለሙያዎች ሂደቱና እቃዎቹ ታይተው በግልጽ ጨረታ ይሸጣሉ።
ይህም የሚከናወነው በአንድ በኩል አገልግሎቱ በአመት ሁለት ጊዜ የሚወገድ እቃ አላችሁ ወይ ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ማንኛውም ተቋም ይሄ ንብረት እንዲወገድልኝ እፈልጋለሁ ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ ይሆናል። በዚህ መንገድ የሚወገዱት እቃዎች የነጠላ ዋጋቸው (የአንዱ እቃ) ከአንድ ሺ ብር በታች ሲሆንና አጠቃላይ በአንድ ጊዜ የሚወገደው እቃ ድምር ደግሞ ከመቶ ሺ በላይ የሚያወጣ ሲሆን ብቻ ነው።
በአብዛኛው ተቋማት ከተሽከርካሪ በቀር የተቀመጠውን ያህል ገንዘብ የሚያወጣ ንብረት ስለማይኖራቸው የሚያስወግዱት በራሳቸው መንገድ ነው። የፌዴራል መንግስት ንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 9/2003 የባለበጀት የመንግስት መስሪያቤቶች መተዳደሪያ ንብረቶች አገልግሎታቸው ሲያበቃና የማይጠቅሙ ሲሆኑ እንዴት መወገድ እንዳለባቸው ዝርዝር መመሪያዎችን አስቀምጧል።
በመመሪያውም ስድስት መንገዶች የተቀመጡ ሲሆን እነዚህም ንብረቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ሲሆን በጨረታና በሐራጅ ሽያጭ ይወገዳሉ፡፡ ንብረቱ ለሌላ የመንግሥት መስሪያቤቶች፤ ለትምህርት ቤቶች፤ ለዩኒቨርሲቲዎች፤ ለምርምር ተቋማትና ሌሎችም የሚጠቅም ሆኖ ሲገኝ በማስተላለፍ ማስወገድ ይቻልል፡፡
የሚወገደው ንብረት በመልካም ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ወይም ሊጠገኑ ለሚችሉ ሌሎች ተመሳሳይ ንብረቶች በመለዋወጫ ዕቃነት እንዲያገለግል ሲፈልግ መጠቀም የሚቻል መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ የሚወገደው ንብረት በንብረት ማስወገዱ ሂደት የሚገኘው ገቢ ወጪውን የማይሸፍን ሆኖ ከተገመተ ወይም ንብረቱ በቋሚ ንብረትነት ሊወገድ የማይችል ከሆነ በውዳቂ ዕቃ መልክ መሸጥ ይፈቀዳል።
ዕቃዎቹ ለምንም አገልግሎት መዋል የማይችሉ ሆነው ሲገኙ ደግሞ በመጣል ወይም በመቅበር ማስወገድ ይችላሉ፤ ንብረቱ በሌሎች የመንግስት ተቋማት የሚፈለጉና የቅርስና የባህል ጠቀሜታ ሲኖራቸው በስጦታ ማስተላለፍ የሚቻልበት ዕድልም አለ።
እነዚህ መንዶች ግን በራሳቸው ችግር የሌለባቸው ቢሆንም በአፈጻጸም በኩል ክፍተት ይታያል፡፡ በተለይ ተወጋጅ ንብረቶች በዝቅተኛ ዋጋ ሲሸጡና መወገድ ባለባቸው መንገድ ሳይሆን ለግለሰቦች ልዩ ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ እየተወገዱ ናቸው የሚል ቅሬታ ሲነሳ ይስተዋላል። በመሆኑም በመንግስት በኩል የሚወገዱትን እቃዎች መከታተል ብቻ ሳይሆን በየተቋማቱ ያሉ ግምጃ ቤቶች የያዟቸውን እቃዎች ተገቢነት መፈተሽ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
« የአብዛኛው የተቋማት የማይጠቀሙበት ንብረት ተሽጦ ለመንግስት ተገቢ ገቢ ሲያስገኝ አይታይም። በመሆኑም ንብረቶችን መንግስት በስሩ ሊገለገሉ ለሚችሉት ማዛወሩ የበለጠ ፋይዳ አለው።» የሚሉት ደግሞ በደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ግርማ አበበ ናቸው።
ባለሙያው የራሳቸውን ተቋም ተሞክሮ መነሻ አድርገው እንደተናገሩት፤ እስካሁን የእኛ ተቋም ሽያጭ አከናውኖ አያውቅም፡፡ የማንጠቀምባቸው የማያገለግሉ እቃዎች ሲኖሩ በህግ መሰረት ንብረት አገልግሎትን አስፈቅደን ለትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት በስጦታ መልክ እንሰጣለን።
ለአብነትም ተቋማቸው በቅርቡም በርከት ያሉ ላፕቶፕና ሌሎች የኤሌክትሪክ እቃዎች ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስጠቱን ያወሳሉ። ዕቃዎቹን የተረከበው ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም ዕድሳት አድርጎ ለሚያስፈልጋቸው አካላት ያስተላልፋል። ይህ አይነቱ አሰራር ከሙስና የጸዳ ነው።
ሆኖም የሚወገድ ንብረት በተቋማት አማካኝነት ሲሸጥ ግን ከፍተኛ ሙስና ሲፈጸም ይታያል:: ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ የሚያገለግሉ እቃዎችና አዳዲስ ዕቃዎች ጭምር ተቀላቅለው ይሸጣሉ፤ ከገዢ ጋር በመመሳጠር አገልግሎት ያልሰጡ የታሸጉ እቃዎች ሳይቀሩ በጣም በዝቅተኛ ዋጋ ሲሸጡ ይታያል። በመሆኑም ለሌሎች ተቋማት ማዛወሩ ጠቃሚ ስለሆነ አስገዳጅ እስካልሆነ ድረስ ባይሸጥ ይመረጣል ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