ገበያ መሩ የውጭ ምንዛሪ ጅማሮ

በሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የውጭ ምንዛሪው በገበያ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በሚል ትልቅ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ መደረጉ ይታወሳል። ሶስት ወራትን ለማስቆጠር ሶስት ቀን የቀረው ይህ ‹‹ፍሎቲንግ›› ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ርምጃ ምን ውጤት አስገኘ? በርግጥስ ብዙ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት፤ ጥቁር ገበያን ለማስቀረት አስችሏል? ጥቅም እና ጉዳቱስ ምን ይመስላል? ብለን ላቀረብናቸው ጥያቄዎች የዘርፉ ምሁራን የሚሉት አላቸው።

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አሶሴሽን በተመራማሪነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ የውጭ ምንዛሪ ገበያ መር ይደረግ ሲባል መነሻው ገበያው ይወስነው ከሚል ነው። ይህ ማለት አንዳንድ በሀገራችን ላይ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ገንዘቦች የሽያጭ ሁኔታቸው ባላቸው የአቅርቦት መጠን ላይ ይወሰን ለማለት ነው። እዚህ ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እጅግ ውስን ይሆናል። የውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ነገሮችን ፈር ከማስያዝ የዘለለ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አይኖርም ማለት ነው።

የውጭ ምንዛሪ ተመኑን የሚወስነው ገበያው ነው ሲባል፤ ምን ለማለት ነው ጥቅሙስ ምን ያህል ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፤ ጥቅሙን ለማብራራት በቅድሚያ የሀገሪቱን የገበያ ሁኔታ ማወቅ ወሳኝነት አለው። በተለይ ከአምራች ኢንደስትሪው ጋር ተያይዞ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ብዙ ሆነው የውጭ ምንዛሪ ማስገባት ከቻሉ ሀገር ተጠቃሚ ትሆናለች። ምክንያቱም ዕቃዎችም ሆኑ አገልግሎቶች የተሻለ ገቢ የሚያስገኙ ይሆናል። እንደ ኢትዮጵያ አይነት ሀገሮች ላይ ግን ገበያ መር ማድረጉ የተወሰነ ጫና እንዳለው መካድ አይቻልም።

የገቢ ንግዱ ከውጭ ንግዱ በሶስት ነጥብ አምስት እጥፍ የበለጠ ሆኖ፤ ገበያ መር የምንዛሪ ሥርዓትን መጠቀም ምንዛሪው ገበያ መር መሆኑን ተከትሎ ዕቃዎች ውድ እንዲሆኑ ያስገድዳል። አሁን ባለው የግሽበት መጠን ላይ እንደገና የውጭ ምንዛሪን ገበያ መር ማድረጉ ሌላ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። ስለዚህ ሊመጣ የሚችለውን ጫና ከመቀነስ አኳያ የመንግሥት ሚና ከፍተኛ ሊሆን ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ያመለክታሉ።

ገበያ መር መሆኑ ሀገርም ሆነ ሕዝብን በርግጥ ምን ያህል እየጠቀመ ነው ? ጉዳቱ አያመዝንም ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) በሰጡት መልስም፤ ከታወጀ አልቆየም። ገና የመዘጋጃ ጊዜ ላይ በመሆኑ አሁን ጥቅሙንም ሆነ ጉዳቱን ለማረጋገጥ ጊዜው አይደለም። በተጨማሪ በደፈናው ጠቅሟል ወይም ጎድቷል ከማለት ይልቅ ምላሽ ለመስጠት ጥናት ያስፈልጋል ብለዋል። አያይዘውም ነገር ግን አሁንም ቢሆን ገበያ መር ቢሆንም መንግሥት የተሻለ ሚና መጫወት አለበት ለዚህም ከመጠባበቂያው ላይ ቀንሶ የውጭ ምንዛሪውን ወደ ገበያው ማውጣት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።

ከአዋጁ በኋላ ባንኮች በተሻለ ዋጋ ለመግዛት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ አንድ ኢኮኖሚስት በእርሳቸው በኩልም ጥያቄ መኖሩን በመጠቆም ባንኮች ውድድራቸው በመግዛት ላይ እንጂ በማቅረብም ሆነ በመሸጥ ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታይም። ይህ ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ስላለው መንግሥት በዚህ ጉዳይ ዙሪያም አተኩሮ መሥራት እንዳለበት አመላክተዋል።

ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር)፤ ጨምረውም ባንኮች የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እያገኙ እንደሆነ እየተናገሩ ነው። ነገር ግን በበቂ መጠን ካላገኙ እጥረቱ እስካልተቀረፈ ድረስ ተፅዕኖ መኖሩ አይቀርም። ተፅዕኖውን ለማቃለል መንግሥት በድጎማ ወይም በተለያዩ መንገዶች እጥረቱን መቀነስ አለበት ሲሉ መክረዋል።

የውጭ ምንዛሪ የጥቁር ገበያ አሁንም እየታየ መሆኑን እና ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እንዲሁም ጉዳዩ የሚቀርበትን ሁኔታ በተመለከተ ለቀረበላቸውም ጥያቄ፤ ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፤ ጥቁር ገበያ በተዘዋዋሪ ጉዳት ይኖረው ይሆናል። ነገር ግን መንግሥት በቢሮክራሲ ጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር ጥረት ከሚያደርግ ይልቅ በሌላ በኩል ሌሎች ሥራዎችን ቢሠራ ይሻላል ብለዋል።

ዋናው ጉዳይ የውጭ ምንዛሪ ገበያ መር ተብሎ ከታወጀ ወዲህ በጥቁር ገበያው እና በባንክ ምንዛሪው መካከል ያለው ልዩነት ሲሆን ይህም በጣም ተቀራርቧል። ባለፉት ሁለት እና ሶስት ቀናት ውስጥ ጥቁር ገበያው ትንሽ በለጥ ያለ ቢሆንም፤ አሁንም እንደ በፊቱ ከመራራቅ ይልቅ እጅግ የተቀራረበ ነው። ይህ ደግሞ ጊዜያዊ የፍላጎት ጭማሪ በመሆኑ፤ የጥቁር ገበያው በጣም እየናረ ነው ለማለት የሚስደፍር አለመሆኑንም አመልክተዋል።

በየትኛውም መስክ የገበያ ውጣ ውረድ ይኖራል። ፍላጎት ሲጨምር ዋጋ ይጨምራል፤ ፍላጎት ሲቀንስ ደግሞ ዋጋ ይቀንሳል። በማለት የተናገሩት ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ቢያንስ ለተወሰኑ ወራቶች ከታየ በኋላ የጥቁር ገበያው መልክ ይይዛል ብለዋል። ዋናው መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ አቅርቦት እና ፍላጎት እስካልተጣጣመ ድረስ ጥቁር ገበያው መኖሩ አይቀርም። ነገር ግን በሁለቱ መካከል ያለው ክፍተት እየጠበበ መምጣቱ የሚካድ አይደለም። ይሄ ደግሞ ዋነኛ የጥቁር ገበያውን የመከላከያ መንገድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሲዳማ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ሐጢያ በበኩላቸው፤ አዋጁን ተከትሎ መንግሥት የውጭ ምንዛሪን ፈሰስ አድርጓል። የውጭ ምንዛሪው ገበያ መር ሲሆን፤ የተለያዩ ባንኮች እንዲገዙ ለማገዝ የተለቀቀ ገንዘብ ባንኮችን ደግፏል። በተጨማሪ ከውጭ ሀገር የሚላከውም ገንዘብ ስለጨመረ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ እያገኙ ነው። ያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ደግሞ እየሸጡ ነው። በባንክ በኩል የውጭ ምንዛሪውን ይዞ መቆየት አክሳሪ ነው። ምክንያቱም ባንኩ ራሱ ትርፍ የሚያገኘው ደንበኞች ባለው ገንዘብ ሲጠቀሙ በመሆኑ ነው።

የሀገር ውስጥ ገንዘብም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። በቢሊየን ቁጥር የገባ ብር መንቀሳቀስ አለበት። አዲሱ ፖሊሲ ብዙ የውጭ ምንዛሪ እንዲገባ አድርጓል። በተመሳሳይ መልኩ ለደንበኞች የውጭ ምንዛሬ ለማቅረብም ጥሩ ዕድል ፈጥሯል። ያሉት አቶ ታደሰ በእነርሱ በኩል ያገኙትን የውጭ ምንዛሪ እየሰጡ መሆናቸውን እና የሚደብቁበት ሁኔታ አለመኖሩንም ይናገራሉ።

ኢኮኖሚስቱ ብርሃኑ ደኑ ( ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ገበያ መር በሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ ብዙ ነገሮች መንግሥት ከላይ ሆኖ ወደ ታች የሚያስተላልፈው ሳይሆን በፍላጎት እና በአቅርቦት ላይ ተመስርቶ የሚወሰን ነው። ዕቃውም ሆነ አገልግሎቱ የሚሸጠው እና የሚገዛው በዚሁ በአቅርቦት እና በፍላጎት ላይ ተመስርቶ ነው። የገንዘብ ሽያጭም ተመሳሳይ ነው። ይህ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ እውነት ነው። ነገር ግን ሲተገበር የኢኮኖሚዎቹ አቋም በምን ዓይነት የልማት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ታሳቢ ማድረግ ደግሞ ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ በግሎባላይዜሽን ዘመን አንድ ሀገር ለብቻዋ ተነጥላ መኖር አትችልም። የዓለም ሀገሮች በአብዛኛው በንግድ፣ በኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንትም ሆነ በፖለቲካ ፣ በማህበራዊ ሁኔታም እየተገናኙ የሚኖሩ ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በአሁኑ ጊዜ ከዓለም ሁኔታ አንፃር የውጭ ምንዛሪ መንግሥት እንደ በፊቱ በብሔራዊ ባንክ በየጊዜው የሚወስነው የምንዛሪ ተመን ከገበያው ጋር መሔድ አልቻለም። በተጨማሪ በቂ የውጭ ገንዘብ አቅርቦት ማግኘት ስላልተቻለ የጥቁር ገበያው ዋጋ የመንግሥት ባንኮች ከሚመዘግቡት በጣም በከፍተኛ ዋጋ የጨመረ ነበር። አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር ስላልተመጣጠነ ሰው ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ሄዶ ከፍተኛ የምንዛሪ ተመን በመስጠት ሲገዛ ቆይቷል ይላሉ።

እንደ ብርሃኑ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ስለዚህ በመንግሥት ትዕዛዝ በብሔራዊ ባንክ ተመን መሠረት በየጊዜው ለባንኮች እየተነገረ የሚሰጠው ዝቅተኛ የባንኮች ተመን ዋጋ ቢኖርም፤ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልግ ሰው ከዛ በላይ ለመክፈል ፍላጎት እንዳለው አመልካች ነገሮች ነበሩ። በግልፅ በአደባባይ እንደታወቀው፤ መንግሥት ሃምሳ ብር አካባቢ እየመነዘረ ጥቁር ገበያው መቶ ደርሶ ነበር። ያ ደግሞ በዛ ዋጋ ለመግዛት የሚሻ ፍላጎት አለ ማለት ነው። ስለዚህ በርዳታም ሆነ በዕዳ ሽግሽግ ከውጭ ካሉ የልማት ድርጅቶች አጋዥነት የአቅርቦቱን መጠን ከፍ ለማድረግ ተሞከሯል።

በተጨማሪ በተለያየ ሁኔታ በሙስናም ቢሆን ጥቁር ገበያም ባይኬድ አንድ ዓይነት የምንዛሪ ተመን እንዲሆን የገበያው ሁኔታ ለቀቅ ይደረግ፤ ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው ጣልቃ እየገባ ይህን አድርግ ብሎ ከሚያዝ በየጊዜው የሚቀያየር ሳይሆን በገበያው ላይ ለማንም በማያደላ ተወዳዳሪነት ባለው ሁኔታ ምንዛሪው ይዳኝ ተብሎ ተወሰነ። ስለዚህ ካለው ከጥቁር ገበያ ጋር የሚስተካከልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተደረገ። አቅርቦቱ እየበዛ ሲሄድ ሰዎች በሚፈልጉት መጠንና ዋጋ በባንክ ማግኘት ከተቻሉ ወደ ጥቁር ገበያ አይኑን የሚያማትር አይኖርም በሚል ነው ይላሉ።

