በመዲናዋ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በስኬት ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ የምዕራፍ ሁለት የኮሪደር ልማት ሥራውም ተጀምሯል። የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ካስገኘላት ጥቅሞች መካከልም ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ የብስክሌት መንገዶች፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ፏፏቴዎች (ፋውንቴኖች) ተጠቃሽ ናቸው። በተለይም የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች (ፓርኪንጎች) በስፋት ተገንብተዋል፣ አሁንም እየተገነቡ ነው።
በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የተገነቡ የመኪና ማቆሚያዎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። ቀደም ብለው ግንባታቸው የተከናወኑ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ወይም የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫዎች መካከል የመስቀል አደባባይ ከምድር በታች የተገነቡት፣ እንዲሁም የታላቁ ቤተመንግሥት የፓርኪንግ ግንባታ እና የአብርሆት ቤተመጻሕፍት የመኪና ማቆሚያ የሚጠቀስ ነው። እነዚህን ጨምሮ በሂደት የከተማዋን የፓርኪንግ አገልግሎት እያሰፉ እና መንገድ ላይ ይቆሙ የነበሩ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር እየቀነሱ በዚያው ልክ ይፈጠሩ የነበሩ የትራፊክ መጨናቆችንና የደህንነት ችግሮችን ማቃለል ተችሏል።
በመዲናዋ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች በበቂ ሁኔታ ባለመገንባታቸው ባለጉዳዮች መኪናቸውን መንገድ ዳር አቁመው ወደ ጉዳያቸው ለመሄድ ሲገደዱ ቆይተዋል። ይህም ለንብረት ደህንነት ችግር ሲያጋልጥ ይስተዋላል። ከዚህም ውጭ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች በበቂ ባለመኖራቸው በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ መንገዶች የሚቆሙ ተሽከርካሪዎች መንገዶችን ሲያጣብቡ እና እግረኞችን ጭምር መንቀሳቀሻ ሲያሳጡ ቆይተዋል። ይሁንና የኮሪደር ልማቱ ይዟቸው ከመጡ በረከቶች አንዱ በመሆኑ በአሁን ወቅት የኮሪደር ልማቱ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ይህን ችግር መቅረፍ ተችሏል። ነገር ግን የኮሪደር ልማት ሥራው ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ችግሩ ባልተጀመረባቸው በአብዛኛው የመዲናዋ አካባቢዎች ችግሩ በስፋት ይታያል።
ይህንን ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ የትራፊክ ጭንቅንቆችን የሚያስቀሩ በርካታ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ተርሚናሎች ተገንብተው ለአገልግሎት እየበቁ ነው፤ በግንባታ ላይ የሚገኙ ከምድር እስከ ፎቅ ያሉ የመኪና ማቆሚያ ሥራዎች አሉ። ከመንገድ ገባ ያሉ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ትኩረት አግኝተው በየአካባቢው እየተከናወነ ሲሆን የትራፊክ መጨናነቆችን የሚያስቀሩ የተለያዩ ድልድዮች እና አቋራጭ መንገዶች ግንባታም እየተስተዋለ ይገኛል። በአራት ኪሎ አራዳ ክፍለ ከተማ አካባቢ፣ በፒያሳ ዓድዋ ሙዚየም የተገነባው የአውቶቡስ ማቆሚያ ተርሚናል፣ በሜክሲኮ ዋቢሸበሌ ሆቴል አጠገብ፣ እንዲሁም በቦሌ እና መገናኛ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙና የፓርኪንግ አገልግሎት መሰጠት የጀመሩ ማቆሚያዎች ወይም ተርሚናሎች ይገኙበታል።
