ባለፈው ሳምንት በዚሁ አምድ እትማችን ከሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ያገኘነውን መረጃ መሰረት አድርገን የዘንድሮው የአየር ንብረት ሁኔታና የዝናብ መጠን በጥሩ ሁኔታ ላይ ስለመገኘቱ ማስነበባችን ይታወሳል።
የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታው በሁለንተናዊው የእድገት ዘርፍ ላይ የሚኖረውን አስተዋፅኦና ተፅእኖ፤ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ስለሚኖረው የማይታለፍ ወሳኝ ሚና እንዲሁም ግብርናው ለኢኮኖሚው እድገት ስለሚኖረው የአንበሳ ድርሻ ተመልክተናል።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ካሉት ዞኖች መካከል አንዱ ወደ ሆነው አርሲ ዞን ተጉዘን ባደረግነው የመስክ ምልከታም የተመለከትነው ይህንኑ መልካም የአየር ጠባይ፣ የዝናብ መጠንና በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን የግብርናው ዘርፍ እንቅስቃሴን ነበር።
በዞኑ ስር ባሉ የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ተዘዋውረን እንደተመለከትነው በአንድ በኩል አርሶ አደሩ በማሳው ላይ በሬውን ጠምዶ ተፍ ተፍ ሲል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች በመታገዝ ሲያርስ፣ ሲያለሰልስና ሲዘራ ይታያል።
በአካል ተገኝተን በተመለከትናቸው አካባቢዎች የእርሻ መሬቶች ሲታረሱ፣ የታረሱትም ዘር ለመቀበል ዝግጁ በመሆን ጊዜያቸውን ሲጠባበቁ፣ ጊዜያቸው የደረሰም ሲዘራባቸው፤ ባጠቃላይ ወርቃማ የመኸር ወቅት የግብርና እንቅስቃሴ ያለበት ሆኖ ነው ያገኘነው።
ወደ መስኖ ልማትም ስንሄድ ያገኘነው ተመሳሳይ ሂደትን ነው። እዚህም እዚያም ድቡልቡል/የወጥ ድንችን የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶች ይታያሉ። ውሀ በ“ካነል” አማካኝነት በየጓሯቸው የገባለቸውም በመስኖ ልማት ስራ ተጠምደው ነው የሚታዩት።
ለጊዜው ዋናው ጉዳያችን ከሰብል ምርት ጋር የተያያዘ ነውና ወደ እሱው እንሂድ። በተለይ ከስንዴ እና ገብስ ሰብል፣ ምርትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ምን እየተረገ እንደሆነ ማየት የዚህ ፅሁፍ አላማ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አማካኝነት የተጋበዘውን፤ ያለውን ሁኔታ እንዲጎበኝ ወደ አርሲ ዞን የተጓዘውን የጋዜጠኞች ቡድን አሰላ ከተማ ላይ ተቀብሎ ወደ የወረዳዎቹ ያቀናው የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት ሲሆን በየደረስንባቸው ወረዳና ቀበሌዎችም ያሉት አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አርሶ አደሩ ማህበረሰብ እየተቀበሉ አስተናግደውታል (ለዛውም እዚህ አዲስ አበባ ካለው ኬክና ዳቦ የሚበልጠውን የስንዴ ዳቦ እየገመጠ)። በጉዞውም ሆነ በምልከታው ወቅት ጋዜጠኛው የፈለገውን እንዲያይ፣ ያልገባውን እንዲጠይቅ፣ “እፈልገዋለሁ” ያለውን መረጃ እንዲያገኝ መንገዱ ሁሉ ክፍት ነበር።
በተለይ የሚዲያ አባላቱ ጉዞ አቢይ አላማ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ከማፋጠን አኳያ ምን እየተደረገ እንዳለ ለመመልከት ነበርና የመጀመሪያው የምልከታ ምእራፍ ያረፈው በዚሁ ዘርፍ እየተከናወነ ወዳለው የእርሻ ማሳ ነበር – በአርሲ ዞን፣ ዲገሉና ጢጆ ወረዳ ስር ወደሚገኘው ፊቴ ከታራ ቀበሌ።
ምልከታው በፊቴ ከታራ ቀበሌ በሚገኘውና የ107 አርሶ አደሮችን፤ በጥቅሉ 316 ሄክታር መሬትን ከሚሸፍነው ክላስተር (በኩታ ገጠምነት ያካተተ) የተጀመረ ሲሆን፤ ሰአቱ መሬቱ ታርሶ፣ ለስልሶና የመጨረሻው ምእራፍ ላይ በመድረስ “በመስመር መዝረያ ትራክተር ማሽን” አማካኝነት በምርታማነቱ የታወቀው ኦጎልቾ ስንዴ የሚዘራበት ነበር።
