መንግሥት በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ ያሸጋገረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በሰነዱ ተገልጿል፤ በማሻሻያው ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ የሚመለከታቸው ሃላፊዎችና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ይህንኑ በሚገባ አስረድተዋል::
ማሻሻያው መተግበር መጀመሩን ተከትሎ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ብድር የተገኘበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል:: ለልማቷ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ለሚያስፈልጋት ሀገር እነዚህ ተቋማት ፋይናንስ ማቅረብ መጀመራቸው በራሱ የማሻሻያው ሌላው ፋይዳ ተደርጎ የሚወሰድ ነው:: የእነዚህን ተቋማት ድጋፍ ተከትሎ ሌሎች አበዳሪ ተቋማትና ያደጉ ሀገሮች ተመሳሳይ የልማት ፋይናንስ ሊያቀርቡ የሚችሉበት ሁኔታም ሊከተል ይችላል ብሎ ማሰብም ጥሩ ነው::
ማሻሻያው ወደ ትግበራ መግባቱን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያም ሕገወጥ የውጭ ምንዛሬ ግብይት እየተዳከመ እንዲሄድ፣ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የቆየውም የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት በነጻ ገበያ እንዲመራ ማድረግ የሚያስችል ነው:: የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ መደረጉን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ ልማታቸውን ለማቀላጠፍና ለመሳሰሉት ተግባሮች የውጭ ምንዛሬ በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው ተቋማትም ስር ነቀል ርምጃ ሲሉ ገልጸውታል:: ጥቁር ገበያ በውጭ ምንዛሬ ግብይት ውስጥ እንዳሻው የሚሆንበትን ሁኔታ እንደሚቀይረውና ሀገርና ሕዝብ በውጭ ምንዛሬ በሚገባ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን ሁኔታ እንደሚያመጣ ታምኖበታል::
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ይዞ የመጣው ቱሩፋት ትልቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በአተገባበር ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ስለመኖራቸውም እየተነገረ ነው ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በሕገወጦች ሊፈጠር የሚችል የሸቀጦች እጥረት ፤ ከዚህ የተነሳ ሊያጋጥም የሚችል የዋጋ ንረት ነው። በርግጥም ችግሩ ማሻሻያው መተግበር በተጀመረ ማግስት መታየት ጀምሯል። እንደ ዘይት ባሉት ሸቀጦች ላይ ብቻ ሳይሆን በግብርና ምርቶች ላይም ሳይቀር ያልተገባ የዋጋ ጭማሪው ታይቷል:: የኢንዱስትሪ ምርቶችን መደበቅም እየተስተዋለም ነው::
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ መንግሥት እንደ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ያሉ መሰል ርምጃዎችን ሲወስድ የዋጋ ለውጥ ሊታይባቸው የሚችለው ከውጭ የሚመጡ እቃዎች ናቸው:: የግብርና ምርቶች የዋጋ ለውጥ ሊታይባቸው አይገባም፤ ከውጭ የሚመጡ የኢንዱስትሪ ምርቶችም ቢሆኑ ዋጋ ጭማሪ ሊታይባቸው የሚገባው ከስድስት ወር በኋላ ነው:: አሁን ግን መጋዘንና መደብር ውስጥ ባለው ምርት ላይ ነው ዋጋ እየተጨመረ ያለው፤ ለዚያውም ከፍተኛ መጠን ያለው ዋጋ::
እንዲህ አይነቱ ሕገወጥነት ተግባር ፊትም ሀገርና ሕዝብን ይፈትን የነበረ፣ አሁን መፈተኑን የቀጠለ ነው:: ይህ ለምን ይሆናል ብሎ በመጠየቅ አሁንም ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት መሥራት ያስፈልጋል:: ከዚህ አኳያ መንግሥት ችግሩን ለመከላከል ፈጥኖ የሄደበት መንገድ የሚበረታታ እና የሚደገፍ ነው።
ምርቶችን የደበቁ ፣ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ መደብሮች ወይም ንግድ ቤቶች ባለቤቶችን ከሕገወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ከማስገንዝብም አልፎ መደብራቸውን የማሸግ ተግባርም እየፈጸመ ነው:: ባልተገባ ተግባራቸው እየቀጣቸው እንዳለም በየቀኑ በሚወጡ መረጃዎቹ እያሳወቁ ነው:: በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ርምጃው ከዚህም ተሻግሮ ተደብቆ የተገኘ ምርትን በመውረስ በሸማቾች ማህበራት በኩል ለሕዝብ እንዲሸጥም ተደርጓል::
ርምጃው በእዚህ ልክ እየተወሰደ እያለ፣ ከዚህም ሌሎች ሕገወጦች ትምህርት እንዲወስዱ ለማድረግ ርምጃው በመገናኛ ብዙሃን እንዲተላለፍ እየተደረገም፣ አሁንም ሕገወጥ ተግባሩ ተጠናክሮ በአደባባይ መቀጠሉን እየተመለከትን፣ እየሰማን ነው:: ከዚህ መረዳት የሚቻለው ርምጃው የሚያም እንዲሁም በሁሉም አካባቢ ሕገወጥ ተግባሩን በሚመጥን መልክ እየተፈጸመ አለመሆኑንም ነው::
አሁንም ርምጃው በሁሉም አካባቢ በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል ያስፈልጋል ። ርምጃው ወንጀሉ ሊያስከትል ከሚችለው ሀገራዊ ጥፋጥ አንጻር የሚሰላ ሊሆን ይገባል። ሕገወጦች ተመልሰወው በተመሳሳይ ተግባር እንዳይሳተፌ አስተማሪ መሆን አለበት:: ርምጃውን እንደ ድብብቆሽ ጨዋታ የሚመለከቱ፣ በእዚህ አይነት ወቅቶች በሚያጋብሱት ሀብት ያደርጉትን ያጡ ፤ የሰቡ ሕገወጦች በሀገሪቱ እንዳሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው:: ይህ አይነቱ ድርጊት አሁን ላይ መቆም አለበት:: መቆም ካለበት ደግሞ ወቅቱ አሁን ነው::
የሀገርን የዜጎችን እጣ ፈንታ ለመቀየር ፣ ተብሎ የተደረገን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚያውክ ተግባር መፈጸም ማለት ለሀገርም ፤ ለሕዝብም ቅንጣት ታህል አለማሰብ ነው:: ይህን አይነቱን ሕገወጥነት ለድርጊቱ በሚመጥን ርምጃ ነው ማስቆም የሚገባው:: እናም ይህን ማድረግ ይገባል::
ማሻሻያው በሁነኛ መሠረት ላይ የቆመ ነው:: መንገራገጭ ሊያጋጥመው ይችል ይሆናል እንጂ ወደ ኋዋላ ሊመለስ የሚያስገድደው ሁኔታ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም የለም:: ሀገሪቱ ምጣኔ ሀብቷን ለማሳደግ የሕዝቡን ሕይወት ለመለወጥ ተግባራዊ ያደረገችው ማሻሻያ በምንም መልኩ ወደኋዋላ እንደማይመለስ ለጠላትም ለወዳጅም ማስገንዘብ የሚያስችል ርምጃ በእነዚህ ሕገወጦች ላይ በመውሰድም ትግበራውን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል:: ትግበራው በሕገወጦች ሊያጋጥሙት በሚችሉ ችግሮች ለአፍታም እንዳይንገራገጭ እነዚህ ቀበኞች ሕጋዊ መስመር እንዲከተሉ ማድረግ ይገባል::
ህብረተሰቡ በትግበራ ወቅት ሊያጋጥሙት የሚችሉትን የአቅርቦት ችግሮች ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች የእነዚህን ሕገወጥ ነጋዴዎች ሴራ ለማምከን በሚያስችል መልኩ መከናወን አለባቸው:: የሸቀጥ አቅርቦት እየተጓጓዘ መሆኑ በመንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ተጠቁሟል፤ ምርቶቹን በፍጥነት በሸማቾች ማኅበራት በኩል የድጎማው ተጠቃሚ ለሚሆነው ማህበረሰብ በአስቸኳይ እንዲደርስ ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህ ሲሆን ነጋዴው ምርቱን ታቅፎ ስለማይቀመጥ ወደ መሸጥ ይገባል::
ሕገወጥ ነጋዴዎች የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በመፍጠር ህብረተሰቡን ሲያቆስሉት ኖረዋል:: እነሱ በአንጻሩ በሕገወጥ ድርጊታቸው ከብረዋል:: ዛሬም በዚሁ በለመዱት መንገድ ቀጥለዋል:: ባለፉት ጊዜያት በትንሹም በትልቁም ምክንያት በምርቶች ላይ ዋጋ ሲጨምሩ ኖረዋል ፤ ይህን ሁሉ ሲያደርጉ የረባ ቅጣት አልደረሰባቸውም:: ቢደርስባቸው “የማንትስን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም “ይሉ ነበር::
ይሄ ድርጊት አንድ ቦታ ላይ መቆም ነበረበት፤ ግን እንዲቆም አልተደረገም፤ አልቆመም:: ችግሩን የመፍታቱ ሥራ ከማስፈራራት፣ ሱቅ ከማሸግ፣ ብዙም የዘለለ አይደለም:: ይህ አሠራር በእጅጉ ተለምዷል:: በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ ማግስት ሕገወጥ ነጋዴዎች ህብረተሰቡን በዋጋ ጭማሪ ለመበዝበዝ ሆ ብለው የተነሱት በተለመደው መንገዳቸው የሚሳካላቸው መስሏቸው ነው፤ በዚህ ወሳኝ ወቅት ከቀጠለው ሕገወጥ ድርጊት መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው::
የእነዚህ ሕገወጦች ድርጊት የሆነ ቦታ ላይ እንዲቆም ፣ እንዲለዝብ ማድረግ ይገባል:: ለእዚህ ደግሞ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩትም ከዚህ ወቅት የተሻለ ጊዜ የለም:: አሁን በሕገወጥ ድርጊት በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የፈጸሙትን ድርጊት የሚመጥን ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል::
ማስፈራራት፣ ሱቅ ማሸግ ምናልባትም መውረስ ብቻቸውን በቂ አይደሉም፤ ከንግዱ ሥራ ውጪ ማድረግና በሌላ ሕግም መጠየቅ ድረስ የዘለቀ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል:: ሕገወጦች ሲያመሩ መንግሥትም ማምረር ነው ያለበት:: እናም መንግሥት ያምርር እላለሁ::
ህብረተሰቡም ኮሽታ ተፈጠረም አልተፈጠረም ነጋዴዎች በሚፈጥሩት ውዥንብር በመታለል ምርቶችን ለመሰብሰብ መሯሯጥ ውስጥ መግባት የለበትም:: “የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል“ እንደሚባለው ነጋዴዎች ግርግርና ወከባ በማብዛት ያልተገባ ዋጋ ይጠይቃሉ፤ ምርት ይደብቃሉ:: ጥራት ያጎድላሉ:: ህብረተሰቡ በእዚህ አይነቱ ድርጊት ዘመናትን ተጎድቷል:: ይህ ድርጊት እንዳይቀጥል ማድረግ ይገባል::
ለእዚህም ባለፉት ዓመታት ከፈጠሩት ሕገወጥ ድርጊት ብዙ መማር ያስፈልጋል:: ከዚህ ይልቅ ሕገወጦችን ማጋለጥ፣ ምርት ለመግዛት አለመስገብገብ ፣ በማሻሻያው ላይ የግንዛቤ እጥረት ያለባቸውን ማስገንዘብ ያስፈልጋል። ለሀገርም ለሕዝብም የሚበጀው ይኸው ነው::
እስመለአለም
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5 / 2016 ዓ.ም