ከእነዚህም መካከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ፊት ለፊት በሰባ ደረጃ በኩል የሚገኘው ፍቅር የተሽከርካሪ ማቆሚያ አንዱ ነው። ፓርኪንጉ ወይም የተሽከርካሪ ማቆያው በራማ ኮንስትራክሽን የተገነባ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ የሚሰጠው የፓርኪንግ አገልግሎት እስከ 100 ለሚደርሱ መኪኖች ነው። በመሆኑም በአንድ ጊዜ ለ100 መኪኖች አገልግሎት በመስጠት በአካባቢው ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ መቅረፍ ተችሏል።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሚኪያስ ፋንታዬ የፓርኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። እንደ አቶ ሚኪያስ አሁን ያለው የፓርኪንግ አገልግሎት በፊት ከነበረው በውበትም በፅዳትም በተደራሽነት ጭምር የተሻለ ነው። ከመንገድ ገባ ብለው የተሰሩት የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች መንገድ ዳር ላይ ይቆሙ የነበሩ መኪኖችን ስለሚያነሳ መንገዱ ነፃ ሆኖ ለትራንስፖርት አገልግሎቱ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የፓርኪንግ አገልግሎቱ ለተሽከርካሪ ባለንብረቶችም የተሻለ ደህንነት ይኖረዋል። በግንባታ ላይ የሚገኙ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሥራ ሲጀምሩ ወደ የክፍያ አሰራር ሲገቡ ተጠቃሚውም ከደህንነቱ አኳያ በአገልግሎቱ የመጠቀም ፍላጎት እንዲያድርበት ከህብረተሰቡ አቅም ጋር የተገናዘበ መሆን አለበትም። ቀደም ሲል ከአራት ኪሎ ጫፍ እስከ ፒያሳ ለመድረስ ከፍተኛ መጨናነቅ እንደነበረና ጊዜ የሚወስድ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን በማንኛውም ሰዓት ቢሆን ይህ ችግር ተቀርፎ መንገዱ ነፃ ሆኖ ለማሽከርከርም ምቹ ሆኖ ይገኛል። በዚያው ልክ ደግሞ አሽከርካሪዎች ከአደጋ ነፃ ለመሆን በኃላፊነት ማሽከርከር ይገባቸዋል።
አንዳንድ አካባቢዎች መስተካከል ይገባዋል ሲሉ እንደገለፁትም የተሽከርካሪ መመለሻ መንገዶች በሲሚንቶ፣ በብረት ተሰርቶ ከተዘጋጀ በኋላ ዝግ የሚደረግበት ሁኔታ መታየት አለበት። ለምሳሌ ከቄራ ቀለበት መሻገሪያው ወደ ወሎ ሰፈር ሲኬድ ወንጌላዊት ጋር ዞሮ መመለሻ መንገድ ተዘግቶ ይገኛል። አንድ ጊዜ መሸጋገሪያው ላይ ከወጣ ኢንሳን አልፎ ወደ ወሎ ሰፈር ዋናው አደባባይ ለመድረስ ከተቃረበ በኋላ ነው ተመልሶ መምጣት የሚቻለው። በዚህም ብዙ ጊዜ መጨናነቆችን የሚፈጠረው መመለሻ መንገድ በሚፈልገው ሰው ነው። የዚህ ዓይነት ችግሮች በኮተቤ ካራ፣ በወሰን እና መገናኛ አካባቢዎች ማስተዋላቸውን ጠቁመው በዚህ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎቱን የተሳለጠ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
አሽከርካሪው መዞር እየፈለገ እስከ ጫፍ 500 እና 600 ሜትር ያህል ከሄደ በኋላ ዞሮ ለመመለስ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች አሉ። በዚህም አምስት እና ስድስት ደቂቃዎችን ለመቆየት እና ከፍተኛ መጨናነቆችን ለመፍጠር ይገደዳል። ይህም ተጨማሪ የተሽከርካሪ መጨናነቆችን የሚፈጥር ነው። በኮሪደር ልማቱ የተገነቡት የተሽከርካሪ እና የብስክሌት መንገዶች ለትራንስፖርት አገልግሎቱ የተመቻቹ ናቸው፤ የእግረኛ መሄጃዎቹም ለእይታ ምቹ ከመሆኑም ባለፈ ህብረተሰቡ በቀላሉ በእግሩ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችሉ ናቸው። ማየት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችል ነው። ለመላው ኢትዮጵያውያን አዲሱ ዓመት የሰላም የብልጽግና እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸውም የሀገር ሀብት ፈስሶባቸው አገልግሎት እንዲሰጡ የተገነቡ የኮሪደር ልማቱ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን አሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሁሉም እንዲጠብቅ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የፓርኪንግ አገልግሎት ሲጠቀሙ ያገኘናቸው ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ቲዮቢስታ ኃይለማርያም ለአምስት ዓመታት ያህል አሽከርካሪ ሆነው ቆይተዋል። በእነዚህ ጊዜያት በጥንቃቄ ማሽከርከራቸውንና ምንም ችግር እንዳልገጠማቸውም ጠቅሰዋል። ይሁንና መኪናቸው መንገድ ዳር ሲያቆሙ የደህንነት ስጋት እና ጥርጣሬ ይሰማቸው እንደነበርና ብዙ ምቾት አይሰማቸውም ነበር። አሁን ግን ራሱን የቻለ የመኪና ማቆሚያ ቦታ በመዘጋጀቱ ሃሳብ ሳይገባቸው መኪናን አቆይቶ ወደ ጉዳይ ሄዶ መመለስ ይቻላል። በአራት ኪሎ አካባቢ ለ15 ቀን ያህል የሚከታተሉት ጉዳይ ስለነበራቸው ያለምንም ችግር መኪናቸውን በፍቅር የተሽከርካሪ ማቆሚያ እየተገለገሉ ናቸው። በማቆሚያው የሚጠብቁትም የደህንነት ስጋት ሳይኖር በጥሩ ሁኔታ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
በፓርኪንጉ ከሁለት ሰዓታት በላይ አቆይተው 20 ብር ብቻ መክፈላቸውን ጠቅሰው አገልግሎቱ መንገዶችን ነፃ ከማድረግ፣ ከመኪና እና የመኪና ስፖኪዮ መሰረቅ ችግሮች ያድናል። በከተማዋ የተሰሩት የመኪና ማቆሚያ ሥራዎችንም አድንቀው በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች መስፋት እንዳለባቸው አመልክተዋል። በአዲስ ዓመቱ ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም ምኞታቸውን ገልጸው በማንኛውም አጋጣሚዎች በጥንቃቄ ማሽከርከር እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ብሩክ ፍቃዱ ቸሩ በበኩላቸው በፍቅር የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ማህበር በመንግሥት የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል አንደኛው ናቸው። በማህበሩ 15 ያህል ሆነው የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ሲሆን፤ ከራሳቸው አልፈው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩም ይገኙበታል። አሮጌና አዲስ መኪና ሳይሉ ሁሉንም ተሽከርካሪዎች ታርጋ ሳይለዩ ያለ አድልኦ እንደስሙ በፍቅር እንደሚያስተናግዱ ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል ከኮተቤ አንስቶ በመገናኛ አድርጎ፣ በፒያሳ ወደ አውቶብስ ተራ ወደ ቀጨኔ ለመሄድ በተለይ በምሳ ሰዓት፣ በተማሪዎች እና በሠራተኛ መውጫ ሰዓት ላይ ለመተላለፍ ከፍተኛ ጭንቅንቅ እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ግን በኮሪደር ልማቱ በተሰሩ ሥራዎች አንድም መኪና መንገድ ላይ ቆሞ አይታይም። በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኪና ማቆሚያዎች እየተሰሩ ናቸው፤ መንገዶች ሰፍተዋል፤ አማራጭ መንገዶች ተፈጥረዋል። ይህ መሆኑ ለባለንብረቱም ሆነ ለወጣቶች የሥራ እድል ከመፍጠር አኳያ በመንግሥት የተሰራው ሥራ አበረታች እንደሆነ በአድናቆት ገልጸዋል።
በፓርኪንግ አገልግሎቱ በተለይ በሰንበት ቀን እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት መኪናቸውን ትተው የሚያመሹ እንዳሉ ጠቁመው ከአራዳ ክፍለ ከተማ እና ከአካባቢው ፖሊሶች ጋር በመሆን በንቃት እንደሚጠብቁም ጠቁመዋል። ቅዳሜ ምሽት አልኮል ጠጥተው መኪናቸውን ለመውሰድ የሚመጡ እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ብሩክ፤ በዚህ ጊዜ ታዲያ ለደህንነታቸው ሲባል መኪናቸውን እንዳይወስዱ በማድረግ ሰኞ ቀን መጥተው ይቅርታ ጠይቀው እና አመስግነው መኪናቸውን የሚወስዱ መሆኑን አስታውሰዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በፓርኪንግ አገልግሎቱ የተለያዩ አጋጣሚዎች የሚገጥሙ እንደሆነ በማንሳት መኪና ያቆመው ሰው ብቻ መውሰድ እንደሚገባውም አመላክተዋል።