በማሳው ላይ ቆመን ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ያልናቸውን ኃላፊዎችና ባለቤቶቹን አርሶ አደሮች ያነጋገርን ሲሆን በቅድሚያ ያገኘናቸው የዞኑን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባቡ ዋቆን ነበር። እሳቸውም “በመጀመሪያ ኩታ ገጠም መሬቶች ይዘጋጃሉ፣ ሰፊ ምርት ለማምረት እንዲቻል በክላስተር ይደራጃሉ፤ ይህ ክላስተር በተመሳሳይ ሰአት በተመሳሳይ ማሽን ይታረሳል፣ ተመሳሳይ ዘር ይዘራል፣ ተመሳሳይ እንክብካቤና አያያዝ ይደረግለታል። ይህ እስከ ገበያ ትስስር ድረስ ለሚዘልቅ አሰራር ምቹ ነው።” በማለት የክላስተር አሰራር (Cluster approach)ን ስልትና ፋይዳ አብራርተዋል።
ሂደቱ በምርትና ምርታማነት ብቻ ሳይቆም “የገበያ ሁኔታንም ይመለከታልና ከዚህ አኳያ እንዴት ነው? ምንስ ታስቧል?” የሚለውንም በተመለከተ ከበፊቱ ደላላ መር አሰራር በመማር አዲስ አይነት የገበያ ትስስርን እየፈጠሩ መሆናቸውን ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል። “በአሁኑ ሰአት እንዴት እሆናለሁ፣ ማን ይገዛኛል ወዘተ የሚል የገበያ ስጋት አርሶ አደሩ ጋር የለም። ከገዥ/ ተቀባይ/ሸማች ዩኒየኖች፣ የዱቄት ፋብሪካዎችና ቢራ ጠማቂዎች ጋርም የንግድ ስምምነት ውል እየተፈራረሙ ስለሆነ ችግሩ ከወዲሁ ተቀርፏል ማለት ነው። በዞናችን የዘንድሮውን መኸር ለየት የሚያደርገውም በዞናችን የሚገኙ ሁሉም ክላስተሮች በዚህ አይነቱ አሰራር ሂደት ውስጥ መሆናቸው ነው።” በማለትም አጠቃላይ የገበያ ትስስሩን ሁኔታ ይገልፁታል።
ቀጥለን ያነጋገርናቸውና የዘመናዊ ግብርናውን ጠቀሜታ፣ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትና በወረዳቸው በሚገኙ 25 የገጠር ቀበሌ ውስጥ የተፈጠረውን የምርትና ምርታማነት እድገቱን ያስረዱንን የወረዳው አስተዳደር አቶ አወል ዋፎን ነበር።
አቶ አወል እንደነገሩን በወረዳቸው ውስጥ 3ሺህ 246 ክላስተር በስንዴ፤ 1ሺህ 582 ክላስተር በገብስ አዝርእት፤ ባጠቃላይ 3ሺህ 33 ሄክታር መሬት በክላስተር ይለማል። “በወረዳችን ዘር እየመጠነ የሚዘራ ዘመናዊ ማሽን መጠቀም ከጀመርን ትንሽ ቆይተናል። በዚህኛው ፈጣንና ጉልበተኛ የመዝሪያ ማሽን (ኤሮ ፕላንተር) መጠቀም የጀመርነው ግን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን አርሶ አደሩን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ አድርጎታል። በበሬ ከማረስ ገላግሎታል፣ ጉልበቱን ከማፍሰስ ገላግሎታል፣ ጊዜ ከማባከን ገላግሎታል። ከሁሉም በላይ ከፍተኛ ምርት እንዲያገኝ አድርጎታል። በአሁኑ ሰአት በስንዴ 6ሺህ 329፤ በገብስ 3ሺህ 33 አርሶ አደር በክላስተር በመታቀፍ የሜካናይዝድ ግብርናው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ነው። ወደ ላይ ወደ ደጋው ስንሄድም ለቢራ ገብስ የሚውል 112 መሬትን የሚሸፍን ክላስተር አለ።” ሲሉም አስረድተውናል።
“የዘንድሮውን የመኸር ወቅት እንዴት ያዩታል?”ም ብለናቸው ነበር። አቶ አወልም “በጣም ጥሩ ነው።” ካሉ በኋላ “በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ በሄክታር 111 ነጥብ 5 ኩንታል በማምረት በአገር አቀፍ ደረጃ ሪኮርዱን የያዝነው እኛ ነበርን። በኋላ ባሌ ዞን (ጊኒር ላይ) 113 ነጥብ 5 ኩንታል በማድረስ ተነጥቀናል። ዘንድሮ እሱን ማስመለስ አለብን ብለን ጠንክረን እየሰራን ነው።” በማለት ፈገግ አሰኝተውናል። የባሌ/ጊኒሮችን ባናውቅም፤ እንደ አያያዛቸው ዲገሉና ጢጆዎች የሚሳካላቸው ይመስላል።
የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ አወልን የወረዳውን ህዝብ ኢኮኖሚያዊ አቅም በተመለከተ “በኢኮኖሚው ወደ ተሻለ ደረጃ ተሸጋግሯል ብለው ያስባሉ?” ብለናቸው “የኛ ወረዳ ለፓስታና ሞኮሮኒ ፋብሪካዎች፣ ለዳቦ ጋጋሪዎች፣ ለቢራ ጠማቂዎች ግብአት የሚያቀርብ ህዝብ ነው። የገንዘብ ችግር የለብንም። በኛ ወረዳ አንድም በገንዘብ የሚረዳም ሆነ በመንግስት የሚደጎም፤ የተራበ ሰው የለም።” በማለት መልሰውልናል።
ሌላው አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የፊቴ ከታራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከበደ ገበቴን ሲሆን እሳቸውም “የአሁኑን ከድሮው ጋር ማወዳደር አይቻልም። ይህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ (የዘር መዝሪያ ማሽን) ከመጣ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ነው የሆንኩት። እራሱ ማዳበሪያ ይሰጣል፤ እራሱ ዘሩን ይዘራል። ሁሉን ነገር እራሱ እየመጠነ፤ የሚገባውን ያህል ብቻ እንዲያገኝ እያደረገ ለመሬት ይሰጣል። እኔ በሄክታር እስከ 85 ኩንታል ድረስ አግኝቻለሁ። ዘንድሮም ከዛ የበለጠ ነው የምጠብቀው።” በማለት የዘመናዊ ቴክኖሎጂውን ጠቀሜታ ተናግረዋል።
“ሌሎች አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ ምን ይመክራሉ?” በማለት ጠይቀናቸው “ምን ጥያቄ አለው። ሁሉም ይሄንን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ (ማሽን) መጠቀም ነው ያለበት። ካልሆነ ታዲያ እንዴት ይሆናል? በእኔ እና በሌሎች መካከል እኮ ከፍተኛ ልዩነት አለ። ስለዚህ ሁሉም ገበሬ መጠቀም ነው ያለበት።” የሚለው መልሳቸውም፤ ምክራቸውም ነበር።
የዘመናዊ ቴክኖሎጂውን ፈርጀ-ብዙ ፋይዳንም “እኔ የምመክረው ሁሉም፣ በሞላ ኢትዮጵያ ያለ አርሶ አደር ይሄንን ዘዴ (“Cluster approach” ማለታቸው ነው) ቢጠቀም ጥሩ ነው ብዬ ነው የምመክረው።” ሲሉ በመግለፅ ነው አርሶ አደር ከበደ ሌሎች መሰሎቻቸው ወደዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እንዲመጡ የሚመክሩት።
አርሶ አደር ከበደ ገበቴ ዘመናዊው ማሽን ብዙ ምርት በማስገኘት ኢኮኖሚያዊ አቅምን ከማሳደግ ባለፈ “ስራን ያቀላል፣ ያቀላጥፋል፣ ጊዜና ጉልበትን ይቆጥባል” የሚለውን ደጋግመው ነግረውናል። ተጠቃሚነታቸውንም በተመለከተ “ድሮ በእጅ ስሰራና ስዘራ 30 እና 35 ኩንታል ካገኘሁ ጥሩ አገኘሁ ማለት ነበር። አሁን በሄክታር እስከ 85 ኩንታል፤ አንዳንዴም ከዛ በላይ አገኛለሁ። ዘንድሮ ደግሞ ካለፉት አመታት ካገኘሁት በላይ እጠብቃለሁ። ምክንያቱም ዘንድሮ ሁሉም ነገር፤ አየሩም ጥሩ ነው።” ሲሉ ነግረውናል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሸጋገር የግብርናን የማይተካ ሚና አጥብቃ ታምናለች። ይህንን ደግሞ የማያውቅና ያልተረዳ የለም ማለት ይቻላል። ባሁኑ ሰአት የ“ፍላጎትና አቅርቦት” ፅንሰ-ሀሳብም ማህበረ- ኢኮኖሚያዊ አንድምታው ለብዙዎቻችን ሚስጥር አይደለም፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ፋይዳ ብዙ እየተባለለት ያለ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ባለመጠቀማችን መዘባበቻ እየሆንን እንገኛለን። ከዚህ አንፃር በኦሮሚያ ክልል፣ አርሲ ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ እየተካሄደ ያለው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብርና እንቅስቃሴ በተምሳሌትነቱ በሁሉም አካባቢ ሊወሰድ ይገባል እንላለን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2011
ግርማ መንግሥቴ