አዲስ አበባ፡- የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል አብዛኛው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች የሚከናወን እንደመሆኑ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ተሳትፈው ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡
አቶ ማትያስ አሰፋ የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር እንደ ሀገር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያለበትን ደረጃ አብራርተዋል፡፡ በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በበጎ ፈቃደኞች ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ማዳን ተችሏል፡፡ ባለፈው የክረምት ወራትም በሁሉም ክልሎች 13.5 ሚሊዮን ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው 4.6 ቢሊዮን ብር ለመንግስት ማዳን ችለዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም፤ በማህበራዊ ዘርፍ የማህበረሰብ ትስስር በመፍጠር፤ የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት፤ በአደጋ ጊዜና ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ያሉ ሰዎችን በመርዳት በመንከባከብ፤ ደም በመለገስ፤ የአረጋውያንን ቤት በማደስ ወዘተ… ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህና መሰል ማህበራዊ ችግሮች በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተቀርፈዋል፡፡ በተለይም በከተማው የሚታዩት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የትራፊክ አገልግሎቱን በማስተናበር ብዙ አደጋ መቀነስ ችለዋል፡፡
አብዛኛው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቶች የሚሰራ እንደመሆኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች በብዛት የሚገኙት በክረምት ወቅት ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ ወጣቶቹ ወቅትን ጠብቀው ብቻ እንዳይንቀሳቀሱና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል እንዲያደርጉት በመንግስት በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ ከነዚሀም መካከል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በህግ እንዲገዛ ማድረግ የሚያስችል ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ፖሊሲ ሲጸድቅም በጎ ፈቃደኞች በተለያዩ መስኮች ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሰፊው ተደራሽ ከመሆኑም ባሻገር ከዘመቻ ስራ ወጥቶ ባህል እንዲሆን ያግዛልም ብለዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃደኞች ቀን በዓለም ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የተከበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ተከብሮ ውላል፡፡ ዋና ዓላማው በጎ ፈቃደኞች በዓለም አቀፍ፤ በአህጉርና በአገር አቀፍ ደረጃ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና የመስጠትና የማበረታታት እንዲሁም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውኑ ባጋጠማቸው ችግሮች ዙሪያ መፍትሄ ለመስጠት የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 3/2011
ፍሬህይወት አወቀ