በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ 300 ሺህ ቶን የአማቂ ጋዝ ልቀት ለመቀነስ ታቅዷል

አዲስ አበባ፡– በመዲናዋ በተያዘው በጀት ዓመት 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአማቂ ጋዝ ልቀት ለመቀነስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአማቂ ጋዝ ልኬት፣ ቅነሳና አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ሰለሞን መለሰ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤በመዲናዋ በበጀት ዓመቱ 300 ሺህ ቶን የአማቂ ጋዝ ልቀት ለመቀነስ ታቅዷል።

በባለፈው በጀት ዓመት 250 ሺህ ቶን ያህል ለመቀነስ ታቅዶ 255 ሺህ ቶን መቀነስ ተችሏል ያሉ ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመትም 300 ሺህ ቶን የአማቂ ጋዝ ልቀት ለመቀነስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ በ2012 በተደረገ የአማቂ ጋዝ ልኬት ሰባት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የነበረው በ2014/15 ዓ.ም ሰባት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሆኗል፡ ፡በየዓመቱ አማቂ ጋዞች ከሚመነጭባቸው ዘርፎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት አሁንም ከአሮጌ መኪናዎች የሚወጣው ነው።

አቶ ሰለሞን አክለውም፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያለው ልዩነት ከአምስት መቶ ሺህ በላይ መሆኑ በከተማው የአማቂ ጋዝ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱንና ለጤና አስጊ ደረጃ የሚያደርስ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

ከመስፈርት በላይ የአየር ብክለት የሚያስከትሉ አሮጌ መኪናዎች ለመቆጣጠር የወጣው መመሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ የኮንስትራክሽን ብናኝ በአግባቡ ማስወገድ የሚቻልበት መመሪያም እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ወደ ረጲ የሚወሰደው ደረቅ ቆሻሻ በመቀነስ በኮምፖስ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ በዘርፉ የተሰማሩ የተለያዩ ማህበራት እንዲጠናከሩ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አቶ ሰለሞን፤ ባለስልጣኑ ችግሩን ከመቀነስ  ጎን ለጎን የኤሌክትሪክ መኪኖች እንዲበራከቱ እንዲሁም ተጠቃሚው በብዛት የከተማ አውቶቡሶች እንዲጠቀሙም ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በሀገሪቱም የተለያዩ የጤና ችግሮች ከመድረሳቸው በፊት የግንዛቤ ስራ የመስራትና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ በሚያስፈልግበት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል።

እስከ እአአ 2050 ድረስ ከምንም አይነት አየር ብክለት የጸዳች ከተማ ለመፍጠር ውጥን ተይዟል ያሉት አቶ ሰለሞን፤ አሁን ላይ ባለው ሂደትም የኤሌክትሪክ መኪናዎች መግባት፣የመንገዶች መስፋት እና የከተማ አውቶቡሶች መበራከት ከጀመሩ ወዲህም የተወሰነ ለውጥ እንዳለ የሚጠቁሙ ነገሮች እንዳሉ አስረድተዋል።

በከተማው ያለው የአማቂ ጋዝ መጠን ምን ደረጃ እንደደረሰ በየሁለት ዓመቱ የመለካት ስራ እንደሚሰራና የ2015/16 ዓ.ም በተያዘው በጀት ዓመት ጥናት እንደሚደረግ አንስተዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You