ዜና ሀተታ
የከተሞች እድገትና መስፋፋት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑ እሙን ነው። “ዘላቂ የከተሞች ልማት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063” በሚል መሪ ቃል በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ በሚገኘው የመጀመሪያው የአፍሪካ ከተሞች ፎረም የተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ተሞክሮአቸውን አቅርበዋል።
በዚህም ከተሞች ውጤታማ በሆነ መንገድ ከተመሩ ትልቅ የልማት አቅም፣ የኢንዱስትሪና የሥራ ዕድል ፈጠራ ማዕከላት እንደሚሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ ከተሞች በቂ ያልሆነ መሠረተ ልማት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ ሥራ አጥነትና የአካባቢ ብክለትን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን እያስተናገዱ መሆኑ ተነስቷል።
የኢትዮጵያ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ እንደሚናገሩት፤ በአፍሪካ ፈጣን የከተሞች እድገት እየተስተዋለ ይገኛል። በዚህም በአመት በአፍሪካ 3 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 4 በመቶ የከተሞች እድገት ይታያል።
እድገቱ የከተማና የገጠር ምጥጥንን የሚቀይር ማሳያ በመሆኑ አፍሪካ እንደአህጉር በርካታ የከተማነት አጀንዳዎች አሏት ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከተሞች ሲስፋፉ በቂ የመሠረተ ልማት መስፋፋት እጅጉን አስፈላጊ ነው። ከተሞቻችንን ለማሻገር ለዜጎች ምቹ መኖሪያ እንዲሆኑ ለማድረግ በጋራ መሥራት አለብን ይላሉ።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ የክትመት ምጣኔ እድገት የአንድን ሀገር የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት፣ የማህበራዊ፣ የቴክኖሎጂና ሌሎች ጉዳዮች እድገትን የሚያመላክት ነው። ይህም በከተማ የሚኖረው ሕዝብ እያደገ የሚሄድበትና ለሀገር ውስጥ አመታዊ ምርት(ጂዲፒ) እንዲሁም አጠቃላይ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግበትን እድል ይፈጥራል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት የከተሞች መስፋፋት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሙሉ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት በሚያስችል መልኩ ከተሞችን ለመምራት የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየወሰደ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከተሞችን ምቹ የመኖሪያ፣ የመንቀሳቀሻ፣ የምርታማነት አካባቢ በማድረግ የምጣኔ ሀብት ማዕከል ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካ የሰፈራ ምክትል ሚኒስቴር ታንዲ ማሀምባሀላላ እንደሚሉት፤ አፍሪካ ፈጣን የከተሞች እድገት የምታስተናግድ አህጉር ናት። በዚህም ወደከተሞች የሚደረገው የዜጎች ፍልሰት ከተሞች እራሳቸውን በመሠረተ ልማት ግንባታ ሊያበቁ እንደሚገባ አመላካች ነው።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ የከተማነት ምጣኔ ማደጉ የከተሞችን ሽግግር ያፋጥናል። እንዲሁም የባህልና የእውቀት ልውውጡን በማሳለጥ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ሥራ አጥነትን፣ ድህነትንና የአካባቢ መራቆትን የሚያስከትል በመሆኑ ለዜጎች መኖሪያ የሚሆኑ ምቹ ከተማዎችን ለመገንባት የተቀናጀ ሥራ ያስፈልጋል። ግብርናን በማዘመንና ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚን በመገንባት በከተሞች አካባቢ ያለውን የሥራ እድል ፈጠራ ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነና ደቡብ አፍሪካም በዚህ ረገድ የተዋጣለት ተግባር እየሠራች መሆኑን ሚኒስትሯ ይገልፃሉ።
የግብፅ የቤቶች አገልግሎት ሚኒስቴር አምባሳደር ሀሰን ኢልላኢቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደዚህ አይነት የተሳካ መድረክ በማዘጋጀቱ አመስግነው፤ የግብፅ መንግሥት በከተሞች ልማት የሚደረገውን የትኛውንም አይነት ፕሮጀክት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ነው የገለፁት።
ግብጽ በከተሞች ልማት እያከናወነች ባለው ተግባር በርካታ ለውጦችን አስመዝግባለች። የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን በመተግበር ለነዋሪዎች ተመጣጣኝ የቤት አቅርቦት፣ በዘላቂ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በመሥራትና አካታች የዲጂታላይዜሽን አማራጮችን በመተግበር ከተሞች ፈጣን እድገት እንዲያስመዘግቡ ማድረግ መቻሉን አምባሳደር ሀሰን ይጠቁማሉ።
በዚህም ግብፅ ያስመዘገበችውን ለውጦች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በማካፈልና በመቀበል የአህጉሪቱን የጋራ እድገት ለማፋጠን ዝግጁ ናት የሚሉት አምባሳደር ሀሰን፤ እንዲሁም የግብፅ መንግሥት በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ እሳቤዎችን ለማሳካት የሚጠበቅበትን ለማድረግ ከመቼውም በበለጠ ዝግጁ መሆኑን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኬንያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ግሬስ ኦካራ እንደሚናገሩት፤ ከተሜነት በአፍሪካ ሁሉንም የኢኮኖሚ ገፅታዎች እየቀረጸ ነው። ይህ ፎረም የአፍሪካ ከተሞችን አሁናዊ ገጽታ ከማስተጋባት ባለፈ በአጀንዳ 2063 የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት ያለንን ቁርጠኝነት የምናረጋግጥበት እድል የሚሰጥ ነው።
አምባሳደሯ አክለውም በአሁኑ ወቅት ከተሞች 55 በመቶ ለሚሆነው የዓለም ሕዝብ መኖሪያ ሲሆኑ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2050 ይህ ምጣኔ 68 በመቶ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ነው የሚሉት።
እ.አ.አ በ2019 የኬንያ የከተማ ሕዝብ ብዛት 31 ነጥብ 2 በመቶ የነበረ ሲሆን በ2030 ወደ 50 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚያነሱት አምባሳደር ግሬስ፤ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ለከተሞች መስፋፋት በዋናነት ይጠቀሳል ይላሉ።
ይህም በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች እና እንደገበያ ማዕከላት ባሉ መሠረተ ልማቶች እና አገልግሎቶች ላይ ጫና መፍጠር የሚችል ሲሆን ይህም በከተማ በሚኖሩ ዜጎች ላይ ተግዳሮቶችን እንደሚያስከትል አምባሳደሯ ይገልፃሉ።
እንደ አምባሳደር ግሬስ ገለፃ፤ እኩልነት ማጣት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የከተማ ኢ-መደበኛነት እና የድህነት ደረጃ መጨመር። እነዚህ ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆኖ የከተሞች መስፋፋት ውስጣዊ እሴቱ ለመዋቅራዊ ለውጥ፣ ለዕድገት መፋጠን እና ለጋራ ብልጽግና የሚውል አዎንታዊ ኃይል ነው።
የከተሞች መስፋፋት ፈተናዎችን ለመፍታት የኬንያ መንግሥት የተለያዩ ኢንሼቲቮችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ትልቅ እመርታ አምጥቷል የሚሉት አምባሳደሯ፤ በተጨማሪም አቅም ለሌላቸው ኬንያውያን ጥሩ መኖሪያ ቤቶች እንዲኖራቸው ለማስቻል ለተመጣጣኝ የቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ቅድሚያ ተሠጥቷል። በፕሮግራሙ በዓመት 250 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ለማቅረብ እየተሠራ ነው ይላሉ።
የሶማሊያ ሪፐብሊክ የኮንስትራክሽን እና ቤቶች ሚኒስትር አብዱሰላም አብዲ እንደሚገልጹት፤ ይህ ፎረም በአፍሪካ አህጉር ውስጥ አካታችና አሳታፊ የሆነ የዜጎች አሰፋፈር እና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚደግፍ ነው። ሁሉን አቀፍና ቀጣይነት ያለው የከተማ ልማት ለማምጣት ከከተማ ልማት ጋር የተያያዙ ሃሳቦችን እና ምርጥ ተሞክሮዎችን መለዋወጥ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው።
የከተሞች መስፋፋት የባህል፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና የመሠረተ ልማት መዘመንን በማጠናከር የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎቶች የሚያሟሉ ነው የሚሉት ሚኒስትሩ፤ የሶማሊያ ሪፐብሊክ የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርት፣ የጤና እና የመሠረተ ልማት አገልግሎት ማስፋፋትን እንደ ቁልፍ የከተማ ልማት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየሠራበት መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ፖሊሲዎችን እና ተዛማጅ ሕጎችን መከለስ፣ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር በአነስተኛ የመኖሪያ መንደሮች ላይ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ግብዓት ማቅረብ፣ ከተሞችን፣ ማዘጋጃ ቤቶችን በተለያዩ መንገዶች ለማሳደግ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በተመራው በዚህ መድረክ በተመሳሳይ መልኩ የሶማሊያ፣ የማዳጋስካር፣ ዩጋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ዚምባዋብዌ፣ ኬንያና ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ልምዶቻቸውን ያካፈሉ ሲሆን ይህንኑ ፎረም እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለዜጎች ምቹና የበለፀገች አፍሪካን ለመፍጠር በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 /2016 ዓ.ም