
አዲስ አበባ:- በ2016 በጀት ዓመት 46 ሺህ 571 የተሽከርካሪ አደጋ ተከስቶ ሦስት ሺህ 111 ሞት መመዝገቡን የመንገድ ደህንነት እና መንገድ ፈንድ ገለጸ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጀማል አባሶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤በ2016 ዓ.ም 46 ሺህ 571 የተሽከርካሪ አደጋ ተከስቶ ሦስት ሺህ 111 ሞት ተመዝግቧል። አምስት ሺህ 581 ከባድ አካል ጉዳት ደርሷል። ለአደጋዎቹ ቁልፍ ችግሮች ከሆኑት መካከል የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነትና ጥንቃቄ ጉድለት እንዲሁም የተሽከርካሪ ቴክኒክ ጉድለት 82 በመቶ ይሸፍናሉ።
አጠቃላይ ሞት በ2015 ዓ.ም ሦስት ሺህ 577 የነበረ ሲሆን፤ በ2016 ዓ.ም በ262 ሰው የመቀነስ ምልክት ማሳየቱን ጠቁመዋል። በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት ከአምናው ከእጥፍ በላይ ጨምሮ አራት ቢሊዮን ብር እንደሚገመት ተናግረዋል።
በ2015 በጀት ዓመት አምስት ሺህ 818 ከባድ አካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ የደረሰው የተሽከርካሪ አደጋም 37 ሺህ አካባቢ እንደነበር፣ በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት ደግሞ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ይገመት እንደነበርም አስታውሰዋል።
ዘንድሮ ሞት ቢቀንስም የተሽከርካሪ አደጋ ግን ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል። የፍጥነት ወሰን ቁጥጥር ላይ የተሻለ ሥራ መሠራቱንና የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ ትኩረት እንደሚሰጥም አመልክተዋል።
ለተሽከርካሪ አደጋዎቹ ቁልፍ ችግር ተብሎ በጥናት ከተለየው መካከል የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነትና ጥንቃቄ ጉድለት 68 በመቶ ይሸፍናል ነው ያሉት። የአሽከርካሪዎች የችሎታ ማነስ፣ ሃሰተኛ መንጃ ፍቃድ መጠቀም፣ በአግባቡ መሰልጠንና መሰል ችግሮች ህይወት እየቀጠፈ ነው ብለዋል።
የተሽከርካሪ ቴክኒክ ጉድለት ለአደጋው ካላቸው ድርሻ 14 በመቶ የሚሸፍን ችግር መሆኑን በጥናት መለየቱንም ነው የተናገሩት። የእግረኛ ክፍተት፣ ዜብራ ጠብቆ አለመሻገር፣ የመንገድ አለመመቻቸትና ሌሎች ችግሮችም ቀሪውን ድርሻ እንደሚይዙ አመልክተዋል።
14 የሚሆኑ ሕጎች ላይ ማሻሻያ እየተሠራ እንደሚገኝና ከእነዚህ መካከልም የትራፊክ ቅጣት መሻሻሉን፣ የካሳ ክፍያ አረቦን ጥናት ጸድቆ ወደ ተግባር መገባቱንም ተናግረዋል።
የትራፊክ ሕግ ዓለም አቀፍ ባህሪ አለው ያሉት ኃላፊው፤ የተባበሩት መንግሥታት ኮንቬንሽንና የአፍሪካ ቻርተርንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቁን አስታውሰዋል።
የትራፊክ አደጋ መከላከያ መስፈርቶችን (ስታንዳርዶችን) በማስጠበቅ ሞትን ለመቀነስ ለመሥራት ቃል ከገቡ የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት። የትራፊክ አደጋን ከመከላከል አንጻር የተሻለ ንቅናቄ እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል። ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ አደጋ ከሚያደርሱ ሀገራት ተርታ ትመደባለች ብለዋል።
ከሦስት ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት በተሽከርካሪ አደጋ የሚሞተው አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሰው እንደነበር፤ በዛን ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከአራት እስከ አምስት ሺህ ሞት ይመዘገብ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በ2020 ዓ.ም የተባበሩ መንግሥታት የትራፊክ አደጋ ሞትን በ50 በመቶ ለመቀነስ እቅድ መያዙን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ በየዓመቱ በ10 ሺህ ተሽከርካሪ ሞት ይመዘገብ የነበረው 43 የነበረ ሲሆን፤ ይህንን ወደ 10 ሰው ለማውረድ ታቅዶ ግቡን በ2015 ዓ.ም 25 ሰው ገደማ ማውረድ ተችሏል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት በተሽከርካሪ አደጋ መጠን በ10 ሺህ ተሽከርካሪ ሞት ደግሞ ወደ 20 ነጥብ ሰባት ማውረድ መቻሉንም ተናግረዋል።
የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጠው፣ በመንገድ የሚጠቀም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ለተማሪዎች ግንዛቤ ፈጠራ በመሥራት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ትኩረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
የቴክኒክ ምርመራና የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ሥራቸውን ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ ሊተገብሩ ይገባል ነው ያሉት።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም