በመዲናዋ በ137 ቦታዎች የበዓል ዋዜማ ድረስ የሚቆይ ባዛር ተከፈተ

አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ ለዘመን መለወጫ በዓል ፍጆታ የሚሆኑ ምርቶችን በቀላሉ ለሸማች ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የበዓል ዋዜማ ድረስ የሚቆይ ባዛር በ137 ቦታዎች ላይ መከፈቱን የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ገለጸ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ ከባዛሮቹ በተጨማሪ በአንድ ሺህ 500 የኅብረት ሥራ ማህበራት ሱቆች የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እንዲሁም የፍጆታ እቃዎች በስፋት መኖራቸውንም ገልጸዋል።

“በዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ከሶስት ወር በፊት የዝግጅት ሥራ ሲካሄድ ቆይቷል። በዚህም በከተማዋ ባሉት 11 ዩኒየኖች አማካኝነት 33 የገበያ ትስስር ተፈጥሯል” ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ከክልል አምራቾች፣ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜም በመዲናዋ ለበዓል ፍጆታ የሚሆኑ ምርቶችን ለሸማቹ ተደራሽ ለማድረግ በ137 ቦታዎች ባዛር ተከፍቷል። ይህም የምርት አቅርቦቱን በማሻሻል ፍትሐዊ ስርጭት እንዲኖር ያደርጋል ያሉት ኮሚሽነር ልዕልቲ፤ ኅብረተሰቡ 239 በሚሆኑ ሉካንዳ ቤቶች የበሬ ስጋ ማግኘት እንደሚችልም ገልጸዋል።

በባዛሮቹ የአትክልት፣ የሰብል፣ የእንስሳት ተዋፅኦ እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶች በብዛት በመቅረብ ላይ እንደሚገኙ ኢፕድ ባዛሮቹን ቦታው ድረስ ሄዶ መመልከት ችሏል።

በገበያዎቹ ቀይ ሽንኩርት ከ85-88 ብር ፣ ቲማቲም 55 ብር ፣ ፈሳሽ ዘይት ባለ 5 ሊትር ከ1060-1080 ብር፣ እንቁላል 10 ብር ፣ ማር 500 ብር ፣ የጠጅ ማር 450 ብር፣ ቂቤ በኪሎ ከ650-700 ብር እንዲሁም ዱቄት በኪሎ 88 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የኅብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ በላይ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ የተለያዩ ምርቶችን በብዛት የማቅረብ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የዋጋ ጭማሪ እና የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በቂ ምርት ማቅረብ ላይ በትኩረት እየሠሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ዮሐንስ፤ ዩኒየኑ ለማህበራቱ 100 ኪሎ ጤፍ ከዘጠኝ ሺህ 450 እስከ 11 ሺህ 200 ድረስ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

የስንዴ ዱቄት በኪሎ ከ83 ብር እስከ 85 ብር እያከፋፈል ሲሆን የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና ሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎች በስፋት ተረክቦ ለማህበራት ሱቆች ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

 አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You