አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ከቱሪስቶች ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ 2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስትራቴጂክ እቅድ የመጨረሻ ዓመትና ለቀጣዩ አምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ መሸጋገሪያ በመሆኑ ከቱሪዝም ማግኘት የታቀደውን ገቢ ለማሳካት ከፍተኛ የሆነ ርብርብን የሚጠይቅ ነው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት 23 ሺህ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እና አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በማስተናገድ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የክልሉን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች በማልማትና በማስተዋወቅ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ መጥተው እንዲጎበኙ የማድረግ ሥራ እንሠራለን ብለዋል፡፡
የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ጥበቃና እንክብካቤ የማድረግ እና የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያቀርቡ በማድረግ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ የማራዘም ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የቱሪስት መዳረሻ ባሉባቸው አካባቢዎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሆቴሎች፣ ሎጂዎችና ሪዞርቶች በአግባቡ በመገንባት ለቱሪስቶች ምቹ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ገልጸው፤ በገበታ ለሀገር ንቅናቄም የአካባቢውን ወግና ባሕል ጠብቆ የተሠራው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ግንባታ ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ለአካባቢው ገጽታ ግንባታ፣ ሌሎች አልሚዎችን ለመሳብ እና የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያበረክት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በገበታ ለትውልድ ንቅናቄም የሎጎ ሐይቅ ኢኮ ሪዞርት ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይ ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ይሆናል ብለዋል፡፡
ለነባር የቱሪስት መዳረሻዎች ጥገና እና እንክብካቤ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸው፤ በ2016 በጀት ዓመት ክልሉ 74 ሚሊዮን ብር በመመደብ እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ 32 ለሚሆኑ ልዩ ልዩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የጥገና ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን የመሥራት እና ለነባሮቹ ጥበቃና እንክብካቤ የማድረግ ሥራ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም የቱሪስቶችን ደኅንነት በመጠበቅ የክልሉ ታሪካዊና ባሕላዊ ቦታዎች እንዲጎበኙ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ እስከ የካቲት ወር ድርስ በርካታ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ የአደባባይ በዓላት መኖራቸውን ገልጸው፤ በዓላቱን እሴታቸውን ጠብቆ በማክበር ቱሪስት እንዲገኝባቸው ይደረጋሉ ብለዋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የክልሉን የቱሪስት መዳረሻዎች የማስፋፋትና ለቱሪስት ምቹ የማድረግ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ በተሠራው ሥራም በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ክልሉን እንደጎበኙት በማድረግ ከሦስት ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡
ክልሉ የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያን፣ የጎንደር ቤተ መንግሥት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በባሕርዳር ከተማ ዙሪያ ያሉ የጣና ገዳማትን ጨምሮ የበርካታ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቦታዎች መገኛ በመሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 8 /2016 ዓ.ም