አፍሪካ የጥቁር ህዝቦች ምድር፣ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች፣ የቱባ ባህል መፍለቂያ መሆኗ እርግጥ ነው። ይሁን እንጂ በእነዚህና በሌሎች ፀጋዎቿ ከመታወቋ ባልተናነሰ በግጭት ቀጣናነት፣ በተደጋጋሚ በረሀብና ድርቅ ተመቺነት፣ በዴሞክራሲ እጦት ፣ በመልካም አስተዳደር ብልሹነት፣ ስር በሰደደ ሙስና፣ ኋላቀርነት … ትታወቃለች።
አፍሪካ ውስጥ ሰላማዊ አካባቢን ከመፈለግ ቀላሉ በርስ በርስ ጦርነት የሚታመሱ አገራትን መፈለጉ ይቀላል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ይህንንም ለማረጋገጥ አንዱና የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን የአፍሪካ ህብረትን ሰነዶች ማገላበጥ ብቻ ይበቃል።
የአፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ ለመረዳት የቅርቧን ደቡብ ሱዳንን መጥቀሱ በቂ ማስረጃ ነው፤ ዜጎች ምን አይነት ስቃይ ውስጥ እንዳሉ ይታወቃልና። ሶማሊያ ከመንግስት አልባነት ተላቀቀች እንጂ ዛሬም ዜጎች እየሞቱ ነው። ለጊዜው እነዚህን እንጥቀስ እንጂ አፍሪካ ውስጥ እዚህም እዚያም ጥይት ይጮሀል፣ ቦንብ ይፈነዳል፣ ፈንጅ ይጋያል፣ ድርቅና ረሀቡ ፋታ ሳይሰጥ በዙር ይፈራረቃል፣ ወረርሽኙ በሺዎች እየገደለ ነው፤ የስደቱ ነገር አይነሳም። የነዚህን ችግሮች መሰረታዊ ምክንያት ለማወቅ አጥኚዎች ያረፉበት፣ ጥናቶች የተቋረጡበት፣ መሪዎች ያልመከሩበትን ጊዜ ማግኘት ይከብዳል። ሰሞኑን ግሎባልኢሹ ዶት ኦርግ እንዳሰፈረው ችግሮቹ ውሰብሰብ፣ መፍትሄያቸው በውል ያልተገኘ፣ ገና በሰፊው መጠናትና መመርመር ያለበት ጉዳይ ነው – የአፍሪካ ችግር።
ከተዘረዘሩትና አፍሪካን ቀስፈው ከያዝዋት ችግሮች መካከል የእርስ በርስ ጦርነትና የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ቀጥለን ሩብ ምዕተ አመትን ያስቆጠረ፣ ዛምቢያንና ማላዊን እያናጨ ያለውንና መፍትሄ የራቀውን የድንበር ውዝግብ ጉዳይ እንመለከታለን።
ሁለቱ አገራት በደቡብ ማዕከላዊ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆን 800 ኪ.ሜ የሚሸፍን ድንበር ይጋራሉ፣ ወሰንተኞች ናቸው። ከጉርብትናቸው በዘለለ የሚያመሳስላቸውና የጋራ ጉዳይ አላቸው ከተባለ ሁለቱም በእንግሊዝ ቅኝ የተገዙ መሆናቸውና በ1964 ነፃ መውጣታቸው ነው።
ዘመኑ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ገዥዎቻቸው ነፃ የወጡበትና ሉዐላዊ አገርነታቸውን ያወጁበት ወቅት በመሆኑ አንዱ ከአንዱ የሚለይበትን ድንበር መከለል የግድ የሆነበትም ነበር። ይሁን እንጂ መከለል ማስፈለጉን የመስማማታቸውን ያህል አከላለሉ እንደተጠበቀው ቀላል ሆኖ አልተገኘም።
