አዲስ አበባ፡- በተጠናቀቀው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
ጳጉሜ 1 የመሻገር ቀን የመሻገር ጥሪቶች የአዲስ ብርሃን ወረቶች በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ደረጃ ትናንት ተከብሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፤ 2016 ዓ.ም ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ ውጤታማ ሥራዎች የተከናወነበት ዓመት ነው፡፡
አዲስ አበባ ለነገ ተስፋ የሚሰጡ ፕሮጀክቶችን በመከወን በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ተምሳሌት በመሆን ዕቅዷን ያሳካች ከተማ ናት ያሉት አቶ ጃንጥራር፣ በአፍሪካ የመጀመሪያውን የከተሞች ፎረም ማዘጋጀቷ ልዩ ያደርጋታል ብለዋል፡፡
በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪና በሀገር ደረጃ በሚከወኑ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የተገኙ ስኬቶች የመሻገር ምልክት የታየባቸው መሆኑን ገልጸው እራሳችን እየተለወጥን የሀገራችንን ልማት ማፋጠን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብዝሃነት የተዋበች በአብሮነት የደመቀች በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ቅርሶች የተዋበች መሆኑዋን ጠቅሰው በራሷ ዘመን የምትቆጥር ነጻነቷን የጠበቀች በልዩ ልዩ መልኮች የተወከለች ቀለመ ብዙ እናት መሆኑዋን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውበቷን ሳትበርዝ እያደሰችና እያስዋበች ከዘመን ዘመን በውድ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ መኖሯን ገልጸው የአባቶቻችንን አደራ ጠብቀን የራሳችንን ዐሻራ ጨምረን ለመጪው ትውልድ ማሻገር አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያን ከዓለም ሀገራት ልዩ ከሚያደርጓት እሴቶች መካከል አንዱ የ 13 ወር ጸጋ ባለቤት መሆኑዋ ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር ጳጉሜን ከከባዱ የክረምት ወራት ወደ ብርሃናማው የመስከረም ወር መሸጋገሪያ ድልድል ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በ13 ወራት ጸጋ የተሸለመች ውብ ሙሽራና የራሷ ዘመን መስፈሪያ ያላት ባለጸጋ እናት ናት ብለዋል።
እንደሀገር በግብርና፣ ደን ልማት፣ ኢንዱስትሪ እና ቱሪዝም ዘርፍን ጨምሮ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገር እንደተቻለ ጠቅሰው እንደከተማ በከተማ ግብርና፣ በቱሪዝም፣ የደን ልማት ሥራን ባህል በማድረግ ሽግግር መፈጠሩን ተናግረዋል።
በአሮጌው ዓመት ከተሠሩ ሥራዎችና የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ በማጎልበት አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ መቀበል እንዲያስፈልግ በመግለጽ፣ ከአስተሳሰብ እንከኖች በመሻገር ባለራዕይ መሆንና በአዲሱ ዓመት አዲስ ሰው መሆን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከአሮጌው ዓመትና ማንነት ወደ አዲሱ ዓመትና ማንነት መሸጋገር አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊዋ፣ የንግግር ብቻ ሳይሆን የተግባር ሰዎች በመሆን ዘመናትን በደስታና በስኬት መሻገር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
በዕለቱ ባዛርና ኤግዚቢሽንም በመስቀል አደባባይ የተከፈተ ሲሆን በመርሃግብሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት፣ አምራቾችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ተገኝተዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 /2016 ዓ.ም