የአንድን ሀገር እድገት ወደኋላ ከሚጎትቱ ጉዳዮች መካከል የቢሮክራሲ ጥራት መጓደል ዋንኛው ምንጭ መሆኑን አምናለሁ። በዋናነት ይህ ስር የሰደደ ችግር የሚፈጠረው ደግሞ በመንግሥት ተቋማትም ይሁን በግል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች አገልጋይነት ባሕሪ አለመላበስ ነው።
ኢትዮጵያ የነደፈቻቸውን የልማት ግቦች ለማሳካት በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የሕግ፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ የተሟላ የአሠራር ሥርዓት እንዲዘረጋ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤ መሠረተ ልማት ማሟላት፣ ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።
እነዚህ መሠረታውያን መሟላታቸው ብቻ የሚጠበቀውን ለውጥ አያመጣም። ይልቁንም የአገልጋይነት መንፈሰ የተላበሰ፣ በሥነ ምግባሩ የተመሰገነና በፍፁም ቅንነት ማኅበረሰቡን የሚያገለግል ሠራተኛ ሊፈጠር ይገባል። ለመሆኑ ከዚህ አንፃር ሲመዘን የሀገራችን የአገልግሎት ዘርፍ ምን መልክ ይኖረው ይሆን? ኢትዮጵያዊ ባሕላችንስ ስለ ‹‹ማገልገል›› ምን ይለናል?
ከላይ ባነሳሁት ርዕሰ ጉዳይ ምክንያት ለዛሬ የአገልጋይነት ባሕላችን ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ (በተለይ በግልና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶቻችን) በጥቂቱ ለመመልከትና የግል ምልከታዬን ለማጋራት ወድጃለሁ። ለመሆኑ ዘመናትን አብሮን የዘለቀው እንግዳ ተቀባይነታችን እና ጎንበስ ቀና ብሎ የማገልገል ልምዳችን ከወዴት ነው? ዛሬስ አብሮን ይሆን? ይህንን እሴታችንን በአገልግሎት ሰጪ ተቋማቶቻችን ውስጥ ለምን ተግባራዊ ማድረግ ተሳነን? እነዚህን ጥያቄዎች በዛሬው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፊ ቦታን የሚይዙ ይሆናሉ።
በሀገራችን የቢሮክራሲ ተቋማት፤ ማኅበራት፣ የግል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ (በሁሉም ባይሆን በአንዳንዶቹ) ለተገልጋይ የሚሰጠው ስፍራ እጅጉን አናሳ እንደሆነ የሁልግዜም የብዙኃን መወያያ ጉዳይ ነው። አንድ ግለሰብ ጉዳዩን ይዞ በአንድ ቢሮ አሊያም መሥሪያ ቤት ውስጥ ቢገኝ ያሰበውን ለመፈፀም በተደጋጋሚ (ለቀናት፣ ለሳምንታት ሲያልፍም ለዓመታት) ደጅ መጥናት እንደሚኖርበት፤ አሊያም ሙስና እስከመስጠት እንደሚደርስ ይነገራል።
ይህን መሰል ብልሹ አሠራር የፈጠረው በተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ተቀጣሪዎች የአገልጋይነት ባሕል ደካማ መሆን፣ የሥነ ምግባር ጉድለትና፣ የአቅም ማነስ እንደምክንያትነት ይጠቀሳሉ። በጥቅሉ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት (የግልም ሆነ የመንግሥት) ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የአገልጋይነት ስሜት ደካማ መሆን ቀዳሚው መንስኤ ነው።
ይህ እሳቤ በመንግሥት ሠራተኛውም ይሁን በእያንዳንዱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ መታየት ማኅበረሰቡ ጥራት፣ ቅልጥፍና እንዲሁም አርኪ ግልጋሎት እንዳያገኝ ከማድረጉም ባሻገር እንደ ሀገር የተያዘውን ልማት እና እድገት የሚገታ የገነገነ ችግር ነው።
እያንዳንዱ ግለሰብ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የግል ጉዳይ ለማስፈፀም ወደ ልዩ ልዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት መሄዱ አይቀርም። እርሱም እንደዚያው በሚሠራበት ቦታ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ደንበኞች ይኖራሉ። ይህ ማለት ሁሉም ሰው የአገልጋይነት (በቅንነት የመታዘዝ፣ ደንበኞችን የማክበር፣ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ በቅልጥፍና ጉዳይን የመፈፀም የመሳሰሉትን ባሕሪያት) ባሕልን ቢያዳብር ጥቅል ውጤቱ ፍፁም አስደሳችና ይሆናል። የምንፈልጋትን የተረጋጋ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ለመገንባት ያስችለናል።
ለሁሉም ግልፅ እንደሆነው በምንኖርበት 21ኛው ከፍለ ዘመን ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ውስብስብ ችግር በማቅለል፣ የአሠራር ሥርዓትን በማቀላጠፍ ግዜና ገንዘባችንን ይቆጥብልናል። የአሠራር ሥርዓታችንን በልዩ ልዩ መልኩ ማሻሻላችንም እንዲሁ የሚፈለገውን ውጤት እንድናስመዘግብ ሊረዳን ይችላል።
ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሠራር ብቻ በቂ አይደለም። የእኛ ማኅበረሰብን በምንሠራበት የሥራ መስክ ላይ (በተመደብንበት የአገልግሎት ቦታ ሁሉ በቅንነት፣ በሥነ ምግባር ለማገልገል ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል። የእነዚህ ጥቅል ድምር የተሟላና ሁለንተናዊ እድገትን ያረጋግጣል።
አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ዜጎች የአገልጋይነት ባሕሪን እንዲላበሱ፣ በሀገር ወዳድነትና በእኔነት ስሜት ለጋራ እድገትና ብልፅግና እንዲሠሩ፣ አዲስ ባሕል፣ አዲስ እሳቤ እንዲፈጠር ተግባራዊ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።
ለዚህ አስረጂ የሚሆነው ዜጎች በተለይ አገር ተረካቢ ወጣቶች (ስለሚከፈላቸውና ገንዘብን ስለሚያገኙበት ሀብት ብለው ሳይሆን) ለሀገራቸውና ለማኅበረሰባቸው እውቀትና ጉልበታቸውን ያለስስት በበጎ ፍቃድ በነፃ እንዲሰጡ ሰፊ ንቅናቄ ተደርጓል።
በዚህ ጥረትም እጅግ ውጤታማ የሆኑ በርካታ ሥራዎችን ተሠርተዋል። የዜጎች የአገልጋይነት ስሜት እንዲዳብር ቀስ በቀስም ይህ ቀድሞም ከነበረው ባሕላችን ጋር (እንግዳን ተቀብሎ፣ አልጋ ለቅቆና ተንከባክቦ በክብር የመሸኘት ባሕልን ጭምር) እንዲቀናጅና እንዲሰናሰን ተከታታይ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በበጎ ፍቃድ ማኅበረሰብን ከማገልገል በተጨማሪ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በውስጣቸው የያዟቸው ሠራተኞች እውቀትን፣ ቅልጥፍናን ከምንም በላይ ደግሞ የሙያ ሥነምግባርን በተሟላ መልኩ እንዲተገብሩ ተከታታይ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። መንግሥት ይህንን ለማስተግበር እየሠራ መሆኑን ይፋ አድርጓል። ይህ እርምጃ በሂደት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚታየውን ብልሹ የአገልጋይነት ስሜትን እንደሚያስተካክለው ይጠበቃል።
ችግሩ በመንግሥት በሚወሰድ ጥብቅ ቁጥጥርና እርምጃ ብቻ የአገልጋይነት ስሜት ሊገነባ አይችልም። ማኅበረሰብን ተመድበው በሚሠሩበት ማንኛውም ቦታ ላይ ለማገልገል ፍላጎት የምናሳድረው ለሀገራችን በሚኖረን ጥልቅ ፍቅርና ቀናዒነት ነው። የሀገር ፍቅራችንን ማሳየት የምንችለው ደግሞ ከውስጣችን ሊፈጠር በሚገባው የአገልጋይነት ስሜት ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሀገር ፍቅሩን በዚህ ልክ ሊገልፅና በተግባር ሊያሳይ ይገባዋል።
የአገልጋይነት ስሜት በውስጣችን ለመገንባት የመጀመሪያው እርምጃ ተነሳሽነትን በውስጣችን መፍጠር ነው። ቀጥሎ ደግሞ በየግዜው እራሳችንን በእውቀትና ማዳበር እና ለአዳዲስ አሠራሮች ተጋላጭ ማድረግ ነው። ሌላውና መሠረታዊው ጉዳይ በጉልበታችንና በእውቀታችን ከምናገኘው ጥቅም በተለየ የማግበስበስ ባሕሪያችንን መግታት ያስፈልጋል።
ለምንሰጠው እያንዳንዱ ግልጋሎት ተገቢ ያልሆነ ዳረጎትን መጠበቅ የአገልጋይ ሠራተኛ ባሕሪ አይደለም። ለማኅበረሰብ ልማትና እድገት ሌት ተቀን መሥራት ነገ ለምንፈጥራቸው ሀገር ተረካቢ ልጆች ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም።
በእርግጥ በአሁኑ ግዜ በሀገራችን ወጥነት ያለው፤ ፍፁም ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተከተለ አገልጋይ ሠራተኛ በተሟላ ሁኔታ ማግኘት ይከብዳል። ይህንን ባሕል ግን በቁርጠኝነት ከሠራን እንቀይረዋለን። ለዚህ ማሳያው ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት የታዩት እመርታዎች ናቸው።
መንግሥት ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት በሚል እሳቤ በሲቪል ሰርቪሱ ላይ ተከታታይ ማሻሻያዎችን እያደረገ ይገኛል። የግሉ ዘርፍም መሰል እርምጃዎችን መውሰድ ይገባዋል። በመንግሥት በኩል እያንዳንዱ ሠራተኛ ማኅበረሰብን በሙያዊ ብቃትና ሥነ ምግባር የማገልገል ቁመና ላይ የሚገኝ ስለመሆኑ የሚያረጋግጡ አሠራሮችን እየዘረጋ ነው።
ይህ ተግባር በሠራተኛው ውስጥ አዲስ እሳቤ የሚፈጥር እንደሆነ ይታመናል። ነገር ግን አገልጋይነት በሕግ አስገዳጅነት ብቻ እንደማይመጣ ተረድቶ ሁሉም ዜጋ በውስጥ ፍላጎት ሊያዳብረው የሚገባ ባሕል መሆን አለበት። ሰላም!!
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም