በአዲስ አበባ፡– የተሠሩት የቱሪስት መዳረሻዎችና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ቀይረውታል ሲሉ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት መጥተው ከተማዋን የጎበኙ ሳይንቲስቶች ገለጹ፡፡
ሉሲ (ድንቅነሽ) የተገኘችበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ ለመሳተፍ ከተለያየ ዓለም የመጡ 200 በላይ ሳይንቲስቶች በአዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻዎችንና ፕሮጀክቶችን ትናንት ጎብኝተዋል።
ከአሜሪካ አሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የመጡት ብሬንት አድሪያን ለኢፕድ እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ ከተማን የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችሉ የመሠረተ ልማቶች ተሠርተዋል፡፡
በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም፣ በብሔራዊ ሙዚየም እና በአንድነት ፓርክ ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለጹት ብሬንት፤ በከተማዋ የተሠሩ የተለያዩ መዳረሻዎች ለጎብኚዎች ምቹ በሆነ መልኩ ተሠርተዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ቅኝ ግዛትን አንቀበልም በማለት በዓድዋ ድል ማድረጋቸው ለአፍሪካውያን ነጻነት መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ የከፈለችው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ እየተሠሩ የሚገኙት የኮሪደር ልማትና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎች የከተማዋን ገጽታ ቀይረውታል ያሉት ብሬንት፤ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም፣ አንድነት ፓርክ፣ የእግረኛ፣ የሳይክልና የተሽከርካሪዎች መንገዶችን ጨምሮ የሰዎች መዝናኛ ቦታዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከታንዛኒያ ዱክ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ቻርለስ ሙሲባ በበኩላቸው፤ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በአህጉሪቱ ከሚገኙ ምርጥ ሙዚየሞች አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ነጻነት የነበራት አበርክቶ እጅግ ትልቅ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ቻርለስ፤ በተለይም ለኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ብሎም ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነት የሀገሪቱ አበርክቶ ትልቅ ነበር ብለዋል፡፡
አዲስ አበባን ከስድስት ዓመት በፊት እንደሚያውቋትና በአሁኑ ጊዜ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከተማዋ እንደለወጡት በመግለጽ፤ በተለይም የከተማዋ ፈጣን የእድገት መጠን፣ የመንገድ፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች በመገንባታቸው በአውሮፓ የምናውቃቸውን ከተሞች መምሰል ጀምራለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ ወጣቶች ወደ አውሮፓ መሄድ የለባቸውም፡፡ ሁሉም ነገር በሀገራቸው እየተሠራ ነው ያሉት ዶክተር ቻርለስ፤ ኢትዮጵያ አፍሪካ መሥራት እንደምትችል በግልጽ ማሳየቷንም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው ያሉት ደግሞ ከካናዳ ዊኒፔግ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ሚርጃና ሮክሳንዲች ናቸው፡፡
አዲስ አበባ አሁን ባለችበት ደረጃ ውብ ትሆናለች ብዬ አስቤ አላውቅም ያሉት ሚርጃና፤ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም፣ ብሔራዊ ሙዚየም፣ አንድነት ፓርክ እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች አድናቆትን ፈጥረውብኛል ብለዋል፡፡
ሉሲ የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር በመምጣታቸው የተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎችን ለመጎብኘት እድል እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደተናገሩት፤ ሉሲ የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ያካሄዱ 230 በላይ ሳይንቲስቶች መምጣት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡
ከመርሃግብሩ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ 13 ድንቅ ግኝቶችን፣ አንድነት ፓርክ፣ ዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እና የኮሪደር ልማቶችን ተመልክተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የኮሪደር ልማቱ መስፋፋትን ተከትሎ አዲስ አበባ እየተቀየረች ለቱሪስት ምቹ እየሆነች ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ጸጋዎችን በመለየት መጠቀምና ማስተዋወቅ የጀመረችበት አዲስ ምዕራፍ ላይ መሆኑዋን ጠቅሰው፤ በጉብኝቱ የተሳተፉ ሳይንቲስቶች የኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች ማስተዋወቅ የሚችሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26 /2016 ዓ.ም