ኢንተርፕሪነሮች ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። ስመጥር የሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች መነሻቸው አነስተኛ ንግድ እንደሆነም የአንዳንዶቹ ታሪክ ያስረዳል። አነስተኛ ንግድ ብዙ የሰው ኃይል በመያዝም ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ይበረታታል።
እንዲህ ያለው የዓለም ተሞከሮ በኢትዮጵያም እየሰፋ መጥቷል። መንግሥትም ለሥራ መነሻ የሚሆን ገንዘብ በብድር እንዲያገኙ፣ የመሥሪያና መሸጫ ቦታ እንዲመቻችላቸው፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ እያበረታታቸው ይገኛል። የበለጠ እንዲተጉም የሚደረገው የድጋፍ ማበረታቻ ከራሳቸው አልፈው በአገር ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ውጤታማ ኢንተርፕራይዞችን ማፍራት ችሏል።
ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ መንግሥት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በብድር ያገኘውን ገንዘብ ለሴት ኢንተርፕሪነሮች ያለዋስትና ብድር በማመቻቸት ውጤታማ የሚሆኑበትን አሠራር ፈጥሯል። ኢንተርፕሪነሮች ካሉባቸው ቁልፍ ችግሮች አንዱ ያለዋስትና የገንዘብ ብድር ማግኘት በመሆኑ ለሴት ኢንተርፕሪነሮች የንግድ ሥራ እፎይታን የሰጠ እርምጃ እንደሆነ ከተጠቃሚዎቹ መካከል የንግድ ሥራቸውን ‹‹ማርታ ዲኮር›› ብለው የሰየሙት ወይዘሮ ማርታ ከበደ ይናገራሉ። በንግድ ሥራቸው እና ስለ ወደፊት ራዕያቸው ቆይታ አድርገናል፤ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡– እራስዎን በአጭሩ ያስተዋውቁን
ወይዘሮ ማርታ፡- ተወልጄ ያደኩት አዳማ ከተማ ነው። ለቤተሰቦቼ የመጀመሪ ልጅ ነኝ። አባቴ መምህር ነው። በጥብቅ ቁጥጥር ነው ያደኩት። የተማርኩት፣ ሥራ ፈጥሬ የምንቀሳቀሰውም በተወለድኩበት ከተማ ውስጥ ነው። አሁን ለተሰማርሁበት ባህላዊና ዘመናዊ የአልባሳት አነስተኛ የንግድ ሥራ አንደኛ ደረጃ የተማርኩበት ትምህርት ቤት አስተዋጽኦ አድርጎልኛል።
በእጅ ሥራ ክፍለጊዜ ጥልፍና የተለያዩ የሹራብ ሥራዎች እንሠራ ስለነበር የሙያ ባለቤት እንድሆን መሰረት ጥሎልኛል። ከዘጠኝ ዓመቴ ጀምሮ እስካሁን በእጅ ሥራ ጥበብ ውስጥ ነው ያለሁት። ሙያዬን ለማዳበርም የዲዛይን ሙያ ለአንድ ዓመት ተምሬያለሁ። አጫጭር ስልጠናዎችንም ወስጃለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በክህሎት ያሳደጉትን ሙያ ለመጀመር ነገሮች ቀላል ነበሩ?
ወይዘሮ ማርታ፡– አልነበሩም። ለሥራ መነሻ ገንዘብም ሆነ በሐሳብ እንኳን የሚያበረታታኝ ሰው አልነበረም። ብዙ መውደቅና መነሳት የበዛበት ነው። ለተወሰነ ጊዜ የዲዛይን ሥራ በተማርኩበት ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግያለሁ። በእጄ የነበረው ገንዘብ አነስተኛ ስለነበር ቤት ውስጥ የሙሽራና የሚዜ አልባሳት ሠርቼ በማከራየት ነበር ሥራ የጀመርኩት። ሥራው እያደገ መጥቶ ወደ ሱቅ ወጣሁ። በዚህ ሁኔታ ብንቀሳቀስም በቤተሰብ ኃላፊነትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የምፈልገው ደረጃ ላይ ልደርስ አልቻልኩም።
ተስፋ ሳልቆርጥ ችግሮችን ተቋቁሜ የገንዝብ ብድርና የመሥሪያ ቦታ ለማግኘት ባለሁበት ቀበሌ ውስጥ በግሌ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጀሁ። ብድሩ የሚፈቀደው ዋስትና ማቅረብ ለሚችል ብቻ ስለነበር አልተሳካም። በግሌ ሱቅ ተከራይቼ እየሠራሁ የሴቶች ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት ሠራተኞች አለሁበት ድረስ መጥተው ሥራዬን ለማሳደግ የሚያግዘኝ የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናና ያለዋስትናም የገንዘብ ብድር ማግኘት እንደምችል መረጃ ሰጡኝ።
ዕድሉን አላሳለፍኩም ተጠቀምኩበት። ያገኘሁት የአጭር ጊዜ ስልጠና ሥራዬን ለማሻሻል በጣም ረድቶኛል። በስልጠናው አጋጣሚም ከኦሮሚያ ካፒታል ዕቃዎች ያለዋስትና 180ሺ ብር ዋጋ ያላቸው ዘጠኝ የስፌት ማሽን በብድር ማግኘት በመቻሌ በአልባሳት ምርት ከፍተኛ ደረጃ የመድረስ ምኞቴን ለማሳካት አግዞኛል።
አሁን በተለያየ ዲዛይን ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳትን አመርታለሁ። ስለጠናው ሙያተኞችን ለማፍራትም እንድችል መንገድ ከፍቶልኛል። ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በልብስ ስፌት፣ ጥልፍና ዲዛይን ሙያ 50 ተማሪዎች ተቀብዬ በደረጃ /ሌቭል/ አንድ እያሰለጠንኩ ነው። በመጀመሪያ ዙርም 34 ተማሪዎች አስመርቄያለሁ። ዘንድሮ 55 ተማሪዎች ለማስመረቅም ተማሪዎቹ የምዘና ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ያለዋስትና ምን ያህል ብድር አገኙ?