ምሽት ላይ የአካባቢው ማህበረሰብም ሮንድ በመውጣት በትብብር የሚሰራ ሲሆን፤ ለዚህም ሲሉም በኮሪደር ልማቱ የተገጠሙ ዘመናዊ መብራቶች አጋዥ እንደሆኑና ችግሮች እንደማያጋጥሙ ተናግረዋል። በአንድ ጊዜ ብቻ ሰባት ያህል ሆነው እንዲሁም ከሁለት ጥበቃዎች ጋር ዘጠኝ ሆነው የመኪና ጥበቃ ሥራውን ያከናውናሉ። አሁን ላይ ዘመናዊ አሰራሮች እየተስፋፉ አጥር እየቀረ መሆኑንም በማስታወስ በቀጣይ በመሰል የፓርኪንግ አገልግሎቶች ከሰዎች በተጨማሪ በካሜራ መታገዝ እንደሚገባቸው እና አንዳንድ የስርቆት አጋጣሚዎችን መከታተል እንደሚገባም አመላክተዋል።
በመጨረሻም የዚህ ዓይነት የፓርኪንግ አገልግሎቶች በየቦታው ተስፋፍተው ለወጣቶች የሥራ እድል እንዲፈጠር ወጣቱም ሥራ ሳይመርጥ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰርቶ ሀገሩን እና ሕዝቡን እንዲያገለግል ሲሉም አመላክተዋል። እንዲሁም ወታደሩም በድንበሩ ዜጋውም በሀገሩ ጉዳይ ሁሉም በየተሰማራበት አንድ ሆኖ ሀገሩን እንዲያገለግል፤ በሰላም በመተሳሰብ አዲሱን ዓመት በፍቅር እንዲቀበል መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በራማ ኮንስትራክሽን የቢሮ ምህንድስና ክፍል ኃላፊ ኢንጂነር ሄኖክ ቢያደርገው በበኩላቸው በአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሕንፃ ፊት ለፊት የተሰራው የተሽከርካሪ ማቆሚያው በከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ መሠረት በራማ ኮንስትራክሽን የግንባታ ሥራው ተከናውኖ ለአገልግሎት የበቃ ነው። ይህም ከዚህ ቀደም የነበረውን ሳይጨምር 1300 ካሬ ያህል ቦታ ላይ ተገንብቶ በአንድ ጊዜም ከ100 በላይ መኪኖችን ለማስተናገድ የተዘጋጀ ነው። ለአካባቢው ወጣቶችም የሥራ እድል ከፍቷል፤ መኪኖችም በአካባቢው መንገድ ዳር መቆም ስለማይችሉ በማቆሚያ ፓርኩ እየተስተናገዱ ነው። የመኪና ማቆሚያው የተሰራበት ደረጃም አፈሩ ተስተካክሎ፣ ሰብቤዝ ማቴሪያል፣ ቤዝኮርስ ማቴሪያል እና አስፓልት ንጣፍ ተሰርቶለት ነው። እንዲሁም ከርቭ ስቶን ሥራም በተጨማሪ ተሰርቶለታል። ተጨማሪ የመንገድ ዳር መብራቶችም ለመኪና ማቆሚያው ተጨማሪ ሰዓታት አገልግሎት ለመስጠት ያስቻለ ነው። በመኪና ማቆሚያው የመፀዳጃ ቤት ግንባታ እና የሻወር አገልግሎትን ጨምሮ የዊልቸር ተጠቃሚዎችን ታሳቢ ተደርጎ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢንጂነር ሄኖክ የራማ ኮንስትራክሽን ለማህበረሰቡ የተሻለ እና ምቹ አገልግሎት የሚሰጡ የግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ እሳቸው ከአራዳ ክፍለ ከተማ እስከ ሲኒማ አምፒር ያለውን መንገድ እና በመሃል የሚሰራውን 120 ሜትር ድልድይ ግንባታ እያከናወነ ይገኛል። ድልድዩ ሀገር ውስጥ ብዙም ባልተለመደ እና ወጥ በሆነ መልኩ የሚገነባ በኬብል የሚሰራ ነው። መንገጫገጭ በማይኖረው መልኩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰራ ነው። በዚህ ረገድ ከዝናቡ በስተቀር ተግዳሮት አልገጠመም። ከሁሉም ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ሲሉም በሜጋ ፕሮጀክት በኩል፣ በአማካሪነት በመነጋገር እና በመግባባት 24 ሰዓት እየተሰራ ነው ብለዋል።
እስካሁንም የመሠረት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው እስከ ቀጣይ አራት ወራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል። ድልድዩንና መንገዱን አጠቃሎም ከ300 ሰው በላይ የሥራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል። አቋራጭ መንገዱ ሲጠናቀቅ ከቅድስት ማሪያም እንደ መጣ ወደ ፒያሳ የሚሄደውን መንገድ የሚያሳጥር ነው። ቀደም ሲል ከራስ መኮንን ድልድይ እስከ አምፒር ድረስ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ያስቀራል። ቀጥታ ወደ ጣይቱ መንገድ ካስፈለገም በአምፒር በመሄድ የትራፊክ ፍሰቱን የሚያስተካክልና ለማህበረሰቡም የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚያሰፋ መሆኑን አመላክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም