ከተማዋ ያላትን ፀጋ በመጠቀም ጥራት ያለው የምግብ ተዋፅኦ ለማምረት እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡አዲስ አበባ ያላትን ፀጋ በመጠቀም ጥራት ያለው የምግብ ተዋፅኦ በማምረት የኑሮ ውድነቱን ለማቅለል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የአርሶአደር ከተማ ግብርና ልማት ኮምሽን ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ኪዳኔማርያም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ በዕፅዋት እና በእንስሳ ዘርፍ ከፍተኛ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በአትክልት ልማት ዘርፍ ከአምስት መቶ ሺ በላይ ተጠቃሚዎች ራሳቸውን ችለው ገበያውን የማረጋጋት ስራ እየሰሩ ነው፡፡

በተያዘው ዓመትም በሁሉም ክፍለ ከተሞች ጥራት ያለው ምርት ለማምረት በዕቅድ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ፤ በዋናነት የከተማ ነዋሪ ባለችው መሬት ላይ የራሱን ፍጆታ ከገበያ ከመግዛት ይልቅ በራሱ አምርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ ከሰባት ሺ በላይ ሄክታር መሬት በአትክልት በመሸፈን ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ይህም የገበያ መረጋጋት ላይ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡ ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ደግሞ ከአምስት መቶ ሺ በላይ በማህበር እና በግል በግብርናው ዘርፍ እየተሳተፉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተያዘው ዓመት ነባሩን ስራ በማስቀጠል ምርትን ለማሳደግ መታቀዱን ጠቅሰው፤ጥራት ያለው እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ለገበያ እንዲያመርት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የከተማ ግብርናው እንዳይጎለብት ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት ዋነኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የህብረተሰቡ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም ከባለሙያ ጋር ባለመመጣጠኑ ዘርፉ ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የግብአት አቅርቦት የዘር፣ የተለያዩ እርሻ መሳሪያዎች ዋጋ መጨመር የከተማ ግብርናው አስቸጋሪ እንዲሆን ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኪሎ የአትክልት ዘር (ቆስጣ፣ቲማቲም እና ሰላጣ) በፊት ከአምስት መቶ እስከ አንድ ሺ ብር ይሸጥ የነበረ ቢሆንም አሁን እስከ ሶስት ሺ ብር መድረሱ እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በአዲስ መልክ እየተሰራ ያለው የከተማ ግብርና ቅንጅት የሚያስፈልገው መሆኑን ጠቅሰው፤ ቴክኖሎጂ አለመጠቀም እና በቂ ባለሙያ ባለመኖሩ ለዘርፉ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከተማዋ ያላትን ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም በተለይ የሀገር ውስጥ ማዳበሪያ በማምረት ውጤታማ ስራ ለመስራት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You