ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የደመቁበት የፍራንክፈርት ማራቶን

የፍራንክፈርት ማራቶን ለ41ኛ ጊዜ ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጀርመኗ ከተማ ደምቀው ውለዋል። በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ሀዊ ፈይሳ የውድድሩን ክብረወሰን በማሻሻል ስታሸንፍ በወንዶች ከሁለት እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

የ25 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሀዊ 2:17:25 በማስመዝገብ የውድድሩን ክብረወሰን በ1:45 ማሻሻል ችላለች። ይህም በ2024 አስራ ሁለተኛው የማራቶን ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። የፍራንክፈርት ማራቶን የቀድሞው ክብረወሰን በኬንያዊቷ አትሌት ቫላሪ ኢያቤ 2019 ላይ የተመዘገበ ነበር።

ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ አትሌት ማዳላይን ማሳይ ያስመዘገበችው 2:18:58 ሰዓትም የግሏ ፈጣን ሰዓትና ከቀድሞው የውድድሩ ክብረወሰን 2:19:10 የተሻለ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሹኮ ገነሞ 2:22:37 በማጠናቀቅ ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች።

ከአጭር ርቀት ውድድሮች ጀምሮ አስደናቂ ብቃት ማሳየት የቻለችው ሀዊ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ፊቷን ወደ ማራቶን አዙራለች። በ2023 የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ሀዊ ፍራንክፈርት ላይ በማራቶን ያስመዘገበችው ሰዓት በርቀቱ ትልቅ ስኬቷና ተስፋ እንዲጣልባት ያደረገ ነው።

“የውድድሩን ክብረወሰን ማሻሻል ትልቁ ግቤ ነበር፣ ከ25ኛ ኪሎ ሜትር በኋላ ይህን ግቤን ለማሳካት በቂ አቅም ስለነበረኝ ከተፎካካሪዎቼ ተነጥዬ ወደ ፊት በመውጣት ተጠቅሜበታለሁ፣ በዚህም በጣም ተደስቻለሁ፣ የውድድሩ ጥሩ ድባብም ረድቶኛል፣ በዚህ ውድድር ከ2:16 በታች ማጠናቀቅ እንደሚቻልም ተገንዝቤያለሁ” በማለት ባለድሏ አትሌት ከውድድሩ በኋላ በስፍራው ለነበሩ ሚዲያዎች አስተያየቷን ሰጥታለች።

ከውድድሩ ቀደም ብሎ ከ2:21:17 የፈጠነ ሰዓት ያለው አትሌት አልነበረም። በዚህም ሀዊ በፈለገችው ፍጥነት የመሮጥ እቅድ የነበራት ቢሆንም የውድድሩ አዘጋጆች እስከ 25 ኪሎ ሜትር ድረስ አትሌቶች በጋራ እንዲሮጡ ፍላጎት ነበራቸው። ይህም ታክቲክ ሰርቶ የቦታው ክብረወሰን ሊሻሻል እንደቻለ ተናግራለች።

በፍራንክፈርት ማራቶን ሁለት አትሌቶች ከ2:20 በታች ሲያጠናቅቁ የዘንድሮው የመጀመሪያ ነው። እስከ አስር ባለው ደረጃ ያጠናቀቁ አትሌቶች የግል ፈጣን ሰዓታቸውን ማሻሻላቸውም የዘንድሮውን ውድድር የተለየ አድርጎታል።

በወንዶች መካከል የተካሄደው ውድድር ክብረወሰን ባይመዘገብበትም አዲስ ነገር የታየበት ነበር። ይህም በማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ የተፎካከረው የ22 ዓመቱ ኬንያዊ ቤናርድ ቢዎት በ2:05:54 ማሸነፍ መቻሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊው ጎሳ ጫላ 2:07:35 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ሌንጮ ተስፋዬ ደግሞ 2:08:02 በመግባት ሦስተኛ ሆኖ የፈፀመ አትሌት ነው።

ገርባ ዲባባ፣ አይቼው ደምሴ፣ ወርቅነህ ሰርባሳ በቅደም ተከተል እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን ሆነዋል።

በሁለቱም ፆታ አሸናፊ የሆኑት አትሌቶች ርቀቱን ያጠናቀቁበት ድምር ሰዓት 4:23:19 ሲሆን ይህም በፍራንክፈርት ማራቶን የረጅም ዓመት ታሪክ ፈጣኑ ድምር ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። በአጠቃላይ በውድድሩ ከ113 ሀገራት የተውጣጡ 13ሺ 939 አትሌቶች የዘንድሮው ፍራንክፈርት ማራቶን ተፎካካሪና ድምቀት እንደነበሩም የውድድሩ አዘጋጆች ገልፀዋል።

“የውድድሩ ክብረወሰን የተሻሻለበትን ፉክክር በማየታችን ተደስተናል፣ ፍራንክፈርት ላይ ፈጣን የማራቶን ሰዓት መመዝገብ እንደሚችልም አረጋግጠናል” በማለት የውድድሩ ዳይሬክተር ፊሊፕ ክሎፕ ለሚዲያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You