ሪፎርም በሀገራችን በተለያዩ ወቅቶች ብሔራዊ አጀንዳ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ ነው። እንደ ሀገር አዳዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ የለውጥ አስተሳሰቦች በመጡ ቁጥር አስተሳሰቦቹን በሕዝብ ውስጥ ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ በማስረጽ ለለውጡ ስኬት አቅም እንዲሆኑ ለማስቻል ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱና ዋናው ነው።
በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ሪፎርሞች፣ በሕዝብ ውስጥ ያሉ በአገልግሎቶች ያለመርካት ጥያቄዎችን በፍጥነት ለዘለቄታው ለመፍታት የሚደረጉ ስትራቴጂክ ጥረቶች ናቸው። ዋነኛ ግባቸውም ጥራት ያለው ፈጣን አገልግሎት በማቅረብ በአገልግሎት የረካ ተገልጋይ መፍጠር ነው።
ከዚህም ባለፈ መሠረታዊ የሆነውን የለውጥ አስተሳሰብ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ በመተግበር አስተሳሰቡ አካል ለብሶ እንዲያገኝ፣ በዚህም መላው ሕዝብ /የለውጡ ባለቤት/ በለውጡ ላይ አመኔታ ኖሮት ለውጡን የራሱ አድርጎ እንዲወስድ እና የሚፈለግበትን ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያስችል የለውጥ ትግበራ አንድ ምዕራፍ ጭምር ነው።
በኢትዮጵያ መንግሥታዊ አገልግሎት መሰጠት ከጀመረ የረጅም ዘመን ታሪክ ያለው ነው፣ ይህም ሆኖ ግን አገልግሎቱ እስካሁን ድረስ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ይገኛል። በየወቅቱ ችግሮቹን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችም የሚፈለገውን ያህል ውጤት ባለማምጣታቸው ከአገልግሎት አሠጣጥ ጋር የተያያዙ የሪፎርም ጉዳዮች ዛሬም ሀገራዊ አጀንዳነታቸው እንደቀጠለ ነው።
በርግጥ የሪፎርም ጉዳይ በሆነ ወቅት ተጀምሮ የሚያበቃ አይደለም፣ ቀጣይነት ባለው መንገድ የሚከወን ሁሌም አገልግሎቶችን በፍጥነት እና በጥራት ለአገልግሎት ፈላጊው ማድረስ የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶችን መፍጠርንና መተግበርን ያካተተ፣ እንደየዘመኑ ተለዋዋጭነት ያለው እና ዘመኑ ከሚጠይቀው አገልግሎት ጋር የሚታይ ነው።
አሁናዊው ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ደረጃ አንፃር አገልግሎትን ለተገልጋይ በተሻለ መንገድ የማድረስ ሁኔታ ስለመኖሩ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። በተለይም ቴክኖሎጂ በፈጠረው ቅርርቦሽ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ በሆነ መንገድ በዝቅተኛ ወጪና በአጭር ጊዜ ማቅረብ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።
ሀገራችን የዚሁ ዓለም አቀፋዊ እውነታ አካል ከመሆኗ አኳያ፣ ተገልጋዮች ጥራት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት በፍጥነት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ማከናወን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተግባራዊ እየሆኑ ካሉ ሪፎርሞች አንዱ በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ የሚደረገው ነው።
በለውጡ ማግስት የአገልግሎት አሰጣጥን በሁለንተናዊ መልኩ ለማዘመን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ከፍ ባለ ሀገራዊ መነቃቃት ተጀምረዋል፤ እንደ ሀገር ካጋጠሙን ፈተናዎች አንጻር በተጀመሩበት ልክ ማስቀጠል ባይቻልም ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።
ሀገራዊ አገልግሎት አሰጣጡ ውስብስብ በሆኑ ችግሮች ውስጥ ረጅም ዓመታትን ማስቆጠሩ በራሱ ችግሮቹን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ፈታኝ አድርጓቸዋል። ከሁሉም በላይ በዘርፉ ሲደረጉ የቆዩ ሪፎርሞች መሠረታዊ የሆነውን የአስተሳሰብ ተሐድሶ ማምጣት ባለመቻላቸው፣ ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት የሚያስችል አቅም መፍጠር አልተቻለም።
የሪፎርም ሥራዎች ስኬታማ ለመሆን ከሁሉም በላይ፣ የሪፎርም አስተሳሰቦች በአገልግሎት ሰጪው የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ሰርጸው የአገልጋይነት ባሕሪ እንዲላበስ ሊያደርጉት ይገባል። ይህንን ባሕሪ መፍጠር ባልተቻለበት ሁኔታ በእውቀት፣ በቴክኖሎጂም ሆነ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ የሚያመጡት ለውጦች በራሳቸው ምሉዕ አይደሉም።
የአገልጋይነት መንፈስ መፍጠር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኝ እውቀት ብቻ እውን የሚሆን አይደለም። ይህን መንፈስ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ከአስተዳደግ ሥነ ምግባር ጋር አብሮ የሚታይ እና ሊሠራ እንዲሁም በማንነት ግንባታ ውስጥ አንድ ትልቅ አጀንዳ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባ ነው።
የአገልጋይነት መንፈስ የተገልጋይነት ሌላው ገጽታ መሆኑን እያወቀ ያደገ ትውልድ መፍጠር፣ በዘርፉ እያጋጠመን ያለውን ዓመታት ያስቆጠረ የገነገነ ሀገራዊ ፈተና መሻገር የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ነው። ይህ በአገልጋይነት ባሕሪ የተገነባ ማንነት በሙያዊ እውቀት፣ በቴክኖሎጂ እና በተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶች ሲደገፍ የምንፈልገውን አገልጋይ ትውልድ መፍጠር እንችለለን። የአገልግሎት አሰጣጣችንም አርኪ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም