የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2011 በጀት ዓመት የመንግስት የስራ አፈጻጸም ትናንት ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው የሰላም፣ የዴሞክራሲና ጸጥታ ጉዳዮች፣ ኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲ፣ በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮችን እና አሁን ያለው አጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታ ዳስሰዋል።በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኮረውን ሪፖርት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የኢኮኖሚ ዕቅድ አፈጻጸም
በያዝነው የበጀት ዓመት ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ፣ እንዲያገግም፣ የተዛቡ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አመልካቾች እንዲቃኑና በሁሉም አቅጣጫ ኢኮኖሚው አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ሊደርስ እንዲችል የተለያዩ የማሻሻያ ተግባራት ተከናውነዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ በዓመቱ የተያዘው የመጀመሪያ ዕቅድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በአጠቃላይና የፋይናንስ ዘርፉን በተለይ ወደ ቀውስ እንዳይገባ በመከላከል እንዲያገግም ማድረግ ነበር።ሁለተኛው ዋና የኢኮኖሚ ዘርፍ እቅድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ጥቅል ፍላጎትን መሠረት ካደረገ የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅስቃሴ ገበያ ላይ ወደ ተመሠረተ ለአቅርቦት ወደሚያደላ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲሸጋገር ማድረግ ነው።አጠቃላይ የ2011 የበጀት ዓመት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከላይ በተገለጹ ሁለት ዋና ዋና የዕቅድ ሐሳቦች እየተገራና እየተመራ የተፈጸመ ሲሆን በየንዑስ ዘርፉ የነበረው አፈጻጸም የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ማክሮ ኢኮኖሚ
የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን በተመለከተ የማክሮ ኢኮኖሚ ዋና ዋና አመልካች ተደርገው ከሚወሰዱ የኢኮኖሚ ማሳያዎች አንዱ የዕድገት ምጣኔ እንደሆነ ይታወቃል።የሀገራችን ኢኮኖሚ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በፍጥነት ሲያድግ ቆይቷል።ይህም ዕድገት የነበረውን ድህነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በተከተልነው የልማት ፋይናንስ ሞዴል ችግርና ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በገጠሙን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች የተነሣ የኢኮኖሚያችን የዕድገት ምጣኔ ከዓመት ወደ ዓመት ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።ከ2008 – 2010 የበጀት ዓመት ባሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት አማካይ ዕድገቱ 8 ነጥብ 65 ሲሆን የ2010 የበጀት ዓመት እድገት ብቻውን ሲታይ ደግሞ 7 ነጥብ 75 ነበር፡፡
የ2011 የበጀት ዓመት ዋናው ዕቅዳችን ኢኮኖሚያችን ካጋጠመው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትና ከተጫጫኑት ወቅታዊ ችግሮች እንዲያገግም ለማድረግ ነበር።የ11 ወራት የሸቀጦች ንግድ አፈጻጸም ከተቀመጠው ግብ አኳያ ዝቅተኛ ከመሆኑ በስተቀር የኢኮኖሚያችን አጠቃላይ የፍላጐትና የአቅርቦት እንቅስቃሴው ሲታይ ማገገማችንን የሚያመለክት መሆኑን መረጃዎቹ ያሳያሉ።የተለያዩ የኢኮኖሚ ጠቋሚዎችን (Economic Indicators) ወስድን ስንመለከት በዘንድሮው በጀት ዓመት ኢኮኖሚያችን እስከ 9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ያመለክታል፡፡
የሥራ እድል ፈጠራ
ኢኮኖሚያችንን አጋጥሞት ከነበረው ሥር የሰደደ መዋቅራዊ ችግር ተፅዕኖ በማላቀቅ ቀውስ ሳይፈጠር ማደግ ወደሚያስችለው ሁኔታ መመለሱ ትልቅ ውጤት ሆኖ ሊመዘገብ ይችላል። በተጀመረው መንገድ ሁኔታዎችን በማሻሻል ከቀጠልን የመጪው በጀት ዓመት እድገት የተሻለ ይሆናል የሚል ተስፋ አለ።የሥራ እድል ፈጠራን በተመለከተ፡ ከማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም አመልካቾች ውስጥ ሌላው ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የሥራ እድል ፈጠራ አፈጻጸም ነው።በሀገራችን አጠቃላይ የሥራ አጥ ቁጥር ከ11 ሚሊዮን በላይ ሲሆን በዚህ ላይ በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን ያላነሰ የሰው ሃይል ወደ ሥራ ፈላጊው ገበያ ይቀላቀላል ተብሎ ይገመታል።ነገር ግን ኢኮኖሚው እስከ አሁን በዓመት የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ከአንድ ሚሊዮን አይዘልም።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የተቋቋመው ኮሚሽን ወደ ተግባር ገብቷል።እስከ መጪው የበጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ለ3 ሚሊዮን ዜጎች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ ቢሆንም በ2011 የበጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በአብዛኛው የተፈጠሩት የስራ እድሎች የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማትን በመጠቀም የተፈጠሩ ናቸው።
የተፈጠረው የሥራ እድል ቀደም ባሉት ዓመታት ከነበረው የተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ያላነሰ ቢሆንም ካለን ከፍተኛ የሥራ ፈላጊ ቁጥር አንጻር በቂ ነው የሚባል አይደለም።ከዚህ በኋላ የኢኮኖሚያችን ዕድገት ውጤታማነት ከሚለካባቸው መመዘኛዎች አንዱ ኢኮኖሚው ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል አንጻር መሆን ይኖርበታል።እስከ አሁን ድረስ እየተከተልናቸው ያሉ የሥራ እድል መፍጠሪያ መንገዶች በመንግሥት ጥረት ላይ የተመረኮዙ፤ በሜጋ ፕሮጀክቶችና በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት እንዲሁም በመጠነ ሰፊ የሕዝብ አገልግሎት መሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራ ምህዳር በመጪዎቹ ጊዜያት በግሉ ዘርፍ ተጨማሪ ሠራተኞችን መያዝ እንዲችል ማበረታታትና በውጭ ሀገር የሥራ ዕድል ፕሮግራም ያልሠለጠነ ሰው ከመላክ የሠለጠነ ባለሙያ ወደ መላክ መሸጋገር አለብን፡፡
የመንግሥት ገቢና ወጪ
የመንግሥት ገቢና ወጪ በጀት አፈጸጸም ሌላው የማክሮ- ኢኮኖሚ አፈጻጸም ወሳኝ አመልካቹ የመንግሥት ገቢና ወጪ አፈጻጸም ሁኔታ ነው።ባለፉት የበጀት ዓመቱ 11 ወራት 178 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን ይህ አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ሲታይ በ10 በመቶ ብልጫ አለው።በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የሚሰበሰበው ገቢ ቢያንስ 189 ቢሊዮን ብር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።ይህ አፈጻጸም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው የ 176 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው።በአጠቃላይ በገቢ አሰባሰብ የዕቅዳችንን ከ80 በመቶ በላይ እናሳካለን የሚል ግምት አለ፡፡
የወጪ አፈጸጸም በተመለከተ በ2011 የበጀት ዓመት የፌዴራል ወጪ በጀት በመነሻው ወቅት ከተቀመጠው የሚበልጥ ሆኖ አይታይም።የበጀት ጉድለቱም የ2011 በጀት ዓመት ሲጸድቅ ከተቀመጠው ገደብ ባልበለጠ ሁኔታ የሚፈጸም ይሆናል።በአጠቃላይ በፊስካል አፈጻጸም የዘንድሮ አመት ክንውን ከተፈጠረው ሁኔታ አንጻር መልካም ቢሆንም በተለይ በገቢ መሰብሰብ ረገድ ይበልጥ መሠራት ይኖርበታል፡፡
የወጪ ንግድ አፈጻጸምና የውጭ ምንዛሪ
የወጪ ንግድ አፈጻጸምና አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ የወጪ ምርቶችን በመጠንና በዓይነት ለማሳደግ ርብርብ ቢካሄድም ከሸቀጦች የወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ አሁንም ዝቅተኛ ነው።ይሁን እንጂ በ10 ወራት ከአገልግሎት ወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ የ25 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ በመቻሉ አጠቃላይ ከሸቀጦችና አገልግሎቶች ወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 10 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ አድርጎታል። በተጨማሪም ከሌሎች የውጭ ምንዛሪ ገቢ ምንጮች ማለትም ከግል ሐዋላ፣ ከመንግሥታዊ ሐዋላ፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ ከውጭ ብድር እና ከውጭ ምንዛሪ ቁጠባ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማግኘት በተደረገው ከፍተኛ ጥረት በ10 ወራት ውስጥ 12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።ይህም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከ 20 መቶ ከፍ ያለ ነው።
በቀጣይ የውጭ ምንዛሪ የማፍራት አቅማችንን በማጠናከር የወጪ ንግዳችንን መዋቅራዊ ችግር በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ መፍታት የምንችልባቸውን ስልቶች መቀየስ፣ የአገልግሎትና የግል ሐዋላ ግኝታችንን ማሳደግና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የመሳብ ብቃታችንን ማጐልበት የትኩረት አቅጣጫዎቻችን ናቸው፡፡
የፋይናንስ ዘርፍ
የፋይናንስ ዘርፍ አፈጻጸምን በተመለከተ ባለፉት 10 የበጀት ዓመቱ ወራት ሁሉም ባንኮች ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ22 በመቶ አድጓል። በተመሳሳይ ወቅት ሁሉም ባንኮች ያሠራጩት አዲስ ብድር ከአምናው 10 ወራት አፈፃፀም በ35 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ ብድር ውስጥ የግል ዘርፍ (ማኅበራትን ጨምሮ) ድርሻ 65 በመቶ ሲሆን አጠቃላይ ለግል ዘርፍ የተሰጠው ብድር ከአምናው በተመሳሳይ ወቅት የተሰጠ ብድር በ54 በመቶ ከፍ ያለ ነው።በዚሁ ወቅት ለመንግሥት ዘርፍ የተሰጠው ብድር የ35 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን ይህ መጠን ባለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ለመንግሥት የልማት ተቋማት ተሰጥቶ ከነበረው በ10 በመቶ ያደገ ነው፡፡
በአጠቃላይ የባንኮች እንቅስቃሴ በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ ነው ማለት የሚቻል ሲሆን በተለይ ብድሩ በስፋት ወደ ግል ዘርፍ መሄዱ ዘርፉን ለማጠናከርና ለማበረታታት የተያዘውን አቅጣጫ የተከተለ መሆኑን ያሳያል።
የዋጋ ግሽበት
የዋጋ ሁኔታን በተመለከተ በ2011 የበጀት ዓመት የሀገራችንን የዋጋ ግሽበት ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ በሁሉም አቅጣጫ ታቅዶ ነበር። ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ 16 ነጥብ 8 በመቶ ደርሶ የነበረውን የዋጋ ግሽበት በመቆጣጠር በያዝነው የበጀት ዓመት ከዚህ ጣሪያ እንዳይዘልና ወደታቀደው ግብ ለማውረድ የተለዩ ጥረቶች ተደርገዋል። የዋጋ ግሽበት የዓመቱ አብዛኛውን ወራቶች ከ12 በመቶ በታች የነበረ ቢሆንም በግንቦት ወር ወደ 16 ነጥብ 2 በመቶ አሻቅቧል፡፡
የዋጋ ግሽበት በኢንቨስትመንት ላይ ከሚያሳድረው አሉታዊ ተፅፅኖ በተጨማሪ በዋናነት ድሆችንና አነስተኛ ቋሚ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚጐዳ መሆኑን በጥብቅ እንገነዘባለን።ስለዚህም የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠርና ለመቀነስ የተቀናጀ ጥረት ይደረጋል። እንደዚሁም በግንቦት ወር ያሻቀበውን የዋጋ ግሽበት ሁኔታ በዝርዝር አጥንቶ ርምጃ መውሰድ ተገቢ ስለሆነ ከፍተኛ የመንግሥት ውሳኔ ሰጪ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ቡድን ያሉበት ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ተደርጐ ሥራውን ጀምሯል።
የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር
ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወር እንቅስቃሴን በተመለከተ ወደ ግል በከፈልም ሆነ በሙሉ የሚተላለፉ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶችን ለታሰበው ዓላማ የማዘጋጀት ሥራ በሰፊው ተጀምሯል።የየዘርፉን ተቆጣጣሪ አካላት የማቋቋም፣ የየድርጅቶቹን ንብረት በአግባቡ ለይቶ የዋጋ ግምት እና በአንዳንዶቹ ላይ ሙሉ ሪፎርም በማድረግ ለተሻለ ዋጋ የማዘጋጀት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሠረት ከዝግጅት ደረጃቸው በመነሣት በሙሉና በከፊል ወደ ግል የማዛወሩ ቅደም ተከተል እንዲቀመጥላቸው ተደርጓል።በመጀመሪያ ረድፍ ላይ ለፕራይቬታይዜሽን ዝግጁ ይሆናሉ ተብለው የተለዩት ቴሌኮሙኒኬሽንና የስኳር ልማት ፋብሪካዎች ናቸው።በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ የኃይል ማመንጫዎች፣ የባቡር ኮርፖሬሽንና የሎጅስቲክስ ተቋማት ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጨረሻ ረድፍ የሚታዩ ናቸው፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚው የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸም በአጠቃላይ ሲታይ፣ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አስቀምጠን ከነበረው ግብ አንጻር ተስፋ ሰጪ ውጤት የተገኘበት ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል ነው።የፋይናንስ ዘርፉን ሆነ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ወደ ባሰ ቀውስ እንዳይገባ የማድረግ ትልማችን ተሳክቷል።በተጨማሪም ኢኮኖሚው ተረጋግቶና አገግሞ ወደ ዕድገት የመመለስ ሁኔታ ላይ ስለሆነ የሚታይበትን የምርታማነት ችግርና መዋቅራዊ ስብራት በአግባቡ በመጠገን ወደ ላቀ ዕድገት ልናሸጋግረው ይገባል፡፡
ቀጣይ ትኩረት
ኢኮኖሚን በተመለከተ፡- በተከታታይ የተመዘገበውን ዕድገት በቀደመው የልማት ፋይናንስ ሞዴል ማስቀጠል ቢፈለግም አይቻልም።ስለዚህም አማራጭ የፋይናንስ አቅርቦት ሁሉንም የልማት ኃይሎች በማሳተፍ መንደፍ ያስፈልጋል፡ ከፈጣኑ ዕድገታችን ጋር ተያይዞ የተገኘው የእድገት ጥራት መፈጠር ከነበረበት የሥራ ዕድል፣ የካፒታል ክምችት፣ የመዋቅር ለውጥና የምርታማነት ዕድገት አንጻር በአግባቡ የመፈተሽና በተገኘው ውጤት መሠረት የማስተካከያ ርምጃ የመውሰድ ሥራ ይሠራል። በቀጣይ ዓመታት ልማቱን ለማስቀጠልና የተሻለ ውጤት ለማግኘት ከሁሉ አስቀድሞ ኢኮኖሚው አጋጥሞት የቆየውን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት በተሟላ መልኩ ማረቅ ያስፈልጋል።ይህ ካልሆነ ከቁጥጥር የወጣ የዋጋ ግሽበት፣ የዕድገት መቀጨጭ እና ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ቀውሶችን ሊያስከትል ይችላል።
የኢኮኖሚያችን ምርታማነት በእጅጉ ዝቅተኛ ስለሆነ በሁሉም ዘርፍ ምርትና ምርታማነት የሚያድግበትና በኢኮኖሚው የሚስተዋለውን የአቅርቦት ማነቆ የምንፈታበት እንቅስቃሴ በሰፊው እንጀምራለን።የግል ዘርፉን በሁሉም አቅጣጫ ደግፎ በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተዋናይ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል።ይህን ለማድረግ በፌዴራልና በክልሎች ደረጃ ለኢንቨስትመንት የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ይኖርብናል። በየአካባቢው ሰላምን በማረጋገጥ ሁሉም ወደ ልማት ሥራ እንዲገባ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል። ሰላም ጠፍቶ ዜጎች ሲፈናቀሱ ተፈናቃዮቹ የሚበሉትና የሚጠጡት ማጣታቸው ብቻ ሳይሆን እነሱ በሰላሙ ጊዜ ያመርቱት የነበረው ምርት ወይ አይመረትም ከተመረተም በሰላም እጦት ወደ ገበያ አይቀርብም።ይህም የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል። ስለዚህ ሰላማችንን ማረጋገጥ ለልማታችን ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡
ሌላው የኢኮኖሚያችን ከባድ ፈተና ሥራ አጥነት ነው። ልማታችን ፋይዳ አለው የሚባለው ለዜጎች ሕይወት መቀየር አስተዋጽዖ ሲያደርግ ነው። በመሆኑም በሚቀጥሉት ወቅቶች የልማትና ዕድገት መመዘኛችን ልማቱ ምን ያህል ሥራ ፈጠረ የሚለውን መሠረት ያደረገ መሆን ይኖርበታል።ግብርናን ለማዘመን የተጀመሩ ተግባራትን አጠናከሮ መቀጠል እንደ ዋነኛ ትኩረት አቅጣጫ ተይዞ ይሰራበታል።በተለይም የቆላ ግብርናን በማስፋፋት እንዲሁም የምርት መተካት ተግባራት ላይ ማትኮር የቀጣይ አቅጣጫ ሆኖ ይቀጥላል።
ቱሪዝምን በተመለከተ፦ የቱሪዝም መስሕብን ለመጨመር ሰፋፊ ሥራዎች ይከናወናሉ።ያሉንን የቱሪስት መስሕቦች ከመጠገንና መዳረሻዎቹን ለቱሪስቶች ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ፍሬ ያፈራል። ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን ለጉብኝት በሚሆን መልኩ አመቻችቶ ለጎብኝዎች ክፍት የማድረጉ ሥራ በመስከረም 2012 ላይ የሚጠናቀቅ ሲሆን በቀጣይም የአዲስ አበባን ተፋሰሶች የማልማት ሥራው ይጀምራል። ይህም ቱሪስት ከመሳብም ባሻገር ከተማዋን ለነዋሪዎቿና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ምቹ እንድትሆን የማስቻል አቅሙ ከፍተኛ ነው።
አካባቢ ጥበቃን በተመለከተ፦ ዝናብ ላይ የተንጠለጠለ ግብርና ይዘን አካባቢያችንን ማልማትና መጠበቅ ነው።እየደጋገመ የሚመታንን ድርቅና ረሐብ ከማስወገድ አንጻር ነው የምናየው።ለዚህም ነው በዘንድሮው ክረምት ከወትሮው በተለየ መልኩ አራት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ይህንን እውን ለማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያውያንን ርብርብ ይጠይቃል፡፡
ከዚህ የአረንጓዴ እቅድ ጋር ተያይዞ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር የምንተክልበት የአረንጓዴ አሻራ ቀን የፊታችን ሐምሌ 22 ስለሚከናወን ለተከበረው ለዚህ ምክር ቤት አባላትና ለኢትዮጵያውያን በሙሉ የሚጠበቅብንን እንድናደርግ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
እንደ ወትሮው ተከሎ ዘወር በማለት ባለቤት አልባ ችግኞችን መፍጠር ሳይሆን ከብካቤው ባለቤት ኖሮት ዘላቂ በሆነ መልኩ እንዲሠራ ሰፊ የቅስቀሳ፣ የማደራጀትና ሁሉንም ባለቤት የማድረግ ሥራዎች ይከናወናሉ።ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ሌላው የሚከናወነው ዐቢይ ተግባር ከተሞችን የማስዋብ፤ የማጽዳትና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ በየወሩ የተጀመረው መጠነ ሰፊ ከተሞችን የማጽዳት ዘመቻን በማጠናከር ከባቢያችንን ንፁህ፤ አስተሳሰባችንን ቀና፤ ኢትዮጵያችንን የበልፀገችና ለዜጎቿ ምቹ ለማድረግ በተደመረ ሐሳብና ተግባር መረባረብ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2011
በጋዜጣው ሪፖርተሮች