ሰሞኑን ስተዲ ዶት ኮም ድረ-ገፅ እንዳስነበበው በአገሮች መካከል ሊካሄድ የታሰበው ድንበር የመካለሉ ሂደት አገራቱን ወደ አልተፈለገ ግጭትና ውዝግብ አስገባቸው እንጂ እንደተጠበቀው አልጋ በአልጋ ሆኖ አልተገኘም። የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረትን የመሳሰሉት አለም አቀፍ ተቋማት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ሁሉ ለተለያዩ ፈተናዎች ዳረጋቸው እንጂ የተፈለገውን ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በተለይ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከ2004 ጀምሮ አቅጣጫ በማስቀመጥ ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አገራት በጋራ የድንበር ማካለልን ተግባር በአስተማማኝ ደረጃ እንዲያከናውኑና እስከ 2010 ድረስም እንዲያጠናቅቁ ጥረት ቢያደርግም ሊሳካ አልቻለም የሚለው የድረ-ገፁ የግጭት ተንታኝ ኖንቶቤኮ ሂደቱ አገሪቱ የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ሊያሳኩት እንዳልቻሉ ያብራራል። ለዚህም ዛምቢያንና ማላዊን በማስረጃነት ያቀርባል። በመሆኑም ይላል ኖንቶኬኮ ”ጉዳዩ ወደ 2017 ተገፋ።”
ማላዊ በ1993 የራሴ የምትለውን መልክዐ ምድሯን በመለየት ከለለች። ይህንኑ ተከትሎ በተደረገ ትክክለኛነቱን የማጣራት ስራ ተከተለ። ጉዳዩን እንደገና ማየት ያስፈልጋል ተባለና በሁለቱ አገራት አማካይነት እንደገና የማካለል ሥራው ተሰራ። ይህም ከአራት ወረዳዎች በላይ መሬትን ለዛምቢያ ይሆን ዘንድ አስገደደ። የማላዊ የመሬት ቤቶችና ከተማ ሚኒስትር ጂን ካቢሲ “ወሳኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም” በማለት አጣጣሉት። ሌላ ስምምነት እስኪደርግ ድረስ ህዝቡ ባለበት ሆኖ ተረጋግቶ መኖር አለበት፤ ዜግነቱንም መለወጥ የለበትም።” ሲሉም ለፓርላማው በማብራራት የመንግሥታቸውን አቋም ገለፁ።
ይህም ዛምቢያን አስቆጣ፤ ተገፋፍታ እርምጃ ወደ መውሰድና ትምህርት ቤቶችን እስከማውደም ደረሰች። ይህም የአካባቢውን ነዋሪ ለፍርሃትና ስጋት ዳረገ፤ እስካሁንም በዚሁ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይኖራል ሲል ኒያሳ ታይምስ ገልጿል።
በአወዛጋቢው ድንበር አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ከተነፈጉት መብቶቹና ከግጭቱ የተረፈው ጉዳይ ቢኖር የአካባቢው ችግር እስኪፈታ ድረስ ምንም አይነት ተጨማሪ ተግባር (ቤት የመስራት፣ ተጨማሪ መሬት የማልማት…) የማከናወን፤ በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት የለውም። ለነዋሪው የተሰጠ መበት ቢኖር ባለበት የመቀመጥና ሲሞት የመቀበር መብት ብቻ ነው።
ይህ መነሻውን 1855፣ ሰበቡን ማላዊ ሀይቅን ያደረገው የዛምቢያ-ማላዊ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ ማላዊን ከዛምቢያ ጋር ብቻ አይደለም እያወዘገባት ያለው፤ ከ1967 ጀምሮ ይሄው ሀይቅ ከታንዛኒያም ጋር እያነታረካት ይገኛል።
ይህን 804.5 ኪ.ሜ በሚሸፍነው አዋሳኝ ድንበር ምክንያት የተነሳውን አለመግባባት ለመፍታት የሁለቱ አገራት መሪዎች በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አቋሞችን በመያዝና ወደመፍትሄው ማቅናት ባለመቻላቸው ችግሩ እስካሁን ሊፈታ አልቻለም። ምንም እንኳን በይፋ ወደ ድርድር ከመጡ 25 ዓመታትን ቢያስቆጥሩም ጠብ ያለ ነገረ የለም፤ አሁንም እዛው ናቸው።
አፍሪካ ህብረትስ ምን ይላል?
መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ህብረት የአህገሪቱ ተወካይና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ተቋም ነውና ከሱ ብዙ እንደሚጠበቅ ይታወቃል። በመሆኑም ይህ ማባሪያ የሌለው ውዝግብ ቅኝ ገዥዎች የፈጠሩት ሴራ መሆኑንና የአፍሪካ አገሪት መሪዎችም ይህንኑ ተገንዘበው የደንበር ይገባኛል ውዝግቦች ወደግጭት እንዳያመሩ፤ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፤ ቋሚ ወሰናቸውንም በዘላቂነት እንዲያረጋግጡ … በሚል መነሻ በርካታ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፍና አስፈፃሚ አካላትን ሲያቋቁም ረጅም ዓመታትን አስቆጥሯል።
በየግዜው ከህብረቱ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ1964 ጀምሮ እስከ 2010 ድረስ በርካታ ፖለቲካዊና ሕጋዊ ማእቀፍ ያላቸውን ድንጋጌዎች ሲያወጣ ቆይቷል። ይሁን እንጂ የህብረቱን ስምምነቶች፣ ውሳኔዎች፣ … የተቀበሉና ችግሮቻቸውን በመፈተሽ ወደመፍትሔ የመጡ አገሪት ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለመመሪያና ደንቦቹ ተገዥ ከሆኑት ናይጄሪያና ካሜሩን፣ ናሚቢያና ቦትስዋና፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በስተቀር ሌሎቹ ከውዝግብና ለህዝቦች መከራን ከማትረፍ ውጪ እስካሁን የፈየዱት ነገር የለም።
እንደ አይ.ኤስ..አፍሪካ ዶት ኦርግ ዘገባ በአወዛጋቢ ድንበሮች ሰበብ ያላባራ ግጭትና ውዝግብ፣ በአካባቢው ነዋሪዎች መካከልም መሬቶችን ማዕከል ያደረገ ጦርነት ብቻ ነው ማትረፍ የተቻለው። በመሆኑም ይላል ዘገባው ህብረቱ የፓን-አፍሪካን ራዕይ እውን ማድረግም ሆነ ለ2063 እደርስበታለሁ ያለውን ከግጭት የፀዳች አፍሪካን የማየት ዕቅዱን የማሳካቱ ጉዳይ ያጠራጥራል።
ዘገባው ጥናቶችን ጠቅሶ እንዳሰፈረው እስካሁን ድንበራቸው በትክክል የተወሰነ፤ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ የፈቱ የአፍሪካ አገራት አንድ ሦስተኛ ብቻ ናቸው። የተቀሩት ገና ውዝግብና ግጭት ውስጥ ሲሆኑ፤ አወዛጋቢ አካባቢዎቹም ከቁጥጥር ውጪ የከባድ ወንጀሎች መፈልፈያና የወንጀለኞች መናኸሪያ ሆነዋል። ሽብርተኝነትና ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን የመሳሰሉ ህገወጥ ተግባራት የዚህ ማሳያዎች ናቸው።
ስለ ዛምቢያ-ማላዊ የድንበር ውዝግብ ትኩረት ሰጥቶ የዘገበው ዲደብሊው.ዶት ኮም እንዳጠቃለለው ይህ አፍሪካን እያተራመስ ያለው የድንበር ውዝግብ ቅኝ ገዥ ኢምፔሪያሊቶች ከ1880ዎቹ ጀምሮ ሲያራምዱት የነበረው አፍሪካን የመቀራመት አባዜና 1884ም በበርሊን ጉባኤያቸው “በ1914 በአፍሪካ የቅኝ ተገዢ አገሪቱን መጠን 90 በመቶ” ለማድረስ የወጠኑት መርዘኛ ዕቅድ ውጤት ነው፤ ውሳኔው በተላለፈ በዓመቱ የተጀመረው የዛምቢያ-ማላዊ ውዝግብን ጨምሮ።
የአፍሪካ ህብረት ተከታታይ መግለጫዎች እንደሚያመለክቱት የአፍሪካ አገራት ለህብረቱ ደንብና መመሪያዎች በተለይም ለኒያሜይ ስምምነት ተገዥ በመሆኑን ለችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ፤ አገራትን በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ ነፃ ዝውውር …እንዲተሳሰሩ በማድረግ ሰላም፣ ፍትህ፣ እኩልነት የሰፈነባት፤ አንድ የበለፀገች አፍሪካን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
ህብረቱ በየዓመቱ ሰኔ 7 “African Border day” በሚል የተሰየመውን አፍሪካ ድንበር ቀንን የሚያከብር ሲሆን፤ በ2022 የድንበር ውዝግቦች ሙሉ ለሙሉ ይወገዳሉ ሲልም ግብ አስቀምጧል፤ ሩብ ክፍለ ዘመንን የዘለቀው የዛምቢያ -ማላዊም ሆነ የዛምቢያ – ታንዛንያ፤ እንዲሁም የሌሎች መሰል ውዝግቦች በተጠቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲፈቱና አፍሪካ ለአፍሪካውያን ምቹ ምድር ትሆን ዘንድ የአብዙዎች ምኞት መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
ግርማ መንግስቱ