ወይዘሮ ማርታ፡– በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚመለስ 250ሺ ብር ነው ያገኘሁት። ያገኘሁትን ብድር የልብስ ስፌት ትምህርት ለምሰጥበት ማጠናከሪያ ነው ያዋልኩት። በሴቶች ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት ስልጠናና፣ ያለዋስትና የገንዘብ ብድር ብቻ ሳይሆነ በዘርፉ ላይ ልምድ ያላቸውንና መምህራንንም ማግኘት መቻሌ ከልማዳዊ የንግድ ሥራ እንድወጣ እና ለሥራ የሚያግዙኝን ነገሮች ለማግኘት የት መሄድ እንዳለብኝ አግዞኛል።
አዲስ ዘመን፡– ያለዋስትና ብድር አልተለመደም በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ ማርታ፡– ያለዋስትና ብድር አለመኖሩ የኔ ተሞክሮ ማሳያ ነው። በኢንተርፕራይዝ ተደራጅቼ ብድር ስጠይቅ ደመወዝተኛ የሆነ ሰው ወይም ንብረት ነበር የተጠየኩት። ሁለቱንም ባለማግኘቴ ዋጋ ከፍያለሁ። በሙያው ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ ብቆይም ገና አሁን ነው መንቀሳቀስ የጀመርኩት። ብድር አለመገኘቱ ዘርፉን ወደኋላ ያስቀረዋል። ያለዋስትና ብድር መመቻቸቱ መሥራት የሚፈልጉ ሴቶች ራዕያቸውን ያሳኩበታል።
ፕሮጀክቱም ሴቶችን ለማበረታታት የሚሠራ በመሆኑ በግሌ ጠቅሞኛል። ሥራዬን በመከታተል ድጋፋቸው አልተለየኝም። እኔ ከሠራሁ ለሌሎችም መንገድ ስለምከፍት ጠንክሬ አርአያ መሆን እፈልጋለሁ።
አዲስዘመን፡– ከባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት ማምርት እና ከማስተማር በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችንም እየሠሩ ነው?
ወይዘሮ ማርታ፡- አዎ፤ ሥራዬን በተለያየ መልክ በማሳደግ ተጠቃሚ መሆን ስለምፈልግ ከሙያው ጋር ተያያዥ የሆኑ ሥራዎችን እሠራለሁ። ለሠርግና ለተለያዩ ዝግጅቶች አዳራሽ የማስዋብ ሥራ እንዲሁም ሱቄ በሚገኝበት አካባቢ ቡና ሻይ አቀርባለሁ። የሥራ መስኩን ማስፋት መቻሌ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችሎኛል። የማስዋብ ሥራ ሲገኝ በጊዜያዊነት ሠራተኞች እቀጥራለሁ። በቋሚነት ደግሞ 20 ሠራተኞች አሉኝ። ወደፊት የሽመና ሥራንም የማካተት ዕቅድ አለኝ። እግረመንገዴንም የባህል ልብስ እንዲዘወተር በምርቱ ኢትዮጵያ እንድትታወቅ በሥራ በማሳየት ጥረት አደርጋለሁ።
አዲስዘመን፡– ምርትዎን የት ነው የሚያቀርቡት?
ወይዘሮ ማርታ፡– አገር ውስጥ ነው የማቀርበው። በውጭ አገር በትውውቅ ካልሆነ ገበያ የለኝም። ወደፊት ግን በስፋት ለማቅረብ ፍላጎቱ ስላለኝ እዘጋጃለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በሥራ ላይ እንደተግዳሮት የሚያነሱት አለ?
