አዲስ አበባ:– ፍትህ ሚኒስቴር ሄግ ከተባለ የሕግ ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በመሬት ጉዳይ የሚነሱ አለመግባባቶች እና ግጭቶችን ወጪ ቆጣቢ እና ማህበረሰብን ማዕከል ባደረገ መልኩ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ።
መርሀ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እና የሄግ ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳሙኤል ሙለር (ዶ/ር) ትናንት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በሶስት ማዕከላት የማህበረሰብ ፍትህን ለማቋቋም ያስችላል ያሉት ኤርሚያስ(ዶ/ር)፤ ለማእከላቱ ለሚያስፈልጉ ወጪዎች እና ግብአቶች እንዲሁም በማእከሉ ለሚሰሩት አሸማጋዮች ክፍያ ድጋፍ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል።
ትግበራው በኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና አዎንታዊ ሚና የሚኖረው መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ማዕከላቱን በማቋቋምና በማጠናከር የመሬት ጉዳይ ከመደበኛ ሥርዓት ውጪ በኢ-መደበኛ ሥርዓት በባህላዊ መንገድ በአሸማጋዮች እንዲፈታ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ትግበራው የማህበረሰብ ፍትህን ለማስፋፋት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር)፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በሲዳማ እና በአፋር ክልሎች በሙከራ የሚተገበር መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ አለመስማማት ይነሳባቸዋል ተብለው ከሚጠቀሱት የቤተሰብ ጉዳይ እና የውርስ ግጭት በበለጠ ዋነኛው የመሬት ጉዳይ ነው። የመሬት ጉዳይ ከኢኮኖሚ ጉዳይ ባለፈ የማንነትና የማህበራዊ ይዘት ያለው እና ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው ሲሉም አክለዋል።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ በሂል አማካኝነት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በዓመት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ መሬት ላይ መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ይነሳሉ።
ስምምነቱ በመሬት ጉዳይ የሚነሱ አለመግባባቶች እና ግጭቶችን ማህበረሰብን ማዕከል ባደረገ፣ አሸማጋዮችን ባሰባሰበ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚተገበር ነው።
በኢትዮጵያ ከሕገ መንግስቱ ጀምሮ የመሬት ውርስ፣ የመሬት ይዞታ፣ የድንበር ማካለል፣ የመሬት ግጦሽ፣ በግለሰቦች መካከል የሚያጋጥሙ አለመግባቶች እና በማህበረሰቦች መካከል የሚያጋጥሙ ግጭቶች የሚፈቱበት የዳበረ የህግ ስርዓት መኖሩንም አመላክተዋል።
የትራንስፎርሜሽን ትግበራ፣ የአቅም ግንባታ እና የቴክኒክ ድጋፎችን በጋራ ለመስራት እንደሚያስችል በስምምነቱ ወቅት የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይ የማዕከላቱን ውጤት በመመልከት በሁሉም አካባቢዎች እንዲስፋፋ እንደሚደረግም ተገልጿል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም