ባለነገዋ ማዕከል ተስፋን የሰነቀው የወጣቷ ሕይወት

አንድ ልጅ በሥነ ልቦናም ሆነ በአካል ጠንካራ ሆኖ እንዲያድግ እና ለስኬት እንዲደርስ የተረጋጋ ቤተሰብ አይተኬ ሚና አለው። የዛሬዋ ባለታሪካችንም በተረጋጋ ቤተሰብ ውስጥ የልጅነት ዘመኗን ማሳለፍ ባለመቻሏ በጎዳና ሕይወት ለአስከፊ ችግሮች ለመጋለጥ ተዳርጋ የነበረች ናት።

ዝናሽ በዛብህ ትባላለች፤ ወላጅ አባቷን አታውቀውም። እናቷ ሌላ ባል ስለአገባች ከእንጀራ አባቷ ጋር መኖር የግድ ይሆንባታል፤ እንጀራ አባቷ ግን አልተመቻትም። የራሱን ልጆች እንድትጠብቅለት እንጂ እንደ እኩዮቿ ወጥታ ከትምህርት ገበታ በሚገባ እንድትቋደስ እድሉን አልሰጣትም። የተሻለ ቢሆን ብላ በማሰብ እናቷ ወደ ቤተሰቦቿ ብትወስዳትም፤ የእናቷ እናት አባት /አያቶቿም/ ሥራ ጫና ስለሚያሳድሩባት አሁንም ለመማር እድሉን አላገኘችም።

እናት አሁንም ግራ ሲገባት ዝናሽን ገና ለሥራ ባልደረጀ እድሜዋ፤ ሰርታ እንድትበላ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ላከቻት፤ አዲስ አበባም ዝናሽን እንዳሰበችው በደስታ አልተቀበለቻትም። «ለነገዋ የሴቶች ማገገሚያ ማዕከልን እስክትቀላቀል ድረስ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እያደረች፤ በሱስ አረንቋ ተዘፍቃ በመሞትና መኖር መሃል ሆና ለመኖር ተገደደች።

ዝናሽ ትውልዷ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በወላይታ ዞን ነው። ዝናሽና ቤተሰቦቿ ግን በሥራ ምክንያት «ዎይጦ» በሚባል አካባቢ ነበር የሚኖሩት። “ወላጅ አባቴ ማን እንደሆነ አላውቅም፤ ስመጣ ስንት ዓመቴ እንደሆነም አላውቅም። ከህጻንነቴ ጀምሮ ያደኩት በእንጀራ አባቴ ስር ሆኜ ነው። ትምህርት ብጀምርም፣ እኩዮቼ የደረሱበት ለመድረስ ግን እድሉን አላገኘሁም። ምክንያቱ ደግሞ እንጀራ አባቴ ነበር፤ ትምህርት ያቋረጥኩበትንም አጋጣሚ ዛሬም ድረስ አስታውሰዋለሁ።›› ትላለች።

“አንድ ቀን ትምህርት ቤት ሄጄ ስመለስ ለምን ልጆቹን ጥለሽ ሄድሽ ብሎ እንጀራ አባቴ በጣም ደበደበኝ። ከዛ በኋላም ትምህርት ቤት መሄድ ብጀምርም፣ ሁልጊዜ ከትምህርት ቤት ስመለስ የእንጀራ አባቴ ይሄን አጠፋሽ፣ ይሄን አደረግሽ ብሎ ይቆጣኝና ይመታኝ ስለነበር ትምህርቴን መቀጠል የምችልበት ሁኔታ አልነበረም። በዛ የተነሳ በልጅነቴ መማር እየፈለኩ ሳልማር ቀረሁ። ” ስትልም ታብራራለች።

እንጀራ አባቴ እንድማር ሳይሆን፤ ልጆቹን እንድንከባከብለት ብቻ ነው የሚፈልገው። አያቴ አጠገብ ስቀመጥ ደግሞ የሥራ ጫና ይበዛብኛል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ በአንድ ወቅት እናቴ ለበዓል ወደ ቤተሰቦቿ «አረካ» ወደ ምትባል ከተማ ይዛኝ ሄደች። በዛ ወቅት እናቴ እኔን የት ማስቀመጥ እንዳለባት በጣም ግራ ገብቷት ነበር። በመጨረሻም አማራጭ ስታጣ ሰርቼ እንድበላ በሚል ወደ አዲስ አበባ ላከችኝ ትላለች።

ዝናሽ በወቅቱ ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ ብቻዬን ነኝ ብላ አልፈራችም። ምክንያቱም ከነበረችበት ሁኔታ አኳያ ስትመለከተው የተሻለ ነገር አገኛለሁ የሚል ሙሉ ተስፋ ነበራት። በደላላ አማካኝነት ለቤት ሠራተኝነት ተቀጠረች፤ ነገር ግን የሰው ቤት የኑሮ ጫናን መቋቋም አልቻለችም።

በተቀጠርኩበት ቤት እንድሰራ የምታዘዘው ነገር በሙሉ ከአቅሟ በላይ እየሆነ መጣ። ‹‹በወቅቱ እኔ ገና ልጅ ስለነበርኩ እና አቅሜም የጠነከረ ባለመሆኑ ብዙ ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎችን ለረዥም ሰዓት መሥራት እያቃተኝ መጣ። በየቀኑ አንድ ትልቅ ቤት እና አራት የልጆች ክፍሎችን ብቻዬን ማጽዳት ይጠበቅብኝ ነበር። ይህንን ስጨርስ ደግሞ በየእለቱ ሌሎች የምታዘዛቸው በርካታ ሥራዎች አሉ›› ስትል የደረሰባትን ጫና ታብራራለች።

ዝናሽ ወደ እንደዚህ አይነት የሚያደክም ሥራ ሰርታ አታውቅም ፤ በዚህ ላይ ምግብ በሥርዓቱ አይሰጣትም። ‹‹ቁርስ እንድበላ የሚፈቀድልኝ አምስት ሰዓት ላይ ነው፤ የሚሰጠኝም አንድ ዳቦና ሻይ ብቻ ነው። በዚህ አይነት ተቀጥሬ በምሰራበት ቤት የኑሮ ጫናው በጣም ሲከብደኝና ከአቅሜ በላይ እየሆነ ሲመጣ ተማረርኩና የሰራሁበትንም ገንዘብ ሳልቀበል ልብሴንም ሳልወስድ ከቤት ጠፍቼ ወጣው›› ስትል ገልጻለች። ዝናሽ ከዚያ በኋላ ተመልሳ ሰው ቤት አልተቀጠረችም። የምትሄድበት ዘመድም አልነበራትም፤ የጎዳና ሕይወትን ተቀላቀለች።

ዝናሽ በተቀጠረችበት ቤት በየእለቱ ይገጥማት የነበረውን ችግር አልፋለሁ ብላ የደረሰችበት ውሳኔ እንደሰባቸው ሳይሆን ሌላ ጉድ አስከትሎባት አረፈው። ምንም ለውጥ፣ ምንም ሰላምና እረፍት ሳታገኝ ወደ አዲስ አበባ መጥታ መኖር ከጀመረች ዓመታት ተቆጠሩ። በእነዚህ ዓመታት እናቷን ተመልሳ ሄዳ ለመጠየቅም አልቻለችም ። ምክንያቷ ደግሞ እናቷ የምታውቀው ሰው ቤት ተቀጥራ እየሰራች እንደሆነ ነው። የዝናሽ የእለት ከእለት ጥያቄ ከጎዳና ሕይወት እንዴት ልውጣ ? ወደ እናቴ እንዴት ልሂድ ? የሚል ሆነ።

ከገባችበት አጣብቂኝ በቀላሉ መፋታት አቃታት። አንዴ ጎዳና ላይ የወጣ ሰው በማህበረሰቡ የሚሰጠው ግምት አሉታዊ መሆኑ ይበልጥ እያመማት መጣ፤ በዚህ ሕይወት ውስጥ የቆየ ሰው ዋስ አያገኝም፤ እናም ሰው ቤት ተቀጥሮ መሥራትም ሆነ በሆቴልና በመሳሰሉት አስተናጋጅነትን ማግኘት የማይታሰብ ሆነ።

አንድ የነበራት አማራጭ ሃሳብ በተለምዶ «ጀብሎ» የሚባለውን ሥራ ነው። ይህም በየጎዳናው እየዞሩ እንደ ሲጋራ፣ ሶፍት፣ ማሲቲካና የመሳሰሉትን ቀላል ሸቀጦች በካርቶን እያዞሩ መሸጥ ነበር። ዝናሽም በዚህ እንኳን ብለወጥ ብላ በቀጥታ ወደ ሥራው ገባች።

ሥራውን የጀመረችው የ40 ብር ሶፍት ገዝታ በመሸጥ ሲሆን፣ ከዛ በኋላ ማስቲካና ሌሎች ነገሮችንም በመጨመር እስፋፋችው፤ ይሁንና እሱም ሳይሳካላት ቀረ። ‹‹አንዳንድ ሰዎች በኋላ እከፍላለሁ ብለው ሲጋራ ይወስዱና ገንዘቡን አይሰጡም፡›› ትላለች።

