አዲስ አበባ፡- በ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን ከዓምናው የተሻለ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየሠሩ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና የትግራይ የክልሎች ገለጹ፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበኸር ኃሊፍ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በክልሉ በ2016/17 ዓ.ም የመኸር ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሁሉንም የእርሻ መሬት በዘር የመሸፈን ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን አንድ ሚሊዮን 308 ሺህ 77 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን አርባ አምስት ሚሊዮን 184 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በምርት ዘመኑ በሰብል ለመሸፈን ከታቀደው አንድ ሚሊዮን 308 ሺህ 77 ሄክታር ውስጥ 917 ሺህ 294 ሄክታሩ ታርሷል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ውስጥ ከ854 ሺህ 418 ሄክታር መሬት በላይ በዘር ተሸፍኗል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የክልሉን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሶስት መቶ ሰባ ሺህ 229 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ በዘር በመሸፈን አስር ሚሊዮን አርባ ስምንት ሺህ 566 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ባበኸር፤ ከ370 ሺህ 229 ሄክታር መሬት ውስጥ 53 ሺህ 705 ሄክታር የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል በግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ኃይሌ ዓባይ በበኩላቸው፤ በክልሉ አንድ ነጥብ ሶስት ሄክታር መሬት በተለያዩ አዝርት በመሸፈን ሃያ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ለአርሶ አደሮች አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ምርቱ ተሰብስቦ ጎተራ እስኪገባ ድረስ ድጋፉና ክትትሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አመላክተዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 /2016 ዓ.ም