ይሄ መልካም ቢሆንም ከባንኮች ጋር ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ካሉ አሁንም ገበያውን ይረብሻሉ። ይህ የታወቀ ነው። ሕገ ወጥ ንግድ እና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማካሔድ የሚፈልጉ ካሉ፤ አሁንም መረበሻቸው አይቀርም። ባንክ የሚሔዱ ከሆነ በሕጋዊ መንገድ መሆን አለበት። ትክክለኛ እና አስተማማኝ ማስረጃዎችን በማቅረብ ማስፈቀድ ይገባል። በብድር እና በርዳታ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ እንደፈለጉት ከሕግ ውጭ ማከፋፈል አይችሉም። ይህም ሆኖ ህጋዊ ሰነድ እና እውቅና የሌላቸው ይህንን ያጡ ሰዎች ወደ ጥቁር ገበያ መሄዳቸው አይቀርም።

ጥቁር ገበያውን ደግሞ በቀላሉ ዝም ብሎ ማሰር አይቻልም። አሁን አማራጭ ተወስዷል። አማራጩን የሚጠቀሙ አሁንም ቢሆን ከጥቁር ገበያው በተሻለ ሁኔታ በጣም ሕጉን በጠበቀ እና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ያገኛሉ። ምክንያቱም አሁን በቀረበው ሪፖርት ባንኮች ባለፉት ወራት ከ282 ሚሊየን ዶላር በላይ ለተጠቃሚዎች አቅርበው፤ ከዚህ ውስጥ ግን እስከ አሁን ድረስ የተወሰደው 28 በመቶ ብቻ መሆኑ ይፋ ተደርጓል። ከባንኮች የመውሰድ ፍላጎት ለምን ቀነሰ ? የሚለው ሲታይ ድሮ በሕጋዊ መንገድም ሄደው ስለሚቆይባቸው እና ስለሚንገላቱ ስለሚያጡ ከጥቁር ገበያ ይገዙ ነበር። አሁንም ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተመዝግበው የንግድ ፍቃድ ያላቸው ገንዘቡን እየተጠቀሙ መሆኑን ያስረዳሉ።

እንደ ብርሃኑ (ዶ/ር) ገለፃ፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በተለያየ ሁኔታ ለተለያየ እንቅስቃሴ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የሚንቀሳቀሱት በጥቁር ገበያው ነው ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ሁሉ በመሆኑ አንዳንድ ነገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ላይስተካከሉ ይችላሉ። የትኛውም ለውጥ ጊዜ ይወስዳል። ጊዜ ይፈልጋል። ዛሬ የተደረጉ ማሻሻያዎች ቢያንስ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ውጤታቸው ላይታይ ይችላል። ስለዚህ ጥቁር ገበያው የቀጠለው በሕገወጦች ምክንያት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ያ እየተስተካከለ ሲሔድ፤ ሕገ ወጥ አካሔድን የሚከተሉ ሰዎች በሩ እየተዘጋባቸው ሲሔድ፤ ፍላጎታቸው ይቀንሳል። በዚህ ጊዜ ሕጋዊው የባንክ የገንዘብ ልውውጥ መንገድ ፈር እየያዘ ይሄዳል ብለዋል። በሌላ በኩል አንዳንድ የውጭ ምንዛሪው ገበያ መር እንዳይሆን የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም ይኖራሉ። ይህ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ሀገር ሊሆን የሚችል መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ኢኮኖሚስቶቹ ገለፃ፤ ሳይንሱ ሲታይ የውጭ ምንዛሪ ተመኑን ገበያ መር ማድረጉ ጠቃሚ እና ተገቢ ነው። ነገር ግን ውጤቱን ወዲያውኑ ለማየት መጓጓት ትክክል አይደለም። በሂደት ለውጥ መገኘቱ አይቀርም። ሂደቱ ፈር እየያዘ ሲቀጥል የጥቁር ገበያ የሚቆምበት ሁኔታ እንደሚኖር አያጠራጥርም።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You