በመሀል ሌላ ነገር አስባ ሲጋራ መሸጡን አቆመችው። ‹‹እቃዎቼን ዘበኛ ቤት በክፍያ እንዲያስቀምጡልኝ ተስማማን። “እቃውን እንዲጠብቁ ያስቀመጥኩት ቦታ ተመልሼ ለመውሰድ ስጠይቅ ሁለት ሺህ ብር ተጠየኩ። እንዴት ለዚህ ትንሽ እቃ ሁለት ሺህ ብር እከፍላለሁ ብዬ ብከራከርም። እቃውን ካስቀመጥሽ ብዙ ጊዜ ስለሆነ የኪራዩ አድጓል አሉኝ›› ያለችው ዝናሽ፣ ይህን እቃም ሌላ ሥራ ሰርቼ የእቃውን ብር መልሼ አገኛለሁ ብላ ተወችላቸው።

ምንም እንኳን ዝናሽ በወቅቱ የተወረሰባትን እቃ ሰርታ እንደምትተካው አስባ የነበረ ቢሆንም ፣ ተመልሳ ወደ ሥራ ለመሰማራት ሳትችል ትቀራለች። ይልቁንም የተለያዩ ሱሶች ውስጥ በመግባት ጎዳና ላይ መዞር፣ የቀን ተቀን ተግባሯ ሆነ። የመሥራት እና የመለወጥ ህልሟም በሱስ ውስጥ ተደበቀ። ከጓደኞቿ ጋር በየሆቴሉ በመሄድ የምግብ ትራፊ ለምኖ መብላትና ጎዳና ላይ ሲዞሩ ውሎ እዛው ጎዳና ላይ ማደር ሕይወቷ ሆነ። አብዛኛው የጎዳና ተዳዳሪ እንደሚያደረገው ሁሉ ብርዱንም ለመከላከል ረሀቡንም ለመረሳት እንደ ማስቲሽ ያሉ የሚያደነዝዙ ነገሮችን መጠቀምም ትጀምራለች።

‹‹ማስቲሽ በጣም እጠቀም ነበር፤ ምክንያቱም እሱን ከወሰድኩ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ እንኳን ቢጥል፣ ልብሴ ይበሰብስ ይሆናል እንጂ እኔ አይሰማኝም›› የምትለው ዝናሽ፣ እሱንም ማግኘት በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ታስታውሳለች። ማስቲሹን የሚሸጡልን ሰዎች ከቦታው በትንሽ ብር ቢያመጡም ለእኛ ግን የሚሸጡት በ100 ብር ነበር። እኔ ደግሞ እንደ ጓደኞቼ አለምንም፤ የሱስ ጥያቄዎችን ለመመለስ ከጓደኞቼ እበደራለሁ ወይም እነሱ ይሰጡኛል። ለቁም ነገር ሲሆን እንጂ፣ ለሱስ ሲሆን ሰው ለመስጠት አይሰስትም›› ትላለች።

ለሱስ የሚሆን ገንዘብ ተበድራ ብትወስድም የመመለስ አቅሙ የሌላት ዝናሽ፣ “እኔ መለመንም ስለማልችል ከየት አምጥቼ እመልሳለሁ፤ ገንዘቡን ከወሰድኩ በኋላ ተደብቄ ነው የምንቀሳቀሰው። ብዙ ጊዜ ቢያበድሩኝም መልሰው አይጠይቁኝም፤ እኔም ካገኘሁ ግን እከፍላለሁ” ትላለች። በዚህ አይነት አስፈሪና ተስፋ አስቆራጭ ሕይወት ውስጥ እያለች ነበር ሕይወቷን የሚቀይር አጋጣሚ የተፈጠረው። የነገዋ የሴቶች ማገገሚያ ማዕከልን እንድትቀላቀል ተደረገ።

ማዕከሉን የተቀላቀለችበትን አጋጣሚ ታውስታወሳለች። ‹‹ ወደ ማዕከሉ ልገባ የቻልኩት እንዲህ ነው፤ አንድ ቀን ጠዋት ተኝታ ባለችበት ወደ ቤቷ የሄዱ ልጆች የነገዋ የሴቶች ማገገሚያ ማዕከል የሚባል ድርጅት እንዳለ ይነግሯታል፤ ሕይወትሽ እንዲስተካከል ለምን እዛ አትገቢም ብለው ይጠይቋታል።

እሷም ወደ ማዕከሉ የገቡ ጓደኞች እንዳሉ ታውቃለች። ከእነሱም ስለማዕከሉ የሰማችው ስለነበር ሳታመነታ ወደ ማዕከሉ እንደምትገባ አረጋጠችላቸው። መዘገቧት፤ ‹‹ወዲያውኑ ወደ ማዕከሉ እንደምሄድ ተነገረኝና ይዘውኝ ተንቀሳቀሱ። ለተወሰነ ጊዜም ዘነበ ወርቅ አካባቢ ማቆያ ውስጥ ከሰነበትኩ በኋላ ወደ ነገዋ ማዕከል ገባሁ›› ስትል እንዴት ወደ ማዕከሉ እንደገባች ገልጻለች።

ጎዳና ላይ እያለሁ ወደ እንደዚህ አይነት ማዕከል እመጣለሁ ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላቅም። ወደ ማዕከሉ በምመጣበት ወቅትም እንደዚህ ሁሉም ነገር የተመቻቸለት ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ያለችው ዝናሽ፣ ማዕከሉ ገብታ ያለውን ነገር ስትመለከት ደስታዋን መግለጽ ተስኗት ነበር።

ሌሎች ድርጅቶች ሲረዱ ገንዘብ ብቻ የሚሰጡት። ይህ ማዕከል ግን ክፉና ደጉን እንድንለይ ጭምር አድርጎኛል ያለችው ዝናሽ፣ ጎዳና ላይ የነበረን ሕይወት በጣም አስከፊና አሳዛኝ ነበር፤ ከርሃቡ እና ከብርዱ ባሻገር በተባይ በጣም ተቸግሬያለሁ፤ የምቀይረው ልብስም አልነበረኝም። በየቀኑ ስለብሰው ከነበረው አንድ ቁምጣ፣ ቲሸርት እና አሮጌ ጃኬት ውጭ ሌላ ቅያሬ የሚባል ልብስም አልነበረኝም›› ስትልም አስታወሳለች።

“ጎዳና እያለሁ በንጽህና ጉድለት ምክንያት ፀጉሬ በተባይ የተሞላ ነበር፤ ስካርፍ አስሬ ነበር የምዞረው። መታጠብ ብዙም አይታሰብም፤ አንዳንድ መታጠቢያ ቤቶች ቢኖሩም፣ የሚያስከፍሉት 15 ብር ነው። ያን ብር ደግሞ ማግኘት ለእኔ ከባድ ነበር፤ ፀጉሬ እንዲህ ያደገውና የተዋበው ወደ ማዕከሉ ከገባሁ በኋላ ነው። ›› ትላለች።

በዚህ ላይ እናቷን ወደ ትውልድ አካባቢዋ ተመልሳ ሄጄ ለማየት በጣም ብትፈልግም ነገሮች የሚሳኩ አልነበሩም። ይህ ሁሉ ተደማምሮ አንዳንድ ጊዜ ምሬቱ ሲበዛበት ብቻዋን ታለቅስ እንደነበርም ትናገራለች።

ዝናሽ ጎዳና ላይ ያሳለፈችው ሕይወት እጅጉን አስከፊ ስለነበር የለመደችውን ተቆጣጣሪ የሌለበትን ኑሮ በመተው አዲስ ሕይወት ለመጀመር በውስጧ የፍርሃት ስሜት አላደረባትም። ወደ ማዕከሉ ለመግባት አንድ ስጋት ብቻ ነበረባት፤ እሱም በጎዳና ከለመደችው የማስቲሽ ሱስ እንዴት እላቀቃለሁ የሚለው ብቻ ነበር። እሱንም ቢሆን ከዛ አስከፊ ኑሮ ለመውጣት ወስና ስለነበር አምርራ ታገለችውናም ነገሮች ሁሉ ተሳኩላት።

ዝናሽ በአሁኑ ወቅት ከዚያ ሁሉ ስቃይ የበዛበት ሕይወት ተላቃ በማዕከሉ በነበራት ቆይታ የሆቴል መስተንግዶ ስልጠና ወስዳ ለመመረቅ በቅታለች። በስልጠናው ሆቴል ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ማሽኖችን እንዴት ማንቀሳቀስ እንደሚቻል፤ እንግዳን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባት እና ሌሎች አስፈላጊ ትምህርቶችን ለመቅሰም በቅታለች።

በዘርፉ ስልጠና ለመውስድ የፈለገችው በማንም ግፊት ሳይሆን በራሷ ፍላጎት እንደሆነም ትናገራለች። እነ ዝናሽ ወደ ማዕከሉ ገብተው አንድ ወር ከተቀመጡ በኋላ ነበር የሚሰለጥኑበትን የሙያ ዘርፍ እንዲመርጡ እድሉ ተሰጥቷቸው ነበር።

ሙያውን የመረጥኩት ራሴ ነኝ፤ በወሰድኩት ስልጠናም በጣም ደስተኛ ነኝ ስትልም ትገልጻለች። ዝናሽ በቀጣይ በሰለጠነችው ዘርፍ ለተወሰነ ጊዜ ከሰራች በኋላ እናቷን ሄዳ ለመጠየቅ እቅዳለች። ከዚያም ስትመለስ ሥራዋን ጠንክራ በመሥራት በተቻላት አቅም ሌሎች የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ሃሳቡ አላት። በማዕከሉ ላስተማሯት እና በአጠቃላይ ድጋፍ ላደረጉላት አካላት ሁሉ ምስጋናዋን አቅርባለች።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You