ወይዘሮ ማርታ፡– በሥራው ላይ በስፋት ከገባሁ በኋላ ያስተዋልኩት በትዕግሥት እና በፍላጎት የሚሠራ የሰው ኃይል አለማግኘት ነው። ብዙዎቹ ይሰለቻሉ። ተማሪዎቹም ቢሆኑ በሌቭል አንድና ሁለት ላይ መቆም የሚፈልጉ ናቸው። ሰፊ የሆነ የእጅ ጥበብ ሙያ ውስጥ ለመግባት ዝግጁ ሲሆኑ አላይም። ይሄ ያሳስበኛ። ሙያው ጥበብ ነው። ጥበብ ደግሞ ትዕግሥት ይፈልጋል።
ለሙያ እንደኔ ፍላጎት ያላቸውና ማደግ የሚፈልጉ ሙያተኞችን ማፍራት እፈልጋለሁ። ሙያውን ወደው በሙያ ውስጥ የሚቆዩ ሙያተኞችን ለማፍራት እኔም በእነርሱ ላይ መሥራት እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ። ከተሞክሮዬ በመነሳት እመክራቸዋለሁ። ስመክራቸው ግን እኔ ያለፍኩበትን ረጅሙን መንገድ ሳይሆን በአጭሩ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ነው የምነግራቸው።
ዛሬ ለሥራ መነሻ ገንዘብና የክህሎት ስልጠና ለማግኘት ምቹ ሁኔታ አለ። ዕድሉን እንዲጠቀሙና ከፊታቸው ብርሃን መኖሩን በመንገር አበረታታቸዋለሁ። እንቅልፍ ድህነት እንደሆነ ነው የምነጋርቸው። ሳምንቱን በሙሉ በሥራ ላይ ነኝ። ወደ መኝታዬ የሚሄደው ዘግይቼ ነው። የምነሳውም ንጋት 11 ሰዓት ነው። ሙያው እንደ ዱላ ቅብብል እንዲያድግ ፍላጎት ስላለኝ ጥረት አደርጋለሁ። ሌላው ተግዳሮት አሁን የምሠራበት ቦታ የኪራይ በመሆኑ ሥራዬን እንዳላስፋፋ እንቅፋት ሆኖብኛል።
አዲስዘመን፡– ከሥራዎ ጋር በተያያዘ ያገኙት ሽልማት ወይም ማበረታቻ ይኖራል?
ወይዘሮ ማርታ፡– አዎ ተሸላሚ ነኝ ማለት እችላሉ። ከዚህ በፊት ያገኘሁት ሽልማት ባይኖርም። ዘንድሮ ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ተሻጋሪ ከሚሆኑት መካከል አንዷ ነኝ። የእኔ ሥራ ሌሎች ሴቶችም በኢንዱስትሪው ውስጥ እንደሚገቡ አርአያነት ያለው ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በአነስተኛ ሥራ ውስጥ የሚያልፉ አንዳንዶች በትንሽ ነገር በመርካት ከፍ ሲሉ አይስተዋልም እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ ማርታ፡- በግሌ ውስጤ ረክቶ አያውቅም። ሁሌም ለራሴ የምነግረው አልሰራሁም ነው። ለራሴ ብቻ አይደለም የምሠራው። ብዙ የተቸገሩ ሰዎች አሉ። በአቅም ማነስ ሙያውን እየፈለጉ የቀሩ አሉ። በተለይ ሴቶች። እነርሱን መርዳት እፈልጋለሁ። ከመንግሥት ጋር ሆኜ መሥራት ፍላጎቴ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ካፒታልዎ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ወይዘሮ ማርታ፡– ሁለት ነጥብ ሚሊዮን ብር ደርሷል። ገንዘቡ አብዛኛው ንብረት ላይ ነው ያለው።
አዲስዘመን፡– ወይዘሮ ማርታን በአልባሳት ኢንዱስትሪው በምን ደረጃ ላይ ሆነው እናግኛቸው
ወይዘሮ ማርታ፡– ጉዞዬ ረጅም ነው። በሙያው ውስጥ ቆይቼ በዘርፉ ታዋቂ ሙያተኞችን ማፍራት እንዲሁም ዘርፉን ወደ ትልቅ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር ነው። በተጨማሪም በሰብአዊ ዕርዳታ ውስጥ መሳተፍ ነው። በተለይ ደግሞ የሴቷን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግና በአገር ኢኮኖሚ ውስጥም የጎላ ሚና እንዲኖራት ማድረግ ነው ፍላጎቴ።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ
ወይዘሮ ማርታ፡- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2011
ለምለም መንግሥቱ