![](https://press.et/wp-content/uploads/2019/07/ታተተተ-2-11-2.png)
«በእርሱ ጅራፍ ቀንተው የተማሩ ሁሉ፤
ወዲያ ማዶ ቆመው ወዲህ እያስተዋሉ፤
መምህራቸውን አይጽፉም ይላሉ፤
የማይጽፍስ እርሱ የፊደል ዘር ውላጅ ብርሃን ያልጎበኘው፤
የማይምነት ግርጃ አፍኖ ያቆየው …›› እያለ ይቀጥላል፡፡
አዎ ! እነዚህ የግጥም ስንኞች ከገጣሚው ሙሉ ግጥም ላይ ለዚህ የጽሑፍ መልዕክት ለመግቢያ ያህል ተቀንጭበው የተወሰዱ ሲሆን፤ መምህሩ ብርሃን የሆነላቸው ተማሪዎች መምህራቸውን ሲተቹ መገኘታቸውን የወቀሰበትን አግባብ ያሳያል̣። ይህ አዲስ ዘመን ጋዜጣችን በመምህር ይመሰላል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ‹‹መጪው አዲስ ዘመን ብርሃን የምናይበት ነው›› በሚል እሳቤ «አዲስ ዘመን» ተብሎ ተሰይሞ በመንግሥትና በህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል በመመስረቱ የታቀደለትን ዓላማ እያከናወነ እነሆ በአሁኑ ወቅት 78ተኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባለፉት 78 ዓመታት ህብረተሰቡን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፍትህ ፣ በባህል ፣ በኪነ ጥበብና በዲፕሎማሲ መስኮች ከአገር ቤት እስከ ውጭ አገራት ድረስ አስተማሪና አቀራራቢ የሆኑ ጉዳዮችን በመያዝ ለዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች የዕውቀት ቤተ መዘክር በመሆን፤ የአገሪቱን መልካም ገጽታ በመገንባትና መልካም ግንኙነት በመፍጠር ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ነው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንዳንዶች ቅርጹንና መልኩን በማየት ብቻ ይዘቱን ሳይገነዘቡ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ጋር በማያያዝ ከማንበብ ይልቅ በሩቁ ሲሸሹት የሚስተዋሉ ቢሆንም መጽሐፍን ውስጡን ሳይመረምሩ ሽፋኑን ዓይተው ‹‹ጠቃሚ አይደለም›› ብለው እንደሚደመድሙት የዋሆች ጋዜጣው የያዛቸውን ጠቃሚ ጽሑፎችን እንደዋዛ ሳያነቡ ማሳለፋቸው መምህራቸውን እንደሚተቹት የዋህ ተማሪዎች ስንት ዕውቀት አመለጣቸው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀደም ሲል ከነበረበት ደረጃ ወደላቀ ተሸጋግሮና ዘመናዊነትን ተላብሶ ለአንባቢው ተመራጭ መረጃዎችንና ዕውቀትን እንዲያደርስ ባለፉት ዓመታት ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ በይዘትና በቅርጽ ጉልህ የሚባል ዕድገት እያስመዘገበ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ደረጃ ላይ ደርሷል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሳምንት 7 ቀን የሚታተም ሲሆን፤ የአንባቢዎቹን ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል የይዘት ለውጥ በማድረግ በፖለቲካ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚ፣ በኪነ ጥበብ እንዲሁም አነጋጋሪ ጠንካራ ዜናዎችን በመሥራት በአገሪቱ ካሉት የህትመት መገናኛ ብዙሃን ተመራጭ የመሆን ደረጃ ላይ ደርሷል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ የተያያዘው የለውጥ ጎዳና የተሳካ እንዲሆን የአሳታሚው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጀት የቦርድ አመራርና የድርጅቱ አመራር አካላት እንዲሁም ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መገኘታቸው ስኬታማነቱን ከወዲሁ የሚያረጋግጥ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ በቀጣይ ለአንባቢዎቹ ተደራሽ እንዲሆን የስርጭት አድማሱን የማስፋት፣ የግሉን ማተሚያ ቤት የማቋቋም፣ የጋዜጦቹን የህትመት ቋንቋ ብዛት የመጨመር፣ ይዘቱን የማጠናከርና አደረጃጀቱን የማሻሻል ሥራ የማከናወን ራዕይ ሰንቆ በትጋት እየሠራ ውጤታማ እየሆነ ይገኛል።
የዛሬው የአዲስ ዘመን የዕረቡ ጋዜጣም የዚሁ የለውጥ ጅማሮ አካል በመሆኑ በድርጅቱ ጋዜጠኞችና በተሳታፊ እውቅ ፀሐፊያን ልዩ ልዩ መረጃዎችን የሚያስተላልፉ ሥራዎችን ይዞ ሲቀርብ የላቀ ኩራት ይሰማዋል። ጋዜጣችን ትኩረቱን በፖለቲካና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያደረገ ሲሆን፤ በየትኛወም ሁኔታ የህዝብ እንግልትና ብሶትን ከማጋለጥ ወደኋላ የማይል መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እየገለጽን አስተያየታችሁንና ጥቆማዎችን እንድታደርሱን አደራችን ጠበቀ ነው።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ እስከ ዛሬ ድረስ በየጊዜው የተከናወኑ ታሪኮችን በመያዝ፣ የባህል፣ የኪነ ጥበብ፣ የቅርስ፣ የታዋቂ ሰዎችን ማንነት በመፈተሽና የፖለቲካ ሁነቶችን በመሰብሰብ የመረጃ ቋት ሆኖ መቆየቱ ለአጥኚዎቸም ሆነ ታሪክን ለሚፈትሹ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ እንደቆየው ሁሉ ወደፊትም ይህንኑ የታሪክ መዘክርነቱንና አስተማሪነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011