ከሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ተገኘ

አዲስ አበባ፡– ባለፉት ሶስት ወራት ከሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የሽያጭና ገቢዎች አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ሚኒሊክ ጌታሁን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ተቋሙ የሚያመርተውን ሀይል ለሀገር ውስጥ ደንበኞች እንዲሁም ለተለያዩ ጎረቤት ሀገራት በሽያጭ ያቀርባል፡፡

በሀገር ውስጥ ሽያጭ ከሚያቀርብላቸው ደንበኞቹ መካከል ዋነኛው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲሆን ባለፉት ሶስት ወራት 9 ሺ 128 ነጥብ 08 ሜጋ ዋት ሀይል በማስተላለፍ ከሶስት ቢሊዮን 297 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጨማሪ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ለኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ሀይል የሚያቀርብ ሲሆን፤ ከእነዚህ ተቋማት ሁለት ቢሊዮን ሚጠጋ ብር ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡

በጥቅሉ ተቋሙ ከሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ሽያጭ አምስት ቢሊዮን 412 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ አምስት ቢሊዮን 226 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የእቅዱን 96 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ከብሄራዊ ባንክ በሀገር ውስጥ ዶላር የማንቀሳቀስ ፍቃድ ያለው ተቋም መሆኑን የገለጹት አቶ ሚኒሊክ፤ አንዳንድ ተቋማትን በዶላር እንደሚያስከፍል ተናግረዋል፡፡ በዚህም በሶስት ወሩ በሀገር ውስጥ በዳታ ማይኒንግ ላይ ለተሰማሩ ተቋማት ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ለጅቡቲ ፣ለሱዳን እንዲሁም ለኬንያ የኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ የምታቀርብ ሲሆን በዘንድሮው ሩብ አመትም ለጅቡቲ 169 ሺ 710 ነጥብ 91 ሜጋ ዋት ሀይል በማስተላለፍ 10 ሚሊዮን 379 ዶላር ፣ለሱዳን 13ሺ 185 ነጥብ 50 ሜጋ ዋት ሀይል በማስተላለፍ 659 ሺ 275 ዶላር ፣ለኬንያ 314 ሺ 931 ነጥብ 38 ሜጋ ዋት ሀይል በማስተላለፍ ከ20 ሚሊዮን 470 ሺ ዶላር የተገኘ ሲሆን፤ በጥቅሉ ተቋሙ ለጎረቤት ሀገራት በሸጠው ሀይል ከ31 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡

አቶ ሚኒሊክ ለሱዳን የቀረበው ሀይል ለማቅረብ ከታቀደው 15 በመቶው ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ሱዳን ካለባት የጸጥታ ችግር አንጻር በአግባቡ ክፍያ ባለመፈፀሟ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You